(By Achamyeleh Tamiru)

አይን እያላቸው ፍሬውን ከገለባው ለይተው ማየት የማይችሉ፤ አእምሮ እያላቸው የሚጠቅመውን ከሚጎዳው ለይቶ ማስተዋል ያቃታቸው፤ እንደ በግ መንጋ ከፊታቸው የሚሄደውን ጌታቸውን ተከትለው የሚንጋጉትና እንደ ጭነት ከብት የጫኗቸውን ተሸክመው ሲጎተቱ የኖሩት የጉድ ማኅበርተኞቹ ብአዴኖች ለውጥ የሚባለው የዐቢይ አሕመድ ቴያትር ከተጀመረበት ጊዜ አስንቶ የማይተገብሩትንና አጀንዳቸው የማያደርጉትን መግለጫ ማውጣትን እንደ ጊዜ መግዣ ስልትና የተቆጣውን የአማራ ወጣት እንደማደንዘዣ ክኒን አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ባለፈው አንድ አመት ብቻ ብአዴኖች ብዙ መግለጫዎችን አውጥተዋል። ሆኖም ግን አንዱንም መግለጫ የብአዴን ቋሚ አላማ አድርገው ሲሰሩበትና ሱኖሩት አላየንም፤ ምክንያቱም ብአዴን የሚሰራውና የሚኖረው ምክትል ላደረጉት ጌቶቹ እንጂ ለአማራ ሕዝብ አይደለም።

ብአዴን በትናንትናው እለት ስለ አዲስ አበባ ያወጣው መግለጫውም የሕዝብ ጫና ስለበረታበት ተቃውሞውን ለማስተንፈስ እንጂ የአዲስ አበባን ጉዳይ ቋሚ እምነቱ፣ ባለ ጉዳይ ሆኖ የሚገፋበት ዘላቂ አላማውና ቀጣይ አጀንዳው ስለሆነ አይደለም። ብአዴን የአማራ ሕዝብም ይሁን የአዲስ አበባ ባለጉዳይ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ለመተቸት ባልተነሳን ነበር። ሆኖም ግን ብአዴን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ የጌቶቹ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ የአማራ ሕዝብ ባለጉዳይ ስላልሆነ የአማራ ሕዝብ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ የሚፈጽምበትን ግፍ ዝም ብሎ እንደማያይ ስለታየ የተነሳሳውን ሕዝብ ለማደንዘዝ ብአዴን ስለ አዲስ አበባ መግለጫ እንዲያወጣ ተደረገ እንጂ አሁንም ብአዴኖች ከራሳቸው ግዞት ያልወጡ፣ ምንም ቢፈጠር የሚያስሸፍት የመንፈስ ወኔ የሌላቸው የጉድ ማኅበርተኞች ናቸው።

የብአዴን መግለጫ ማደንዘዣ [ሕዝብን demobilize ማድረጊያ] እንጂ ባለጉዳይ የሚሆንበት አጀንዳው አለመሆኑን የአዲስ አበባ ባለቤትነትን አጀንዳ እነማን ጉዳይ እንዳደረጉት ከሰጠው ማጭበርበሪያ ማየት ይቻላል። ብአዴን በአቋም መግለጫው «[የአዲስ አበባ ባለቤትነት አጀንዳው] ለዉጡን የማይደግፉ ኃይሎች የሚጠነስሱት የፖለቲካ ሤራ ነው፡፡» ብሏል። እስካሁን ድረስ ሲነገር እንደሰማነው ለውጥ የተባለውን ነገር የማይደግፉ የሚባሉት ፋሽስት ወያኔዎች ናቸው። ሆኖም ግን የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጉዳይ አጀንዳ ያደረጉት ብአዴን እንደሚለው ለውጡን የማይደግፉት ፋሽስት ወያኔዎች ሳይሆኑ የለውጡ ሐዋርያ ነን የሚሉን ኦሕዴዶቹ እነ ዐቢይ አሕመድ ናቸው። ብአዴን ግን ባለጉዳይ ስላልሆነ፤ መግለጫውም ማጭበርበሪያ እንጂ ምንነቱ ሳልሆነ የችግሩን ምንጭ ሊነግረን አይፈልግም።

