February 23, 2019t

ሁሉም ተናጋሪን ይወዳል፣ አርዝሞ ለሚናገረው ደግሞ ይጨበጨባል፣ ስሜትን የሚኮረኩር ሰው ደግሞ እትከሻ ላይ ታቅፎ እሽክም፣ እሽክም ይባልለታል። አንድ የናይጄርያ ወጣት “politics is not mathematics but mouth” ያለው አስገርሞኛል። መቼ ይሆን ከእንዲህ ዓይነቱ አባዜ የምንገላገለው? በእርግጥ ሰውም አይፈረድበትም፣ ድብቅ ፍላጎትና (hidden intention) የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ (wolve in sheep’s clothing) ስውር ናቸው። የቋንቋ ፌደራሊዝም፣ የተማከላ አስተዳደር፣ ያልተማከለ አስተዳደር፣ የዜግነት ፖለቲካ፣ ልዩ ጥቅም፣ የሞግዚት አስተዳደር፣ አውቶኖሚ፣ እስከ መገንጠል፣ ኅብረ ብሄራዊ ፊደራሊዝም፣ የዘርና የቋንቋ አደረጃጀት፣ ማስተር ፕላን፣ የሕዝቦች መብት፣ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ወዘተ፣ ለሃያሳባት ዓመታት የሰማናቸው የሌብነትና ዝርፊያ አቅጣጫ ጠቋሚ ስሜትን ኮርኳሪ አፍዛዥ ቃላት ናቸው። እነዚህ ቃላት ከሃገሪቱ ጋር የተቆራኙ የፖለቲካ ጽንሠ ሃሳብ ወይም የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ መመርመርያ ሳይንስም አይደሉም – ወደ ስልጣን መውጫ ጥቁር መሰላሎች እንጂ።
ኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ሕወሓት በቋንቋ ፌደራሊዝሙ ላይ አንዳች ድርደር እንደማያደርጉ በማሳሰብ ከሰሞኑ መግለጫ እንደ ሰጡ አንድ ጓደኛዬ ነገረኝ። ሁለቱም ድርጅቶች በሥልጣን ጥያቄ ላይ እንጂ በዕምነት አንድ መሆናቸውን መናገራቸው ይሆን ወይስ አንዱ አንዱን ሊበላ ያቀደበት “ስውር ታክቲክ“? እኔ አልገባኝም። አንድ ነገር ግን መጠርጠር ይቻላል። ሕወሓትስ ግድ የለም፣ መቀሌ ተቀምጣ ያሻችውን ትበል። ኦዴፓ ግን ይህን ካለ – ፖለቲካው ለበታች ካድሬዎቻቸው በተለመደው የጨረታና ፕሮፎርማ” ስልት አሁንም ዝርፊያን እንዲያከናውኑ ለመፍቀድ ይሆን? ካድሬዎቻቸው የዚህ የፖለቲካ ዕምነት “ልዩ ተጠቃሚ” ከሆኑ ሕዝቡን ያፍኑላቸዋል። የበላይ አካላት ይህ ሁኔታ ሲስተካከልላቸው ነው – ዱባይና አሜሪካ ቤት የሚሰሩት፣ እውጭ ባንክ ቤቶች ገንዘብ የሚያጠራቅሙት፣ ልጆቻቸውን አሜሪካና አውሮፓ የሚያስተምሩት።
የሚያሳዝነው የአማራ ሕዝብ ነው። ሳይወድ በግድ ወደ ትግራይ እንዲደባለቅ የተደረገው የራያና የወልቃይጥ ጠገዴ ሕዝብ፣ ሳይወድ በግድ ወደ ኦሮምያ ክልል የተደባለቀው የሸዋ ምድር ነዋሪ፣ ከቤንሻንጉልና ጉሙዝ ጋምቤላ ክልል ውጣ የሚባለው የጎጃም ተወላጅ እጅግ አሳዛኝ ነው። የቋንቋ ፌደራሊዝም የሸዋን፣ ወሎን፣ በጌምድርንና ጎጃም አማራን ባይተዋር ያደረገ ጎጂ የበቀል ፖለቲካ ነው። ይህ ግፍ አማራን ለመጉዳትና ለማምከን መለስና ስብሃት ደደቢት ላይ ጸንሰው፣ እዛው ደደቢት ላይ አምጠው፣ እዛው ደደቢት ላይ የወለዱት ጠመዝማዛ እባብ ነው። አማራው ሶስት አስርት ዓመታትን ሊያስቆጥር ትንሽ በቀረው የፍዳ ዘመናት፣ ሃገሬ ነች ብሉ ከተሰማራበት አካባቢ የሚፈናቀለውና ውጣ እየተባለ የሚገፋው በሌዋታኑ የነመለስ መንፈስ እገዛ ነው። ሌላው ቀርቶ ከተሞች ናቸው በሚባሉት ደብረዘይት፣ ናዝሬት፣ ሻሸመኔ፣ ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ወዘተ፣ የሚኖሩ አማሮች እንኳን በተወለዱበትና ባደጉበት ቀዬ እንደ ባይተዋር እየተቆጠሩ ማመልከቻዎቸውን ወደ ኦሮምኛ ለመለወጥና በአስተዳደርና ፍርድ ቤቶች ሃሳባቸውን ለመግለጽ ለተርጓሚና ጠበቃ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመድቡና እንዲደኸዩ የተደረገው የበቀል መንፈሱ ያረፈባቸው እጅግ ጥቂት ካድሬዎች እፎይታ እንዲያገኙ ነው። የኦሮም ሕዝብ የዚህ ዓይነት ጭካኔን የማያውቅ ደግና ርህሩኅ ሕዝብ ነው። አየር ምድሩ በሌዋታን መንፈስ ተበከለ እንጂ ኦሮሞው ከአማራው ጋር እጅግ የተሳሰረ ሕዝብ ነው።
አድዋ ላይ የተዋጋው ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጣው ሕዝብ ሆኖ ሳለ በጀግናው ሚኒሊክ ዘር ሳብያ የፈረደበት አማራ በቅኝ ገዥዎችም እምብዛም አይወደድም። የምዕራቡን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል “አማራውን ከእንግዲህ ወደ ሥልጣን እንዳይመጣ እናደርጋለን” በሚል ልዩ ሸፍጥ ጊዜአዊ ድጋፍ ለማግኘት የሚጥሩ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆን ራሳቸውን ይጎዳሉ እንጂ ምድር ከእንዝርቷ እንደማትዛነፍ ሁሉ እውነትም ቦታዋን አትለቅም። ውሸት ወደ ሥልጣኑ ወንበር ብታመራም – ሃቅ ግን ውላ አድራ አለአግባብ ወደ ወንበሩ የመጣውን ባሥልጣንን ትፈነግላለች።
ፖለቲካ አደገኛ ሳይኮሎጂ ነች። ላንድ ሰሞን የሠይጣኑ ኮከብ የሌለበትን ከእግዚአብሄር የተበረከተውን ባንዲራ መያዝ ፈቅዳ ስሜትን አብርዳለች። ዛሬስ – ይህችን ባንዲራ መያዝ በፀረ–አንቀጽ 39 እና በቋንቋው ፌደራሊዝም ጠላትነት ያስፈርጅ ይሆን? ፖለቲካ ጩኸትንም ታስታግሳለች። በከፍተኛ ሙስና የሚፈለጉ በርካታ ርኅራሄ ቢስ የጨረታ ምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እንዲሁም በሃገሪቱና ደሃው ገንዘብ በዱባይና አሜሪካ ሠፋፊ መሬቶችን የገዙ ግፈኞች እያሉ አንድ ሁለት ፊት ለፊት የተገኙ ወንጀለኞች ብቻ መርጦ እፍርድ ቤት ማመላለሷ ጩኸትን አቅባ ሙስና ለማዳን ይሆን? ፖለቲካ የሕመም ስሜት ማስታገሻም ነች። የታሰሩትን አውራ ባለሥልጣናት ነገ ትለቃቸው ይሆን? ምን ይታወቃል – ፍርድ ቤቱ “ከልጅነታቸው ጀምሮ በረሃ ገብተው ለቋንቋው ፌደራሊዝም የታገሉት ሚዛን ላይ ተካቶ በምህረት ለቋቸዋል” ይል ይሆናል። ሌሎች መቀሌ መሽገው አንድ ሁለቱ ብቻ ምን ፈረደባቸው? ምናልባት ለሌሎቹ ወንጀለኞች የሚሰዉ የመስዋዕት እባብ ሆነው ነው?
በአዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ደብረዘይት፣ ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ሻሸመኔ፣ ወዘተ፣ የሚኖረው አማራ ስውር ደባ ተፈጽሞበታል። አማራው በደርግ ፀረ–ፊውዳሊዝም ትግል ሳብያና ወያኔ ባመጣው የዘር ጥላቻ ምክንያት በገፍ ተሰዷል። የትም ብትሄዱ፣ የቱንም ሠፈር ብትቃኙ ያማራ ልጆች ቁጥር መቀነሱ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት በሠፈራ ፖለቲካም ይሁን አዲስ መታወቅያ በመስጠት መላ የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር እንዲበዛ በወያኔ ትዕዛዝ ኦሕዴድ በብርቱ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ። ይህ የተደረገው ምርጫም ሆነ ሕዝባዊ ውሳኔ ቢደረግ አማራው ሃሳቡ እንዳይደመጥ ለማድረግ ነው። አዲስ አበባ ካካባቢዋ የመጡ ኦሮሞዎች እንዲሁም ናዝሬትና ሻሸመኔ ላይ ደግሞ ከአርሲ የመጡ ኦሮሞዎች እንዲሰፍሩ ማድረግን መለስ ካልሆነ ማን ፖለቲከኛ ያስበዋል? ደደቢት የተወለደው “የቋንቋ ፌደራሊዝም” ማለት በአጭሩ ይህን ዓይነቱን ግፍ መተግበርያ ፀረ–አማራ ሳይንስ ነው። እድሜ ለወያኔ አማርኛ ቋንቋን እንደ ጋፋትኛ ቋንቋ ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ፈጽሞ ባይሳካም እንኳን መስመሩን ይዟል። በረራ ኋላም አዲስ አበባ የተባለችውን የሸዋና ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደ ፊንፊኔ ለመቀየር የተካሄደው የሥነ–ልቦና ጦርነትም ከሞላ ጎደል ተሳክቷል። አዲስ አበባ – የሸዋ ዋና ከተማ – የአጼ ሚኒልክ አያት የንጉሥ ኃይለመለኮት አባት – የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ግዛት ነበረች ብሎ እንዳያወራ አማራውን አቅሙን ሠልበውታል። ከደርግ መምጣት ማግስት ጀምሮ በፖለቲካው ምክንያት የአያት ቅድም አያቶቹን አገር እየለቀቀ አሜሪካና አውሮፓ የተሰደደው አማራ ገና ድሮ ሳያውቅ ሃገሩን አሳልፎ ሠጠ። “ማሰደድ፣ ስደትና ስደተኛን መቀበል” የቅኛ ገዥዎች ስውር ፖለቲካ ነው።
