February 20, 2019t

እንደሚታወቀው ኦዴፓ የስልጣን መንበሩን ለመቆጣጠር ባቆበቆበበት ወቅት ደጋፊ ይፈልግ ነበርና በዚህም በዚያም ብሎ የአዴፓን ድጋፍ አገኘ። ኦዴፓ ይህንን የአዴፓን ድጋፍ የፈለገው በህወሃት ሰዎች ተይዞ የነበረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ የበላይነት ለሞቆጣጠር አስቦ እንደነበር ለመረዳት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎችን በማየት መረዳት ይቻላል።
ኦዴፓ አሁን ስልጣኑን ከሞላ ጎደል እያደላደለ ስለመጣ የአዴፓ ድጋፍ አያስፈልገኝም እያለ ይመስላል። ምክንያቱም ድሮውንም ቢሆን የኦዴፓና የአዴፓ ወዳጅነት ታክቲካዊ (Tactical) እንጅ ስትራቴጂካዊ (Strategical) አልነበረምና። በነዚህ ሁለት ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት ታክቲካዊ እንጅ ስትራቴጅካዊ የማይሆንበትን ሁኔታ ሶስት ዋና ዋና የሆኑ ምክንያቶችን በመጥቀስ ብቻ መረዳት ይቻላል።
በመጀመሪያ ደረጃ ኦዴፓ ውስጥ የተሰባሰቡት አብዛኛዎቹ አመራሮች በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝም አቀንቃኞች ናቸው። በተቃራኒው አዴፓ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ አመራሮች ደግሞ አህዳዊ የሚል ስሜት የሚንፀባረቅባቸው ናቸው። ሁለተኛ ኦዴፓዎች በህገመንግስቱ ላይ ከሞላ ጎደል እምነት አላቸው። አዴፓዎች ግን ህገመንግስቱ እኔን አይወክልም በሚል የማህበረሰብ ክፍል ጫና ምክንያት በህገመንግስቱ ላይ የተሟላ እምነት አላቸው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ሶስተኛ ብዙዎቹ ኦዴፓዎች ሲሻቸው አማራ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአማራ ገዥ መደብ ለረጅም ጊዜ ሲጨቁነን ኖሯል የሚል ያደረ ቂም እንዳላቸው መረዳት ይቻላል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአዴፓ ሰዎች በበኩላቸው ኦዴፓ በአዲስ አበባና በኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋነት ጉዳይ ላይ ባለው አቋም ብዥታ ውስጥ የገቡ የሚመስሉበት ሁኔታ መኖሩ ነው።
ይህን የሁለቱን ድርጅቶች ግንኙነት ስትራቴጅካዊ አለመሆን የሚያጎላው ደግሞ ሁለቱም ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች ያሉት የፖለቲካ አቀንቃኞችም ይሁኑ ሌሎች አካላት ያላቸው እሰጥ አገባ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ ያሉት ሃይሎች አማራ ሲጨቁነን ኖሯልና እንዲህ በቀላሉ ይቅር የምንልበት አንጀት የለንም ይላሉ። በዚህም ምክንያት የአፄ ሚኒሊክንና በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎችን ሃውልት ማየት አንፈልግም በሚል ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። በአማርኛ የሚጠሩ የቦታ ስሞችም በክክልላችን እንዲኖሩ አንሻም ብለውም አምርረው ድምፃቸውን ያሰማሉ። እስካሁን የተቀየሩ ብዙ የቦታ ስሞችም አሉ።