እንዴውም አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ ብአዴን ኦሕዴድ ዋና አጀንዳ ያደረገውን ጉዳይ ሕዝቡን ለማደንዘዝ ባወጣው የማይገፋበት መግለጫው ጉዳዩን ላም ባልዋለችበት የሕወሓት ሴራ አድርጎት አረፈ። ብአዴን ስለ አዲስ አበባ ያወጣው መግለጫው ባለጉዳይ የሚሆንበት ትክክለኛ አጀንዳው ቢሆን ኖሮ ሕዝብ የሚያውቀውን ትክክለኛውን የችግሩን ምንጭ ይነግረን ነበር እንጂ የእንጀራ አባቱ የዐቢይ አሕመድ ግብረ በላነቱን እንዳይቀርበት በፈጣሪውና በአሳዳጊው በፋሽስት ወያኔ አሳቦ ቀባብቶ ለማለፍ ባልሞከረ ነበር። ግና ብአዴን ዘንድሮች እንደድሮው የአዲሶቹ ጌቶቹ ጉዳይ ፈጻሚ እንጂ የአማራ ሕዝብ ባለጉዳይ ከቶ አይደለምና አይጥ በበላ ዳዋ ይመታል።

ሕገ መንግሥት ተብዮው አዲስ አበባን በኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ እንጂ «ኦሮምያ» የሚባለው ክልል ዋና ከተማ እንደሆነች አያውቅም። ሕገ መንግሥት ተብዮውን ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉን ኦነጋውያንና የመንፈስ ልጆቻቸው ኦሕዴዶች አዲስ አበባን ኦሮምያ የሚሉት ክልል ዋና ከተማ አድርገው የሚቆጥሯት ሕገ መንግሥት ተብዮው ስለፈቀደላቸው ሳይሆን አብዛኛው ኗሪ አማራ የሆነባትን መዲና እያስገበሩ ሕዝባችን የሚሉትን ጥቅም ለማስከበር በሕግ ያልተከለከለን ነገር ማድረግ ወንጀል አይደለም የሚል መከራከሪያ እያነሱ ነው።

ብአዴን መዲናው ካደረገው ባሕር ዳር ኗሪ በብዙ እጥፍ የሚባልጥ አማራ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖራል። አብዝሃ የሆነውን የአዲስ አበባን አማራ ራስን በራስ ማስተዳደር እየተባለ በየለቱ በሚለፈፍበት አገር ውስጥ ኦሮሞ እንጂ አማራ አስተዳድሮት አያውቅም። በሌላ አነጋገር አማራ እየተዳደረ ያለው በብአዴናን በኦሕዴድ በሁለት መንግሥት ነው ማለት ነው። ብአዴን የአማራ ባለጉዳይ ከሆነ እስቲ የአማራን ጥቅም ለማስከበር እንደ ኦሕዴድ በሕግ አልተከለከለም ብሎ አዲስ አበባን የአማራ ዋና ከተማው አድርጎ መናገሻውን ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ በማዘዋወር የአማራን ሕዝብ አንድ መንግሥት ስር አስተዳድሮ ያሳየን?

ሁልጊዜ በአፍለኛ አጀንዳዎች የሚታለለው ሕዝባችን በብአዴን ማደንዘዣ መታለል የለበትም። ታድሻለሁ የሚለው ብአዴን ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ሲነሳ እንዲደነዝዝ አፍለኛ አጀንዳ ሲያወጣ እንጂ ተከታታይነት ያለው ስራ ሲነራ አላያነውም፤ ታሪኩም ይህንን አያሳይም። በኢትዮጵያዊነቱ ሟች ለሆነው ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሲያስተምሩ የሚውሉት ስራ ፈት ስሑት ኃይሎች ሲያደነዝዙት የሚውለው ባላነሰ የአማራ ሕዝብ በኅልውና አደጋ ላይ የተኙት የጉድ ማኅበርተኞችና ከጅብ የማያስጥሉት የአህያ ባሎች የማይተገብሩትን ግን የተቆጣውን ሕዝብ ለማረጋጋት በሰጡት ጊዜያዊ መግለጫ ተታሎ መደንዘዝ [demobilized መሆን] የለበትም።

የአማራ ሕዝብ ተስፋው በትግሉ ከሕወሓት ሎሌነት ወደ ኦሕዴድ ግብረ በላነት ያሸጋገራቸው የጉድ ማኅበርተኞች ሳይሆኑ አንድነቱ፣ ብርታቱ፣ ጥንካሬውና ክንዱ ብቻ ናቸው! ሕገ ዘወያኔ ወኦነግ ተወግዶ የሁሉም የሆነ ሕገ ኢትዮጵያ እስካልቆመ ድረስ አማራ እነዚህን መሳሪያዎች ታጥቆ በተከታታይነት እስከቀራንዮ ድረስ የሚደረግ ተጋድሎ ብቸኛው መዳኛ መንገድ! አበቃ!FacebookTwitterGoogle+