በሃምሳ ዓመታት ውስጥ አንድ ትግራዋይ መቀሌና አዲስ አበባ ውስጥ ቤት እንዲኖረው የማድረጉ የመለስ ሕልም በቄሮ ትግል ተጨናግፏል። ዛሬ መለስ ፓርክ፣ መለስ ዜናዊ ስታዲዩም፣ መለስ ዜናዊ ጎዳና፣ መለስ ዜናዊ ቡቲክ የሉም። በድንጋይ እየተደበደቡ እንደ መለስ ተቀብረዋል። የቀሩ ምስሎች ቢኖሩ በወያኔዎቹ ኪስ የሚያዙ ትናንሽ ፎቶግራፎች ናቸው፣ እነሱም ፍርሃቱ ባመጣው ላብ ብዛት ደብዛቸው ጠፍቷል። ወያኔዎች ዛሬ መቀሌ መሽገው ጫት ይቅማሉ፣ በውስኪ ይነዳሉ። ሰማይ ቢያዩ ምድር ቢቃኙ አምላካቸው መለስ የለም። ይልቁንም መለስ በሌለበት – እነሱ በሌሉበት – በሱ መቃብር ላይ – መዲናይቱ አዲስ አበባ ላይ የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ሃውልት በግርማ ሞገስ ቆሟል። ከሁሉም ይልቅ ደፂ ሳይሻል አይቀርም። “አሮጌ መሳርያዎቻችንን እየወለወልን ነው” ብሎ አስፈራርቷል። ምናልባት ደፂ ይህን ያለው ብረት ይዞ በወፍራም ፈረስ ሲሄድ ያየውን ሕልም ይሆን። ደፂ – ሕልም እኮ ብዙ ጊዜ ተቃራኒ ነው።
ወያኔ አማራን አጠፋለሁ ብሎ የውድ ጀግናው ትግራይዋዎች አያት ቅድም አያት የተዋደቁላት ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመድፍ ደበደበ። ዛሬ በትግራይ ልጆችና በአማራው ልጆች መካከል የተጋረደው የኃጢዓት ግንብ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ እንዳትዘልቅ ትልቅ ግርዶሽ ሆነ። የአማራና፣ የኦሮሞ፣ የትግራ ልጆች የተስማሙ ዕለት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የታቀደው የግማሽ ምዕት አመቱ ደባ ይገረሰሳል። የቋንቋ ፌደራሊዝም፣ የተማከለ ያልተማከለ አስተዳደር የሚለው ልፍለፋ እስከነግሳንግሳቸው ሁሉም ከመለስ ጋር ይቀበራሉ። አፍራሽ ፖለቲካ ለተረትነትም አይበቃ። ሙዚየምም አይቀመጥ፣ በአውሬነት ይመሰላል እንጂ። ቀኑ ቅርብ ነው። መለስ የለም – ነገ እነ እገሌም የሉም። ማን እንደሆኑ ማንም አያስታውሳቸውም። ደደቢትን እንደ ጥልቅ ጉድጓድ ሁሉም ይፈራታል። ደደቢትን እንደ ሌዋታኑ የጨለማ ዋሻ እየረገሟት ሰዎች በርቀት ያልፏታል። ኢትዮጵያ ተመልሳ ቀና ትላለች። ፍላጎታቸውን እየሸሸጉ ፖለቲከኛ የሆኑ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች ከጥፋታቸው ከተመለሱ የእግዚአብሄርን ምህረት ያገኛሉ፣ ካልተመለሱም ፍርዱን ለእግዚአብሄር እንተው።
እኔ አሁን ይህን ሁሉ ያልኩት ፖለቲካ ልተነትን ሳይሆን ጊዜ ላነሳቸው ለቋንቋ ፌደራሊዝም አቀንቃኞች ልመና ለማቀርብ ነው። አማራው በየቦታው ይገኛል። ይህ የሆነው መላ ሃገሪቱ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች መኖርያ በመሆኗ ነበር። “የኔ ዘር ካልሆንክ ክልሌን ለቀህ ሂድ” አዲሱ የቋንቋው ፌደራሊዝም መመርያ ከሆነ ሰንብቷል። ልመናዬ ይህን ተከትሎ ነው።
