February 25, 2019

እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ 1984 በተደረገው የኢትዮጵያ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይ የማከላዊ እስታቲስቲክስ ጽ/ቤት ሰራተኛ ሆኜ ገና ከኮሌጅ በወጣሁ በሁለት አመት የተሳተፍኩበትና ለሃገሪቱም የመጀመሪያው ስለነበር በብዛት ትዝ የሚለኝና የማረሳው ግዜ ነበር። ወቅቱ የደርግ ጊዜ ነበርና በሲዳሞ ክፍለ ሃገር በያቤሎ አውራጃ የቴክኒክ ሃላፊ ሆኜ ለሶስት ወራት ያህል በመስክ ላይ ስለነበርኩ በመሬት ላይ የነበረውን ሁኔታ በደንብ አስታውሳለሁ። በዚያን አስርተ አመታት (1975 -1984) 95 በመቶ የሚሆነው የአለም ህዝብ የተቆጠረበት ጊዜ መሆኑን አንድ በተባበሩት መንግስታት የእስታቲስቲክስ ኮሚሽን በወቅቱ የወጣ ሪፖርት ያመላክታል። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ፣ በኤርትራ እና በኦጋዴን የገጠር አካካቢ በወቅቱ በነበረው የበጸጥታ ችግር ቆጠራው አለመካሄዱ የሚታወቅ ሃቅ ነበር።. ያኔም እንዳሁኑ ቆጠራውን በበላይነት እንዲመራ በአዋጅ የቆጠራ ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር። አለመታደል ሆኖ ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ የህዝብና የቤቶች ቆጠራን በበላይነት የሚመራው የማከላዊ እስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከመንግስት ተጽእኖ እና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ስራውን በትክክል የሰራበትን ጊዜ ግን ትዝ ኣይለኝም። እኔ የመስሪያ ቤቱ አባል በነበርኩበት የደርግ ዘመነ መንግስት እንኳ የአወቃቀር ተጽእኖ በአጀንሲው ላይ እንደነበረ ቢታወቅም ተጽእኖው ግን ከህዝብ ቆጠራው ይልቅ በሌላው የአጀንሲው መደበኛ የስታቲስቲክስ ስራ ላይ ነበር። በግብርና እና በሌሎች የምርት ውጤት ጥናቶች ላይ ጫና ነበር ማለት ይቻላል መረጃዎች በሙያው እውቅት የሌላቸው የበላይ ባለስልጣናት ካላጸደቁት ለተጠቃሚዎች አይለቀቅም ነበር። አሁን ሚን ያህል እንደሆን ባላውቅም ያን ጊዜ መንግስት ያልተስማማባቸው የጥናት ውጤቶች ይፋ አይሆኑም ነበር። ያም ሆኖ ግን ለደርግ የህዝቡን ብዛት ማወቅ ያለው ፋይዳ አሁን ከሚኖረው በጣም ይለያል፤ ክፍልሃገራት የህዝብ ብዛት ፉክክር ስላልነበራቸው ወይም የህዝብ ቁጥር መብዛት ለክፍለሃገራት የሚያስገኘው ልዩ የፖለቲካ ጥቅም ስላልነበረ በአቆጣጠሩ ላይ ብዙም የከፋ ጫና አልታየም። የህዝቡን ቁጥር ማወቁ ግፋ ቢል አስፈላጊ የምግብና ሌሎች ፍጆታዎችን ለመገመት ካልሆነ፣ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ የአለም ህዝብ አካል ስለነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚያደርገው ትጽእኖ ካልሆነ በስተቀር ሌላ የፖለቲካ ፋይዳው ይህን ያህል አልነበረም ማለት ይቻላል። ብቻ ያኔ የነበረው የፖለቲካ ድባብ አሁን ካለው ፍጹም የተለየ ነበር ብሎ ለመገመት የተለየ አዋቂ ሰው መሆን አያስፈልግም እንደኔ አይነቱም ሰው ይህንን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ታዲያ የፖለቲካው ሁኔታና የጸጥታ ሁኔታ ለቆጥራ ፍጹም ነው በማይባልበት ጊዜ፤ እንዲያውም የሃገሪቱ አለመረጋጋት ከፖለቲካው ጋር ቁርኝቱ ከፍ ባለበት ሁኔታና ጽንፈኝነት በነገሰበት በዚህ በአሁኑ ሰአት ቆጠራውን እንዴት በትክክል ማስኬድ ይቻላል?
