የለገጣፎ ለገዳዲ ነዋሪዎች በግፍ የመፈናቀል ዕጣ ለአዲስ አበባ ሕዝብ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ በዚህ ፍጥነት ይሆናል ብየ ግን ፈጽሞ አልገመትኩም ነበር፡፡ ወገኖቸ ይሄ አሸባሪ አገዛዝ ምስቅልቅልህን ለማውጣት ቆርጦ ተነሥቷል፡፡

የማፈናቀያ ስልቱ የአዲስ አበባ ወንዞችን ዳርቻ የማልማት ፕሮጀክት!” ተብሎ ተሠይሟል፡፡ ፕሮጀክቱ (የሥራ አቅዱ) ሆን ተብሎ ሕዝብ ለማፈናቀል የታቀደ ስልት እንደሆነ የሚያረጋግጡ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ልጥቀስ፦

1. ወንዞቹ ክረምት ብቻ የጎርፍ ውኃ የሚኖራቸው መሆናቸውና በጋ ላይ ግን ደርቀው ለከተማዋ ነዋሪ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሆነው የሚያገለግሉ በመሆናቸው ሲሆን፡፡

2. በገንዘብ እጥረት ምክንያት በርካታ አንገብጋቢ የመንግሥት ፕሮጀክቶችበታጠፉበትና በተቋረጡበት በአሁኑ ወቅት የደረቅ ወንዞችን ዳርቻ በ29 ቢሊዮን (ብልፍ) ብር በ3 ዓመታት ውስጥ አልምቶ ለመናፈሻ አገልግሎት ማብቃቱ አንገብጋቢነቱ ፈጽሞ የማይመስልና የማያሳምን በመሆኑ ነው፡፡

አገዛዙ ይሄንን ፕሮጀክት እንዴትና ለምን እንዳቀደ ሲገልጽ ያደጉ ሀገሮችን ከተሞች በማንሣት በከተማዎቹ መሀል እየፈሰሱ በመዝናኛነት የሚያገለግሉትን ወንዞች በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡

ነገሩን ፈጽሞ የሚይመስል የሚያደርገውም ይሄው ነው፡፡ ምክንያቱም የእነኝህ ያደጉ ሀገራት ከተሞች በመሀል የሚፈሱ ወንዞች ሊኖራቸው የቻለው አንደኛው ምክንያት የእነሱ የክረምት ወቅት ከዓመቱ የሚበዛው ጊዜ የሚይዝ በመሆኑና በበጋውም ከከፍታ ቦታዎች ላይ በክረምት ወቅት የተጋገረው በረዶ እየቀለጠ ስለሚፈስባቸው ወንዞቹን ክረምት ከበጋ ውኃ የማይጠፋባቸው ስለሆኑ ሲሆን፡፡

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከተሞቹ ከውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ያሉ ወይም የተቆረቆሩ ስለሆኑና በከተሞቹ የመሬት አቀማመጥ ምክንያት የውቅያኖሱ የውኃ ክፍል እንደወንዝ እየሆነ በከተሞቹ መሀል የመተኛትና ለመዝናኛነት የመገልገል ዕድል ስለሰጣቸው ነው፡፡

አሁን ጥያቄው የእኛ ወንዞች ይሄ ዕድል አላቸው ወይ???” ማለትም ከዓመት እስከ ዓመት በውኃ የመሞላት ዕድል አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ብለን የጠየቅን እንደሆን ሁላቹህም የምታውቁት ነው እነኝህ ወንዞች ውኃ የሚኖራቸው በክረምት ወራት ነው፡፡ እሱም ዝናብ ሲዘንብ ተንደርድሮ የሚያልፍ ጎርፍ እንጅ እንደምዕራባውያኑ የከተማ ወንዞች ውኃ የሚተኛባቸው ወይም ተሰስ ብሎ የሚፈስባቸው ወንዞች አይደሉም፡፡ በበጋ ደግሞ ደረቅ ናቸው፡፡ በበጋ ውኃ አለባቸው ከተባለም ከየቤቱ የሚወጣው የፍሳሽ ቆሻሻ እንጅ የወንዝ ውኃ አይደለም፡፡

ፕሮጀክቱን የውሸትና ሕዝብን የማፈናቀያ ሰበብ መሆኑን የሚያጋልጠውም ይሄው ወንዞቹ በረጅሙ የበጋ ወቅታችን ውኃ አልባና በክረምትም ቢሆን በዝናብ ወቅት ብቻ የጎርፍ ውኃ ተወርውሮ የሚያልፍባቸው እንጅ እንደ የምዕራብ ከተሞች ወንዞች ውኃ የሚተኛባቸው አለመሆናቸው ነው፡፡

እንግዲህ በእነኝህ ሰባት ወንዞች ግራና ቀኝ ያለህ የአዲስ አበባ ሕዝብ በተለይም ፕሮጀግቱ በቅድሚያ ይሠራባቸዋል በተባሉት ሁለት ወንዞች ግራና ቀኝ 50 ..(ጉነ ጉዝ) ስፋት ያለህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ፕሮጀክቱ (የሥራው አቅድ) በሦስት ዓመት ይጠናቀቃል በመባሉ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተመንጥረህ ትወገዳለህ፡፡

ለልማት!” እያለ ስንቱን መንደር ነው አፈራርሶት የሙጃ መብቀያ አድርጎት የቀረው??? አሁንም አፈራርሶልህ ካጸዳህ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የታለ የለማው?” ብትል ማን ይሰማሃል??? ምንስ ታመጣለህ??? ለምደኸው የለም ወይ???ነው ወይስ አገዛዙ እንደ ቀንደኛ ጠላት የሚያየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለዚህ በልማት ስም ለመጣበት የማፈናቀልና የማጽዳት ዘመቻ እጅ ሰጥቶ ይፈናቀልለታል ወይስ ሊሆን የማይችል ሐሰተኛ የማፈናቀያ ስልት መሆኑን አውቆ ለመብቱ በመቆም ይተናነቃል??? በመጭዎቹ ሳምንታት የምናየው ይሆናል!!!

እጅግ ያሳዝናል!!! ወይ ሕዝቡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ፈጽሞ የማይምረው ጠላቱና የማይድን የማይፈወስ አካይስት መሆኑን ተረድቶ ቆርጦ በመነሣት መክፈል ያለበትን ዋጋ ከፍሎ እራሱን ነጻ አላወጣ ወይ ደግሞ ወያኔ/ኢሕአዴግ ከፀረ ሕዝብነቱ የሚለወጥ የሚፈውስ ሆኖ አይፈወስ ነገር የዚህች ሀገርና የዚህ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ እያደር ከድጡ ወደማጡ እየሆነ መጥቶ አረፈው፡፡

እንግዲህ አውቄ ልጃጃል ካልክ ይበልሃ ሌላ ምን ልልህ እችላለሁ ምድረ በድን??? ተረቱስ የሚለው ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ!” አይደል እንዴ??? እና ይበልሃ!!!

አምሳሉ