የተከበራችሁ የበላይ ባለሥልጣኖች፣ የክልልና የዞን መሪዎች፣ የፖሊስና የጦር አለቆች – አማራው እግዚአብሄር የወሰነለት እስኪጸና ድረስ በግድ እንዳይፈናቀል እባካችሁ ጥበቃ አድርጉለት። እባካችሁ እግዚአብሄር የሚወደውን ሠብዓዊ መብት ጥበቃ አትንፈጉት። አያት ቅድም አያቱ ከቡልጋ የመጡት አማራ ዛሬ ድንገት ወደ ቡልጋ ሊሄድ አይችልም። ማንም የአያት ቅድም አያቱን አገር አያውቅም። ስለሆነም ወደ ሸዋ፣ በጌምድር፣ ወሎና ጎጃም መሸኘት ካለበትም – እባካችሁ –በሠላም እስኪሄድ ድረስ መቆምያ መቀመጫ አታሳጡት። አማራም ሰው ነውና እንደ ሰው ተመልከቱት። እባካችሁ የበደኖውና አርባጉጉው የዘር ፍጅት ይብቃ። እባላችሁ የጉራፈርዳው፣ የሃረሩ፣ አርሲው፣ ጂማው፣ ወለጋው፣ አፋሩ፣ መተከሉና ቤንሻንጉሉ መፈናቅል ይብቃ።፡እባካችሁ ጥቃት ይብቃ –ፖለቲካውን በሠለጠነ መንገድ እንምራው። ወያኔ ፊታውራዊን ልኮ “ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖር አማራ ነፍጠኛ ነው” ያለውን የጥላቻ፣ የበቀልና የማስጠቅያ ስውር ቃል ተግባራዊ አይደረግ። መላው አማራ እንደምን ገዥ ተደርጎ ይፈረጃል? እኔ በጦርነት አላምንም። ሁሉንም አይተነዋል – ጥቅም አልሰጠንም። እኔ ለምስኪኑ አማራ ስል ልመናዬን የማቀርበው በፖለቲካ ውሃ በማይቋጥር ትግል ሙሉ እምነት ስለሌለኝ ነው። ደካማ ትግል ትተን እንዳቅማችን በልመናና ጸሎት ደሃውን አማራ ብንታደገው ጠቀሜታ አለው ብዬ አምናለሁ።
በሃገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም በመላው ዓለም በስደት የምትኖር አማራም ጸልይ፣ እጆችህን እላይ እሰማይ ላለው አምላክ አንሳ፣ ሃገሪቱ ላይ ሠላም እስኪሰፍን ድረስ ለራስህ ብቻ መኖርን፣ ብቻህን መብላትንና ብቻህን መጠጣትን አቁም። ቤት የሚሰራው፣ መኪና የሚነዳው ወገንህ በሠላም ሲኖር ነው። አማራ እየተፈናቀለ፣ በዱር አውሬ እየተበላ፣ እየተራበና እየታረዘ ቪላ ቢገነቡ፣ ሾፍሬሌትና ማርቼዲስ ቢያማርጡ፣ ፓሪስና ኒውዮርክ ላይ ቢዝናኑ አምላክ ይታዘባል። በዚህ ችግርና መፈናቀል ወቅት አንዱ አማራ ለሁሉም አማራ – ሁሉም አማራ ለአንዱ አማራ ዘብ ይቁም። አማራ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋርም በፍቅር ይኑር። ዘረኝነት ኃጢዓት ነው። አማራው በፖለቲካ ሥርዓቱ ከሚጎዳ ወገን ጋር ሁሉ በመቆም ትልቅ ግብረገብ ያለው ሕዝብ መሆኑን ማሳየት አለበት። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይታደጋል። እሳትና ችግር እያደር ይጠፋል። ኢትዮጵያ ፈጽሞ አትወድቅም። አይዞህ ወገኔ፣ በርታ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፣ አሜን
