February 17, 2019e

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2011 (ኤፍቢሲ) የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና የባህል ቡድን ከአማራ ክልል ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የበለጠ የሚያጠናክር ወይይት አካሂዷል።
በወይይቱም በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር አርዓያ ደስታ እና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አቶ አሰማኸኝ አስረስ የአማራና የኤርትራ ህዝቦች የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው የተዋሐዱ ህዝቦች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ህዝቦቹ በታሪክ ብቻ ሳይሆን በደም የተሳሰሩ ሊነጣጠሉ የማይችሉ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
የአማራና የኤርትራ ህዝቦች ለጥንታዊ እናት ምድራቸው ኢትዮጵያ ነጻነት አብረው የተዋደቁና የጋራ ታሪክ የሚጋሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ቀኝ አገዛዝን ከመታገል አንጻርም የአርበኝነት ትግል በማውሳት የጎጃሙን በላይ ዘለቀን እንዲሁም ዘርዓይ ደረስን አውስተዋል፡፡
በመጨረሻም የአማራ ህዝብ ለኤርትራ ህዝብ ልዩ ፍቅርና ክብር አለው ለዚህም በቅርቡ በደብረማርቆስ በባህርዳር ለኤርትራውያን ከ20 ዓመታት በኋላ የቀድሞ ቤታቸውን መልሰው ማስረከባቸውን እንደምሳሌ አስታውሰዋል፡፡
አምባሳደር አርዓያ ደስታ በበኩላቸው የጦርነትና የመራራቅ ዘመን ፀሐይ እንደመታው ጤዛ ተኖ በምትኩ የሰላም፣ የአንድነትና ወዳጅነት እንዲሁም የሙሉ ፀሐይ ጮራ ዘመን የምናይበት ጊዜ ሆኗል ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ራዕይ በሰንቀ አመራር ተመርተው የጦርነት ወሬ አልፎ የፍስሃ ዘመን ስለመምጣቱም ተናግረዋል።
55 አባላትን የያዘው የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ በትናንትናው ዕለት ነበር ባህርዳር የገባው።
በናትናዔል ጥጋቡ