አዴፓ በዋነኛነት በሚንቀሳቀስበት አማራ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ሃይሎች ደግሞ ኦዴፓ የበላይነቱን ለማንገስ እየሰራ ስለሆነ ህዝባችን በእኩልነት ላይጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል ብለው ይሰጋሉ። ምናልባትም አማራ ክልል ውስጥ ያለውን የኦሮሚያ ልዩ ዞን በመጠቀም ግዛታችን አልፈው ለመምጣት ሊሞክሩ ይችላሉ ብለውም ጥርጣሬያቸውን ያጋራሉ። በአዲስ አበባ የባለቤትነትና በኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን የሚሉ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ጉዳይ ላይም ጎራ ለይተው እሰጥ አገባ የገቡ መሆኑን እያየን ነው።
በዚህ ሂደት ኦዴፓ እቅዶቹንና አላማዎቹን ለማሳካት በሚገባ በተጠናና በተደራጀ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ለዚህም አዴፓን በፈለገው መንገድ የተጠቀመበትና አሁንም እየተጠቀመበት ያለ ሲሆን አዴፓ በበኩሉ መያዣ መጨበጫው ጠፍቶበት ተበትኖ ያለ ፓርቲ ሆኗል። እንዲያውም ብዙዎቹ የሚያምኑት አዴፓ ልክ በብአዴን ስም የህወሃት አገልጋይ እንደነበረ ሁሉ አሁን ደግሞ ለኦህዴድ አጋፋሪና አጃቢ እንደሆነ አድርገው ነው። አዴፓ እንደፓርቲ ያለው ግምገማ ግን ከዚህ እውነታ ተቃራኒ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት አዴፓ የሚያምነው በሃገሪቱ ውስጥ መጣ ለተባለው ለውጥ ከኦዴፓ ጋ እኩል ድርሻ እንዳለውና አሁንም ለውጡን በማስቀጠል ረገድ ከኦዴፓ ጋ መሳ ለመሳ ሆኖ ሚናውን እየተወጣ እንዳለ ነው። በዚህም አለ በዚያ ግን አዴፖ የወቅቱን የሃገሪቱን ፖለቲካ ተንትኖና ሰፋ አድርጎ ብልህነት በተሞላበት መንገድ የተረዳው አይመስልም። ለመረዳት ፍላጎት የለውም ብቻ ሳይሆን አቅም እንደሌለውም ከሚያደርጋቸው እሰጥ አገባዎች መረዳት ይቻላል። አዴፓ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የአማራውን ህዝብ ተገቢ ጥቅም (Legitimate Interest) ሊያስጠብቅ ይቅርና የራሱን ህልውናም ሊታደግ የሚችል ፓርቲ አይሆንም። በመሆኑም ይህን የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥቅም የሚተነትን፣ የሚያቅድና የሚያስፈፅም ብቃት ያለው ግን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፓርቲ የማጎልበት ወይም የመፍጠር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የአማራ ሙህራንና የፖለቲካ ልሂቃን በደንብ ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
የኦዴፓና የአዴፓ ግንኝኙነት ከላይ በተገለፀው መልኩ ታክቲካዊ/ጊዚያዊ ነው ከተባለ የኦዴፓና የህወሓት ግንኑነት ስትራቴጅካዊ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው የሚለውን ደግሞ ከዚህ በታች ለማብራራት ይሞከራል። በእርግጥ በህወሃት ሰዎች ይፈፀም የነበረ ግፍና በደል ስፍር ቁጥር ያልነበረው በመሆኑ የኦዴፓን ሰዎች ለትግል አነሳስቷል። በዚህ ወቅት ወትሮውንም ቢሆን ለህወሃት የመረረ ጥላቻ የነበራቸው ብዙዎቹ የአዴፓ አመራሮች ከኦዴፓ ጎን በመሰለፍ ለህወሃት ሰዎች መንኮታኮት ታላቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህን የተረዱት ኦዴፓዎች ደግሞ በቀላሉ ስልጣን ሊጨብጡ ይችሉ ዘንድ የአዴፓን አመራሮች በበለጠ ወደነሱ ቡድን እንዲሳቡ አድርገዋቸዋል። ለዚህ እቅዳቸው መሳካት የተጠቀሙበት ዋነኛው ዘዴ አማራ ክልልን መጎብኘት ነበር። መጎብኘት ብቻም ሳይሆን ስለኢትዮጵያዊነት ከፍታ እንዲሁም ስለኢትዮጵያ ሱስነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሰብከዋል።