ትክክለኛ የህዝብ ቆጠራ ማለት ህዝቡን ባለበት ቦታ በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ በትክክል መቁጠር ማለት ሲሆን ይህንን ለማካሄድ የማአከላዊ እስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሶስት ዋና ዋና ነገሮችን ማድረግ መቻል ያለበት ይመስለኛል። ይህም ቆጠራውን በመመሪያው መሰረት የሚመዘግብ ሰራተኛ ማዘጋጀት፤ በተባለው የጊዜ ሰሌዳ የሚቆጠረው ህዝብጋ ደርሶ ምዝገባውን ማካሄድ፤ እና ከዚያም መረጃውን ሰብስቦ እና አጠናቅሮ የቆጠራውን ውጤት ለህዝብ ማሳወቅ ናቸው። ታዲአ እነዚህን ለማድረግ ከፖለቲካ ጫና ውጪ የሆነ የቆጠራ ሰራተኛ በየቆጠራው አካባቢ ለማግኘትና በተባለው ሰአት ህዝቡጋ ደርሶ ቆጠራውን ለማካሄድ የየአካባቢው ሁኔታ አመቺ መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው። እንደእውነቱ ከሆነ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ከላይ የጠቀስኳችውን የኤጀንሲው ማድረግ ያለበትን ነገሮችን ለማሳካት ከመርዳትና ከመተባበር ውጭ ሌላ ተጽእኖ መፍጠር የለባቸውም። ሌላው የቆጠራ ጉዳይ መተው ያለበት ለቆጣሪው መ/ቤት ብቻ ነው። የማአከላዊ እስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በቆጠራው ጉዳይ ላይ ፍጹም ነጻ መሆን ይገባዋል። ያለበለዚያ የቆጠራው ውጤት በተወሳሰበው የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ አንድ ተጨማሪ እራስ ምታት እንዳይሆን እሰጋለሁ። ለሃገራችን ፖለቲከኞች አይታያቸው ይሆናል እንጂ የማአከላዊ እስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደምርጫ ኮሚሽንና እንድ ፍርድ ቤቶች ፍጹም ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ተቋም መሆን አለበት። በተጨማሪ የተቋሙ ቀዳሚ ስራ ደግሞ የሃገሪቱን መረጃዎች በሚገባና ሳይንሳዊ ዘዴን በተከተለ ሁኔታ ሰብስቦ ያለምንም አድሎና ተጽእኖ መረጃ ስጪዊችን ባላጋለጠ ሁኔታ ለተገልጋዮች ወይም ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መሆን አለበት። የህዝብ ቆጠራው አካሄድና ውጤትም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይገባውም። ታዲያ አሁን ያለንበት ሁኔታ ለምርጫ አመቺ ካልሆነ እንዴት ለቆጠራ
አመቺ ይሆናል ተብሎ ተገመተ? በርግጥ ትክክለኛ የህዝብ ቆጠራ ከምርጫው በፊት መሆን ቢገባውም የምርጫውን ያህል ጸጥታና መረጋጋት ስልሚፈልግ እንዴት ያንን መንግስት ማየት እንዳልቻለ ለኔ ግልጽ አይደለም። በመሬት ላይ ያለው ጉዳይ የዛሬ 35 አመት እኔ ከነበርኩበት ጊዜ የተለየ ቢሆንም ዋናው ቆጥራ የሚደረገው በታችኛው የመንግስት መዋቅር ማለትም በቀበሌ ወይም በገበሬ ማህበር መሆኑ በአሁኑ ቆጠራ የሚቀየር ጉዳይ አይመስለኝም።
ከበጀትና ሌሎች ክልላዊ ድልድሎች ውጭ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ማወቅ ብዙ አዎንታዊ ፋይዳዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። መንግስት ወቅታዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፕላን ለማዘጋጀት የህዝቡን ቁጥር በብሄራዊና በክልል ደረጃ ብሎም ወረድ ባሉ የአስተዳደር ደረጃዎች ማወቅ ቢችል ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም። እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የአለም ህዝብ አካል እንደመሆኑ ሁሉ ቆጠራው የአለም ህዝብን በትክክል ለመቁጠር አንድ እርምጃ ተደርጎ ሊገመት ይችላል። ለኤጀንሲው ደግሞ ወደፊት ሌላ የህዝብ ቆጠራ እስከሚካሄድ ድረስ አመታዊ የህዝብን ግምታዊ ቁጥር ለመተንበይ (population projection) እና ለሌሎች የኤጀንሲው ቀጣይ ጥናቶች ናሙናዊ ማእቀፍ (sampling frame) ለማዘጋጀት ዋናው ቁልፍ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አመታዊ የግብርና ናሙናዊ ጥናቶችም ሆኑ ሌሎች የእኮኖሚ ጥናቶች ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት መሰረታቸው የሚሆነው ይኸው ያሁኑ ጠቅላላ የህዝብ ቆጠራ ውጤት ነውና በትክክል የመሰራቱን አስፈላጊነት ላሰምርበት እፈልጋለሁ። የፖለቲካ ምርጫ በትክክል ወይም ባልተጋነነ ሥህተት መካኼድ እንዳለበት ካመንን የሕዝብ ቆጠራን በትክክል ወይም ባልተጋነነ ሥህተት መካኼድ እንዳለበት መቀበል ግድ ይላል፤ የምርጫን ውስብስብነት ከተቀበልን የሕዝብ ቆጠራን የባሰ ውስብስብነት መገንዘብ ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ። ምርጫ በምርጫ ጣቢያ ብዙ ታዛቢዎች ባሉበት ባብዛኛው የሚከናወን ሲሆን ከምርጫ ጣቢያ ደረጃ ሳይወርድ ሊጠናቀቃል፣ በጣቢያ ደረጃ ስለሆነም የብዙ ሰው አይንም ሁኔታውን በቅርብ ሊከታተለው ይችላል፤ ያም ሆኖ ግን በየጊዜው የሚከሰተውን የምርጫ ችግር የሚያውቅ ያውቀዋል። ህዝብ ቆጠራ ላይ ግን የቆጠራው ጣቢያ እኔ እስከማውቀው ድረስ የሚሸፈነው በአንድ ቆጣሪ ነው፤ የሚከናወነውም በእያንዳንዱ ነዋሪ ቤት ነው። ተመራጭ ባይሆንም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የአካካቢው የጸጥታ ሰዎች የቆጣሪውን ስራ ለማሳካት ሊያጅቡት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም በጸጥታ ጠባቂዎች እገዛ ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ ቆጠራ ለመረጃ ብክነት ከመጋለጥም ባሻገር ሰዎች በሚሰጡት መረጃ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው መገመት ተገቢ ነው። ስለዚህ በባለስልጣናት አጀባ የሚካሄድ ቆጠራ ውጤት ላይ ጥያቄ እንደሚጋብዝ ቢታወቅም ከመደበኛ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ውጪ በመሆኑም የመረጃ ጥራት ጉድለት ሊኖረው ይችላል። ታዲያ አሁን ባለው ሁኔታ ይኼ ጉዳይ ፍጹም ሆኖ ሊከናወን ይችላል ወይ? በየቤቱ እየዞረ ቆጣሪው የሚያከናውነው ሰራተኛ በቆጠራ መመሪያው መሰረት መስራት ቢፈልግስ ምን ያህል ይሳካለታል? የአካካቢው ሰው እንደመሆኑ መጠን ቆጣሪው ሕሊናውን ነጻ አድርጎ ለመስራትስ አሁን ያለው ሁኔታ ያስችለዋል ወይ? እነዚህ ችግሮች ያሉት በአንዳንድ አልፎ አልፎ በሚገኙ ኪስ አካባቢዎች ቢሆን እንኳን ልዩ የግመታ ዘዴዎችን (inferential method) በመከተል ቆጠራውን ማስተካከል ይቻል ብሎ አማራጭ መፍትሄ ማቅረብ ይቻል ነበር፤ የችግሩ ጀረጃ ግን አልፎ አልፎ በሚገኙ ኪስ አካባቢዎች ላይ ብቻ የተወሰነ አይመስለኝም። ካልተሳሳትኩ በስተቀር በአሁኑ ጊዜ ያለው የሃገሪቱ አጠቃላይ ገጽታ በተሻለ መረጋጋት የመረጋጋት ሁኔታ ላይ መሆን ይገባዋል ብዬ አስባለሁ። ሁኔታው ለቆጠሪዎች የተመቻቸ፣ በየአካባቢው የፖለቲካ ተጽእኖ የማይታይበት፣ የማእከላዊ እስታቲስቲክስ አኤጀንሲም የቆጠራ ተልኮውን ያለ እኔ አውቅልሃለሁ የፖለቲካዊ ጉትጎታ ማጠናቀቅ መቻል አለበት። ይህንን መሚገባ ተግባራዊ ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጃል የሚል ሃሳብ አለኝ። ይህንን ያህል በርካታ ሃብት አፍስሶ በቆጥራውን ዘግይቶም ቢሆን በትክክለኛ ውጤት ማጠናቀቁ ይሻላል እንጂ አሁኑኑ ብዙ ክፍተቶች ባሉበት ሁኔታ እናድርገው ማለቱ ጉዳቱ ያመዝናል ብዬ አምናለሁ። መንግስት ለምርጫው የወደፊት ተአማኒነት ጥረት እንደሚአደርገው ሁሉ ለህዝብ ቆጠራውም የወደፊት ተአማኒነት የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ።
