February 19, 2019

ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2011 ዓ.ም(አብመድ) በጎንደር ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰባቸውን አስታውቀዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ከ90 ሺህ በላይ መድረሳቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። ድጋፍ ለማድረግም ጥሪ አቅርቧል።

ከተፈናቀሉት ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞን በተፈጠረው ግጭት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱት ናቸው።

የጎንደር ከተማ ባለሀብቶችም የክልሉን መንግሥት ጥሪ ተከትለው የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው። ወገኖች ወደቀደመ መኖሪያ ቦታቸው ተመልሰው ኑሯቸውን እንዲመሩ ለማድረግ ትናንት ምሽት በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር አካሂደዋል፡፡

1 ሚሊዮን 412 ሺህ ብር መሰብሰባቸውም ታውቋል። በገቢ ማሰባሰቢያው 25 የሚሆኑ ባለሀብቶች እንደተሳተፉ ነው የተገለፀው፡፡ ሁሉን አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር ለማካሄድም ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ የኮሚቴው ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ሰጥአድርገው እንደተናገሩት ባለሀብቶች ከ20 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ለተፈናቀሉ ዜጎች አበርክተዋል፡፡

የካቲት 17/2011 ዓ.ም ደግሞ ተቆርቋሪ ግለሰቦች የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ጥሪ ተከትሎ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) 25 ሚሊዮን ብር፣ ጥረት ኮርፖሬት ደግሞ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል። የደብረ ታቦር ፖሊ ቴክኒክ ሠራተኞችም ከየካቲት ወር ደመወዛቸው 10 በመቶውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ከማዕከላዊ እና ከምዕራብ ጎንደር ዞን 53ሺህ 402 ግለሰቦች በጊዜያዊ ግጭት ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተፈናቀሉ ከክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ በአማራ ክልል በአጠቃላይ ደግሞ 90ሺህ 736 ተፈናቃኞች በ13 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ ብሏል ጽሕፈት ቤቱ፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