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ታላቅ ቁምነገር ግን ኦዴፓ በጊዚያዊነት ከአዴፓ ጋ ቡድን ፈጥሮ የተንቀሳቀሰው ከህወሃት ጋ መሰረታዊ የአላማና የአደረጃጀት ልዩነት ኖሮት ሳይሆን ስልጣንን ከህወሃት ሰዎች ነጥቆ የራሱ ለማድርግ ካለው የጠለቀ ፍላጎት ተነስቶ ነው። ይህን መሰረታዊ የሆነ በህወሓትና በኦዴፓ መካከል ያለ ስትራቴጅካዊ ግንኙነት ለመረዳት የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በደንብ ማጤን ብቻ ይበቃል።
አንደኛው ነጥብ ህወሃትም ሆነ ኦዴፓ በአማራ ገዥ መደብ ተጨቁነናል የሚል ጠንካራ የሆነ አቋም አላቸው። ሁለቱም ይህን ጭቆና ለማስወገድ ዋጋ ከፍለናል ይላሉ። የኦዴፓም ሆነ የህወሓት ሰዎች የአፄ ሚኒልክን አስተዳደር እንደወራሪና ቅኝ ገዥ እንጅ እንደ አገር ባለውለታ አያዩትም። በዚህም ምክንያት በሚኒልክ አስተዳደር ላይ ያላቸው ስር የሰደደ ጥላቻ አሁን ድረስ የሚታይ ነው። ይህ አስተሳሰብ በሁለቱ ድርጅቶች ሰዎች ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው ባሉ ሁሉ ይቀነቀናል።
ሁለተኛ ኦዴፓም ይሁን ህወሓት በህገመንግስቱ ላይ ፅኑ እመንት አላቸው። ሁለቱም ድርጅቶች ህገመንግስቱ የትግላቸው ውጤትና ዘላቂ ጥቅማቸውን ሊያስከብር የሚችል መሳሪያ ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሁለት ድርጅቶ የመገንጠልን መብት ጨምሮ ብሄራዊ ጥቅማችንን ልናሟላበት የምንችል ትልቅ መሳሪያ ቢኖር ህገመንግስቱ ነው የሚል የማያወላውል አቋም አላቸው።
በሶስተኛ ደረጃ ሁለቱም ድርጅቶች የኢትዮጵያ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በፌዴራሊዝም ስርዓተ- መንግስት ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሁለት ድርጅቶች የሚያምኑበት የፌዴራሊዝም አይነት ደግሞ መልክዓ ምድራዊ ሳይሆን በማንነት የተመሰረተው ፌዴራልዝም ነው። በሁለቱም ድርጅቶች ከዚህ አይነቱ የፌዴራል ስርዓተ-መንግስት ነቅነቅ ማለት የሃገር ህልውናን እንደማናጋት ተደርጎ ይቆጠራል። ለዚህም ነው ሰሞኑን ኦዴፓም ሆነ ህወሓት በፌዴራሊዝም ስርዓተ–መንግስት ላይ አንደራደርም የሚል ጠንካራ መግለጫ እየሰጡ ያሉት።
ይህ በህወሓትና በኦዴፓ መካከል ያለ ስትራቴጅካዊ ግንኙነት በደጋፊዎችም ሆነ በሌሎች አካላት በተለያዩ መድረኮች ጎላ ብሎ በመገለፅ ላይ ይገኛል። ለምሳሌ እነዚህ ሃይሎች ሁለቱም ድርጅቶች በማንነት ላይ የተመሰረት የፌዴራል ስርዓተ-መንግስት አቀንቃኞች መሆናቸውን በመግለፅ በዘላቂነት አብረው ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ። ይህን ጠንካራ የሆነ አቋም ለመረዳት ለአጭር ጊዜም ቢሆን የማህበራዊ ትስስር መድረኮችን መከታተል በቂ ሊሆን ይችላል።
ከላይ የተገለፁት አጠቃላይ ሁኔታዎች ሲቃኙ መረዳት የሚቻለው የአዴፓ (ብአዴን) እና የኦዴፓ (ኦህዴድ) ግንኙነት ታክቲካዊ/ጊዚያዊ ሲሆን በህወሓትና በኦዴፓ (ኦህዴድ) መካከል ያለው ግንኙነት ግን ስትራቴጅካዊ/ዘለቄታዊ መሆኑን ነው። በመሆኑም ኦዴፓና ሀወሓት አዴፓን በማግለል ተመልሰው የሚገጥሙበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም።