የህዝብ ቆጠራ ውጤት ሁሉንም ፖለቲከኛ ያስደስታል ብሎ ማመን ይችግራል። እንኳን እንደኢትዮጵያ ባለው ታዳጊ ሃገር ይቅርና በአደጉትም ሃገሮችህ የህዝብ ቆጠራ አጨቃጫቂ የፖለቲካ መስመር መፍጠሪያ መንገድ መሆኑን እናያለን። ታድያ በበለጸጉት ሃገሮች ጭቅጭቁ እነማን ይቆጠሩ በሚለው ላይ ሊሆን ይችላል እንጂ በቆጠራው ውጤት ላይ ግን ሲሆን እምብዛም አይስተዋልም።
ምክንያቱም ቆጠራው የሚከናወነው እና የሚመራው ኤጀንሲ የሙያው ክህኖት ባላቸው አዋቂ ኤክስፐርቶች እንጂ በፖለቲካ ተሳትፎአቸው በሚመደቡ የፖለቲከኞች ስላልሆነ የቆጠራው ውጤትም ሆነ የኤጀንሲው ተአማኒ መሆን አከራካሪ አይሆንም። ፖለቲከኞችም በቆጠራ ጉዳይ ባጀት ከመመደብ በላይ ጣልቃ ለመግባት አይደፍሩም። ይህ ግን በኛ ሃገር የህዝብ ቆጠራ ታሪክ ሆኖ ባያውቅም አሁን ሃገሪቱን የሚመራው መንግስት ኤጀንሲውን ከፖለቲካ ነጻ ማድረግ አይፈልግም ብዬ መገመት ፍጹም ይቸግረግናል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የለውጡ ሃይል ሌሎች ሃገሪቱ አይታ የማታውቀውንና ለየዲሞክራሲ መሰረታዊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሲያመቻች በአይናችን አይተናል። የሃገሪቱን ህዝብ በሚገባ ማወቅ በተለይም ለፌደራላዊ ዲሞክራሲ በጣም አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅምና መንግስትም የህዝቡን ቁጥር በትክክል ማወቅ ያለውን ጠቀሜታ በሚገባ ተገንዝቦ፣ ቆጠራውን የሚመራው መንግስታዊ ድርጅት ከማንምና ከምንም የፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ መሆኑን ከቆጠራው በፊት ማረጋገጥ ዪኖርበታል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም በመጀመሪያ የማእከላዊ እስታቲስቲክስ አኤጀንሲ እራሱን ከፖለቲካ ነጻ በሆነ መንገድና በበቂ ሙያተኞች መገንባቱ ግድ ይሆናል። ኤጀንሲው ከፈለገ ሊረዱ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማግኘት የሚቸግረው አይመስለኝም። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተናገሩትን ማስታወስ ይበቃል፤ “ሃገራችንን የተማረ ሰው ድህነት የለባትም” ብለው ነበር። በርግጥም ኤጀንሲውን በዚህ የሙያ መስክ ሊረዱ የሚችሉ በቂ ኤክስተርቶች በአለም ዙሪያ አሉን ብዬ እገምታለሁ። እነዚህን የፖለቲካ አጀንዳ የሌላቸውንና ሃገራቸውን ሊረዱ የሚፈልጉ ሙያተኞች ከሃገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ለዚህ ስራ እንዲረዱ ኤጀንሲው ምን ያህል ጥረት እንዳደረገ ባላውቅም ብዙ እንደማይሆን ግን እገምታለሁ። ዋናው ጉዳይ ግን ቆጠራው በሙያተኖች በተሞላ እና በሙያተኛ ብቻ በሚመራ ድርጅት ያለ ምንም መንግስታዊ ተጽእኖ መከናወኑ ስለሆነ ይህ መሟላቱን መንግስት ከቆጠራው በፊት ማረጋገጥ ይኖርበታል።
