
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ጀምሬያለሁ አለ፡፡አለም የደረሰበትን የፌደራል ፖሊስ አሰራርንም ለመከተል ጥናቱን እንደጀመረው ሰምተናል፡፡በለውጡ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት አሰፋፈርና አደረጃጀት 4 ክላስተሮች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተማ ልዩ የፌደራል ፖሊስ ሀይልና የፌደራል ፖሊስ የአየር ሀይል ክንፍ እንደሚደራጅ ሰምተናል፡፡
ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና ድሮኖችን በመጠቀም የቅድሚያ ወንጀል መከላከል ስራዬንም በለውጡ አካትቼዋለሁ ብሏል፡፡ሥነ-ምግባሩን የጠበቀ፣ ሀላፊነት የሚሰማው፣ ሕዝቡን የሚያስቀድም ሰራዊትም ለማደራጀት በለውጥ ስራው እመለከተዋለሁ ማለቱን የፌደራል ፖሊስ ለሸገር ተናግሯል፡፡ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ፀጥታውንም ለመጠበቅ በአየር የታገዘ አሰራር ለማቋቋም መታሰቡንም ሰምተናል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ሃይልና በአየር የታገዘ የፖሊስ ቡድን እስከ ማቋቋም የደረሰ የአደረጃጀት ማስተካከያ አደረገ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሸው ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የኮሚሸኑ ተቋማዊ ሪፎርም ሂደት እና የደረሰበትን ደረጃ አብራርተዋል።
የሰው ሃይል፣ ቴክኖለጂ፣ ስልጠና፣ ሎጅስቲክስ እና ከባለደርሻ አካላት ጋር የሚኖር ግንኙነት ላይ መሰረት ያደረገው ሪፎርም በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በረፎርሙ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት አሰፋፈር እና አደረጃጀት መከለሱን እንዲሁም በአራት አቅጣጫ በአራት ክላስትሮች እንዲከፋፈል መደረጉን ነው የገለፁት። ክላስተሮቹም፥ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምእራብ እና ማእከላዊ ክላስተር ናቸው።
በሪፎርሙ መሰረት የከተማ ልዩ የፌደራል ፖሊስ ሃይል እና በአየር የታገዘ ክትትል ለማድረግም የፌራል ፖሊስ የአየር ሃይል ክንፍ ( AIR WING ) ይደራጃልም ብለዋል ኮምሽነር ጀነራሉ።
የጦር መሳሪያ ትጥቅን በተመለከተም የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና ልዩ ሃይል እንዲሁም ሚሊሻዎች ምን አይነት መሳሪያ ሊታጠቁ ይገባል የሚለውን የሚመልስ አዋጅ በመዘጋጀት ላይም ነው።
የሪፎርሙ አካል የሆነ የምርመራ ስርዓትን በሚመለከትም የምርመራ ማንዋል ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ትግባራ እንደሚገባ ተነግሯል።
ፌዴራል ፖሊስ ከአሁን ቀደም ከምርመራ ጋር የተያያዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ካሜራ የተገጠመላቸው፣ በመስታወት የተከለሉ፣ ሶስተኛ ወገን ምርመራውን መከታተል የሚችልባቸው የምርመራ ክፍሎች መዘጋጀታቸውም በመግለጫው ተነስቷል።
