February 19, 2019
(ዘርዘር ያለ ገለፃና ምልከታ ለማስቀመጥ የመግለጫው ሙሉ ሃተታን ማግኘትና ማጤን ይበጃል:: ይህ ለጊዜው የለኝም::

ኦዴፓ ለመደራደር የማይፈልገው በፌደራላዊ የመንግስት ቅርፅ (Form of Government) ላይ ከሆነ ችግር የለውም:: አሜሪካና ካናዳም ፌደራላዊ ናቸው:: የማይደራደረው ይህ የማይደራደርበት መንግስታዊ ቅርፅ የሚከተለው የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም (Political Ideology) አሁንም “የጎሣ ፌደራሊዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ከሆነ ይህ ከባድ ችግር አለው::
ምክንያቱም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ይህን የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም ማለትም “የጎሣ ፌደራሊዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ይዞና የማይደራደርበት ከሆነ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የገባውን ቃል አጥፎ የጎሣ የበላይነትን ለመጫን ተዘጋጅቷል ማለት ነው:: የለውጥ ጉዞው ተጨናግፏል ማለትም ነው:: ማንኛውም የመንግስት ቅርፅና (Form of Government) የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም (Political Ideology) ለድርድር ይቀርባል:: ለድርድር የማይቀርበው የሐገር ህልውና ብቻ ነው::
ይህ የኦዴፓ መስመር ግልፅ ከሆነ ውጤቱ ተደጋግፈን እንደቆምነው ተያይዘን እንዘቅጣለን። ይህን ከመረጡ። ኪሣራው ለኛ ትርፉ ለህወሃት ይሆንና እኛም እንደ ደቡብ ሱዳንና ፓኪስታን በስርዐተ አልበኝነት እንዲሁም በእርስ በርስ እልቂት ተያይዘን እንደቃለን።
በቅርቡም ይህን ብለን ነበር። ‘እኛ ለጠ/ሚ አቢይ አህመድና ቡድናቸውን ድጋፍ የሠጠነው በማፈግፈግ ላይ ያለውን የህወሃት – ወያኔ የአናሣ ቁጥር አፓርታይዳዊ ሥርዐት በብዙሃን ቁጥር አምባገነነት (tyranny of majority) ለመተካት አይደለም::
እኛ ለጠ/ሚ አቢይ አህመድና ቡድናቸውን ድጋፍ የሠጠነው የኢትዮጵያ አንድንትን የጠበቀ የሕግ የበላይነት የምድሩ ገዢ የሚሆንበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የሚመሠረትበትን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝብን የበላይንት ማረጋገጫ የሆነውን ዴሞክራሲ በተገባልን ቃል መሠረት ይከወናል፣ ይተገበራል ብለን እንጂ የአንድን ጎሣ ወይም የጎሣ ስብስብ የበላይነት የሚያረጋግጠውን ‘ኸረንቮክ ዴሞክራሲ (Herrenvolk Democracy’ እና ኢትኖክራሲን (Ethnocracy) ለመተካት እይደለም::
ኦዴፓ አሁንም በዚህ የፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም (Political Ideology) “የጎሣ ፌደራሊዝም” ላይ መደራደር ካልፈለገና የብዙ ቁጥር አምባገነንነትን ((Tyranny of Dictatorship) ወይም ኢትኖክራሲን ለመጫን ካለመ እኛም በዴሞክራሲ አንደራደርም::’
‘ጨዋታው ፈረሠ፣ ዳቦ ተቆረሠ’፣ ‘የፍፃሜው ጦርነት ነው’ ብለን የጨዋታው ፍፃሜም ይሆናል::