ቆጠራው በዋናነት መሚካኼድባቸው ወረዳና ቀበሌዎች ያሉ ባለስልጣናት የሕዝብ ቁጥር የአስተዳደር ጫና ፈጣሪ እዳ እና የመልካም አስተዳደር መንገድ የወደፊት አመላካች መረጃ እንጂ የፖለቲካ ትርፍ ማካበቻ ዘዴ አድርገው እንዳያዩት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። እንደዚህ ያለ የተንጋደደ ግንዛቤ በአሁኑ ወቅት በዞንም ሆነ በክልል ደረጃ አይኖርም ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ፤ ስለዚህ የህዝብ ቁጥርን ውጤት በትክክል ማወቅ ያለውን ጠቀሜታ በየደረጃው ላሉ ባለስልጣናት ማስገንዘብ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ፤ ታዲያ ይህንን በሚገባ ለማከናወን ኤጀንሲው በቂ ጊዜ ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁ። የህዝብ ቁጥርን ውጤት መቀየር ወይም ሆን ብሎ ማሳሳት ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለህዝቡ በተለይም ለወጣቱ መሚገባ ማስተማር ይገባል። አሁን የሚሰራ ስህተት የሚያምጣውን ችግር የሚረከው ያሁኑ ወጣት ነው፤ ይህንን ደግሞ አዲሱ የሃገሪቱ የለውጥ ሃይል በሚገባ እየሰራበት ስለሆነ የኤጀንሲውን ስራም ያቀለዋል ብዬ እገምታለሁ ሆኖም እታች ወጣቱጋ እስከሚደርስ ጊዜ መውሰዱ ግን አይቀሬ ነው።
የግድ አሁኑኑ ይደረግ ብሎ ከማሰብ አላስፈላጊ የጊዜ ገደብ ከመጫን ይልቅ የህዝብ ቆጠራውን የተሳካ ማድረጉ ላይ ቢሰራ ጠቃሚ ይመስለኛል። ያን ያውራ የነበረ ነውና ለቆጠራው መሳካት የተረጋጋና ፀጥታው የተረጋገጠ ሃገራዊ ሁኔታን ማመቻቸት ከሁሉ በላይ ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት፤ በተጨማሪ ቆጠራውን አስመልክቶ የህዝቡ ግንዛቤ እንዲያድግ በቂ ትምህርትና ቅስቀሳ ከቆጠራው በፊት መደረግ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ። ቆጠራውን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርት በየአካባቢው ላሉ የክልል፣ የዞን የወረዳ የገበሬ እና የከተማ ቀበሌ ባለስልጣናትና ሊሰጥ ይገባዋል፤ በርግጠኝነት ለመናገር ያብዛኛዎቹ የቆጠራ ግንዛቤ ከፖለቲካ የተያያዘ ነው ቢሎ መናገር ይቻላል፤ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ በበቂ ትምህርትና ስልጠና መቀየር አለበት። በመጨረሻም ቆጠራውን የሚመራው ኤጀንሲ ለቆጠራው መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው። በአደረጃጀቱም ሆኖ በሰው ሃይል ክምችቱ ከፖለቲካ የራቀ መሆን አለበት። መስሪያ ቤቱ እንደ ፍርድ ቤትና እንደ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተጽእኖ የማይደረግበትና በራሱ የሙያው ብቃት ባላቸው ሰራተኞቹ ሃላፊነት ሥራውን በሚገባ መስራት የሚችል መሆን አለበት። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን ኤጀንሲው በዚህ ደረጃ ላይ ነው ብሎ መናገር ይቸግራል። መንግስትም ኤጀንሲውን ከፖለቲካ ነጻ በሆነ አደረጃጀት መስሪያ ቤቱን ማደራጀቱ ላይ በማተኮር የህዝብ ቆጠራውን ለተሻለና ለተረጋጋ ጊዜ ማስተላለፉ ተገቢ ነው። ቆጠራው ቢተላለፍ ለስራው የተመደበውን ሃብት ለሌላ አሁን ሊሰራ ለሚችል ተግባር ማዋል ይቻላል ማለት ነው።
የዚህ ፁሁፍ አቅራቢ በእትዮጵያ በማእከላዊ የእስታቲስቲክስ አጀንሲ ውስጥ ለስድስት ዓመት ተኩል እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ከ1982 ጀምሮ የሰራ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በሚገኝ አንድ ፈደራል መስሪያ ቤት ከፍተኛ የእስታቲስቲክስ ባለሙያ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። በተጨማሪ የፁሁፉ ይዘት የፀሓፊውን የግል ሃሳብ እንጂ በምንም መልኩ የሚሰራበትን መስሪያ ቤት በመወከል አለመሆኑ በቅድሚያ እንዲታወቅ ፀሃፊው ያሳስባል። 428
