February 23, 2019 t
ታህሳስ 16 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 5/ 2011 ጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በ1 ድምጸ ተዓቅቦ በ1 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
የኮሚሽኑ ዓላማም በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ ብሄራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም እርቅ እንዲሰፍን መስራት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡
ኮሚሽኑ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-
1/ ስራዉን በሚመለከት ማንኛዉም ያገባኛል የሚል ሰው ወይም አካል ሃሳቡን እንዲያቀርብ ጥሪ ማቅረብ እና አስፈላጊውን ምዝገባ ማካሄድ፤
2/ ስራዉን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ተደራሽ፣ አሳታፊ፣ ሁሉም አካል እኩል ተደማጭ የሚሆንበት የዕርቀ-ሰላም ውይይት መድረክ ማዘጋጀት፤
3/ የተለያየ ዐቋም የያዙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየትና ለሃገራዊ እርቅ መሰረት የሚሆኑ የጋራ መርህዎችንና እሴቶችን መለየት፤
4/ የግጭቶችንና የመብት ጥሰቶቹን መነሻ ምክንያት ለመለየት፣ፖለቲካዊ: ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውዶችን፣ የተጎጂዎችንና ጥፋተኞቸን አስተያየት በመወሰድ የማጣራት ስራ ማካሄድ፤
5/ ለሰራው አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን ለአገር ደህንነት ሲባል በሚስጥር እንዲጠበቁ በህግ ጥበቃ ከተደረገላቸው መረጃዎች ውጭ ማንኛዉንም የሰነድ ወይም ሌላ መረጃ ከመንግስትም ይሁን ከማናቸውም ሌላ አካላት የመቀበልና በፈለገው ጊዜ እንዲያቀርቡ የማዘዝ፤
6/ ሀላፊነቱን ለመወጣት የማናቸውንም ተቋም ይዞታ የመጎብኘት፣ በጉብኝቱም ጊዜ የሚያገኛቸውን ማናቸውንም መረጃዎችና፣ ሰነዶችን ቅጂ የመውስድ፤
7/ መረጃ ለመሰብሰብ በተናጠልም ሆነ በቡድን፣ በሚስጥርም ሆነ ለህዝብ ክፍት በሆነ ሁኔታ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ መጥሪያ በመላክ ማንኛዉም ሰው እንዲቀርብ የማዘዝ እና ቃሉን በቃለ መሃላ እንዲሰጥ የማድረግ፤
8/ ሃላፊነቱን ለመወጣት እንደ ሁኔታው የፌደራልም ሆነ የክልል ፖሊስ እገዛ የማግኘት፤
9/ በማጣራት የሚደርስባቸውን መደምደሚያዎች እንደ ሁኔታው በየጊዜው ለህዘብና ለሚመለክታቸው የመንግስት አካላት ማሳወቅ፤እና
10/ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ልዩነት እንዲረግብ እና መግባባት እንዲፈጠር እርቀ ሰላም እንዲወርድ የማድረግ።
ሪፖርተር፡- ዳዊት በጋሻው/EBC
