February 19, 2019

ጉዳዩ- የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ለአማራው እንቅፋት በመሆን በእጅ አዙር ህውሀትን እየረዱ ነው!!

የአማራው ምሁር ( elite) ከጭፍን አንድነት እራሱን ቢያርቅና የራሱን የአማራ ድርጅቶች ቢያነቃቃና ቢያደራጅ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና መግባባት ይኖራል:: ይህ አንድ ህዝብ የዜግነት ፖለቲካና ጩኸት አማራው የበዛበት አካባቢ ደስ የሚል ወዘና ሊኖረው ይችላል ሆኖም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ወርዶ ስራ ላይ ቢውል አደገኛ መስመር ነው::ይህ ለዶክተር ዐቢይን የሚፈታተን ዶክተር ዐቢይም በኦዴፓ ውስጥ ድጋፍ የሚያሟሽሽ እሱንም ለአደጋ የሚያጋልጥ መስመር ነው::በዛሬዋ ኢትዮጵያ ምርጫ ቢመጣ ኦሮሞው ከኦሮሞ ድርጅቶች ውጪ ለማንም የአንድነት ፓርቲዎች ድምፅ አይሰጥም::ይህ ማንም ሊክደው የማይችለው መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው::ዐቢይና ቲም ለማ ከኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ወይንም ግንቦት 7 አልወለዳቸውም:: በኦሮሞነት ተደራጅተው ወደትግሉ ሜዳ ብቅ ያሉ ናቸው:: ባለፉት 27 አመታት የተበታተነውን ኢትዮጵያዊነትን እያሰባሰቡ ነው::የትግሬው  ምሁር ከትግራይ ውጪ የአንድነት ፖለቲካ ሲያራምድ አልታየም ወደፊትም አይታይም:: ያውም ትግራይ በዚህ ወቅት በስም እንጂ ተገንጥላ በራሷ የምትሽከረከር አዲስ ሀገር እየመሰለች ነው::በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 70 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች አሉ::ከነዚህ ውስጥ 80% የሚሆኑት በአማራ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚንቀሳቀሱ ናቸው:ብል አልሳሳትም::እነዚህ ስብስቦች እርስ በርስ ከመናቆር ውጪ ለህዝባቸው ምን የረባ ነገር በ27 አመታት አተረፉ? የአማራውን ድምፅና ጉልበት በመበታተን የበለጠ የወያኔን ሀይል እንዲጠናከርና ለረጅም አመታት እንዲገዛ እድል ሰጥተዋል:: ዛሬም አንድም ፋይዳ ላይጨምሩ ከኦሮሞ አክቲቪስቶች ጋር ግጭትን በመጋበዝ ጉልበት ኖሯቸው እንኳን ስለማይከላከሉ እነሱ በሚያቦኩት ስራና የስልጣን ሽኩቻ የፈረደበት ምስኪን አማራ እንዳይዘጋጅና እንዳይደራጅ እራሱን እንዳይከላከል የእነሱን ቡቱቶ የፖለቲካ ሸማ አልብሰውት ለጉዳት እየጋበዙት ነው::

አማራ በአማራነት ከተወነጀለ መደራጀት ያለበትና መታገል ያለበት በአማራነቱ ብቻ መሆን አለበት:: የ50 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድራማ አማራውን ጨቋኝ ሌሎችን ተጨቋኝ በሚል ትርክት ብዙ ፖለቲካ ተሰርቶበታል::አማራ ከአማራነቱ የሚያሸሸው ቆሻሻ ታሪክ የለውም:: ይህ እንዲሰመርበት ይገባል:: የአንድነት ሀይል ተብዬዎች አማራው በአማራነቱ ተደራጅቶ እንዳይከላከል የአነሱን የፖለቲካ መደብር ገቢያ ይሻማናል በሚል ስጋት አማራው ሳይደራጅ ለእልቂት እየጋበዙት ይገኛሉ::የአማራ ምሁር ተብዬዎች ለአማራው ኢትዮጵያዊነትን ለማስተማር ሲሞክሩና ሲፍጨረጨሩ ማየት  እጅግ ያሳዝናል:: አማራ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ህልም ኖሮት አያውቅም::ወደፊትም አይኖረውም::ይህ ያፈጠጠ ሀቅ ነው::

ከብዙ አመታት በሗላ ወደፊት በመግባባት ይህ የአንድነት ሁኔታ ስሜት በሌሎችም ሊለወጥ ይችል ይሆናል:: አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ መፈክር አማራ በበዛበት ልዩ ድምቀቱን አይተናል::እስቲ ነቀምቴና መቀሌ ላይ እንየው::ያኔ አናምናለን የህልም ኢትዮጵያና ዛሬ በተጨባጭ የምናያት ኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ናቸው::ይህ ሀቅ የማይዋጥላቸው እኛ እናውቅላችሗለን ባዮች –

1. የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ስራ ከንቱ ያደርጋሉ

2. የማያቋርጥ ጦርነትና የማንወጣው ውዝግብና መናቆር ውስጥ ይከተናል:: በዚህ ወቅት የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመመስረት ወቅቱ የሚጠብቀው አማራው ተደራጅቶ በአማራነት ከወንድሙ የኦሮሞ ህዝብና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የጋራ ፖለቲካ አጀንዳ ቀርፆ ሲንቀሳቀስ : በመከባበርና በተማመን ሀገሪትዋን ለማረጋጋትና ለማሳደግ ይቻላል::ድርጅት ሀይል እንደሆነ በአናሳው ህውሀት አይተናል:: 6 ሚሊዮን ህዝብ እወክላለሁ ብሎ የተነሳ ድርጅት 100 ሚሊዮንን ረግጦና ዘርፎ የገዛው በመደራጀቱ ብቻ ነው::ይህን ሀይል ማምከን የሚቻለው በመደራጀት ብቻ ነው:: አሁን በመሬት ላይ ያለው ሀቅ ከአማራ በስተቀር ሁሉም ተደራጅቷል::ከዚህ ውጪ ኦሮሞውም ተጨፍልቆ ኢትዮጵያዊ ላለመሆን የቆረጠ ይመስላል:: አያደርገውም::አማራውም በስሙ የሚነገድበት ሞግዚት አስተዳዳሪ አይፈልግም:: የሚያሳዝነው የአንድነት ሀይሎች ለዐቢይ እንቅፋት እየሆኑ በተዘዋዋሪ መንገድ  ደግሞ ለህውሀት መመለስ በር እየከፈቱ ነው::የኦሮሞ አክቲቪስቶችን 24 ሰአታት ስማቸውን ብናጠቁር ለውጥ የሚያመጣ ፋይዳ የለውም::አንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች አ ብ ንና ኦነግን በአላማም ይሁን ቅርፅ የማይመሳሰሉትን በአንድ ሙቀጫ ሲወቅጡ ማየት ትርፉ ከፍተኛ ትዝብት ነው:: አ ብን በምንም መልኩ ከአዴፓ ጋር አብሮ የአማራውን ጥቅም ከማራመድ ውጪ ለሌሎች መጠቀሚያ ሆኖ ወደ ግጭት እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻዋል:: አማራ ከተደራጀ ሌሎችን በመረጃ በሞመገት ማሸነፍም ይችላል:: በጉልበትም የሚገዳደር ሀይል ይኖረዋል:: ጃዋርና ጏደኞቹ ደፍረውም ተንኮል አያስቡም:: ዘመናዊ ፖለቲክኞች ናቸው:: አቅማቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ::በዚህ ወቅት አማራ ለፖለቲካ ጫወታ የቅንጦት ዘመን ላይ አይደለም::አማራው ድህንነቱን ለማስጠበቅ በአማራነት መደራጀት ገንቢ ስራ ነው:: የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ትንኮሳን በሚቻለው ሁሉ ለማርገብ ሞክሩ:: ባለፉት 27 አመታት ለህውሀት ስልጣን ላይ ለመቆየት ትልቁ ስራ የኦሮሞንና አማራን ህዝብ ለያይቶ በመግዛት ረጅም እድሜን አስቆጥረዋል:: ዛሬም አልተኙም የእነሱ ዲጂታል ወያኔዎች ሰፊ ስራ እየሰሩ ነው::እጅግ ብዙ ሚሊዮን አማራ ከኦሮሞ ጋር ተቀላቅሎ በኦሮሚያ ይኖራል:: አብን ከዚህ ህዝብ ጋር ጤናማ ግኑኝነትን መፍጠር ይገባዋል:: ህውሀት በሚከፈተው ቀዳዳ ሁሉ እጃቸውን በማስገባት አ ብን ከኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ለማቃረን የማፈነቅሉት ድንጋይ የለም:: ለምሳሌ የርእዮት ጋዜጠኛ ለ አብን ድጋፍ ማሳያ ለአብን አላማ ተቆርቋሪነት ሳይሆን በኦሮሞ ላይ አብንን ለማዘመት የሚያራምደው የተንኮል ስራ ነው::የአማራ ፀጋ አስተዋይነትና ትእግስት ስለሆነ ነገሮችን በሰከነና በመረጃ የታጀበ መንገድ እንደምታስተናግዱ ተስፋ አለኝ:: በሚደረገው የህዝብ ቆጠራ ላይ ያወጣችሁት መግለጫ የሚደነቅ ነው::አብ ን በሚቻለው ሁሉ ከአዴፓ ጋር የጋራ አጀንዳ በመቅረፅ ለአማራ ህዝብ አገልጋይነቱን በተግባር ማሳየት ወቅቱ የሚጠይቀውም ክስተት ነው::በርቱ!379