February 25, 2019

t

ለሁሉም ግልፅ እንደሚሆነው የኦነግ ተልዕኮ ኦሮሚያን “ቅኝ እየገዛች ካለችው አቢሲኒያ ማለትም ኢትዮጵያ ነፃ ማውጣት” ነው። ይህን ተልዕኮውን ደግሞ በድህረ ገፁ ላይ በሚከተለው መንገድ በ’ንግሊዝኛ ቋንቋ ከትቦት ይገኛል። እንዲህም ይነበባል The Oromo Liberation Front (OLF) is a political organization established in 1973 by Oromo nationalists to lead the national liberation struggle of the Oromo people against the Abyssinian colonial rule. Please follow the link herein next for further information: http://oromoliberationfront.org/english/mission/

የኦነግና ደጋፊወቹ ጥያቄ ቅኝ ገዝታናለች ብለው ከሚያስቧት ኢትዮጵያ ነፃ መውጣት ብቻ ሳይሆን የቅኝ ግዛቱ መሪዎችና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎቻቸውም በድለውናል ብለው ያስባሉ። በዚህም ምክኒያት ከቅኝ ግዛቱ ጋ የተያያዙ ናቸው የሚሏቸውን የሌላ አከባቢ ተወላጆች ሁሉ “ሰፋሪ” ወይም “መጤ” የሚል ጥልቅ በሆነ ጥላቻ ላይ የተመሰረት መጠርያ ሰጥተዋቸዋል። ዋናው ችግር ያለው ስሞቹ ላይ አይደለም፤ እነዚህ ስሞች የተሰጧቸው የሌላ አከባቢ ሰዎች ጠቅልለው ይውጡልን የሚል እንደምታ ያለው ቅስቀሳ እንጅ። ይህ ቅስቀሳ የሚካሄደው ደግሞ ተማርን በሚሉት እንደነ አቶ ፀጋየ ረጋሳ አይነት የኦሮሞ ልሂቃን ሳይቀር ነው። ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችን የቃኘ ሰውም ሊታዘበው የሚችለው ሃቅ ይህንኑ ነው።

ለምሳሌ አቶ ፀጋየ ካስተላለፋቸው መልዕክቶች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፥

እቴጌ ጣይቱና የአፄ ምኒልክ መንግሥት፣ ከተማውንና የሌሎች የብዙ ሕዝቦችን አገሮች ቀምተው ወስደዋል። በተስፋፊነት መንፈስ እየወረሩ ነጥቀዋል።

ከወረራውም በኋላ በፊንፊኔና በሌሎች ከተሞች እየሰፈሩ (በሰፋሪነት) የሰፋሪ ቅኝ ገዥነት ስርዓትን በመመስረት እየተጋነኑ ኖረዋል። በየከተሞቹ እስካዛሬ ያሉት ሰፋሪ ነዋሪዎችም ለዚህ ህያው ምስክርና፣ ተጨባጭ ማስረጃ ናቸው።

የኦህዴድ ሰዎች በበኩላቸው ይህን “መጤዎች” እና “ሰፋሪዎች” ተብለው በሚታወቁ ነዋሪዎች ላይ ያለ ስር የሰደደ ጥላቻ በሚገባ ይገነዘባሉ። ይሁን እንጅ የተሳሳተ ዝንባሌ መሆኑን ለህዝብ አስረድተውና አስተምረው የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ችግሮቹ መሰረታዊ በሆነ መንገድ እንዲቀረፉ ከማድረግ ይልቅ ኦሮሚያ ውስጥ በኦነግ ላይ የበላይነቱን ለማግኘት ሲሉ ስር የሰደደውን ጥላቻ የሚያንፀባርቁ እርምጃወች እየወሰዱ እንደሆነ እየታዘብን ነው።  ለዚህም ነው ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ለገጣፎን በመሳሰሉ አካባቢዎች “የመጤዎችና “የሰፋሪዎች” ቤቶች ናቸው የተባሉትን ሁሉ በጅምላ የማፍረስ እንቅስቃሴን ስራየ ብለው የተያያዙት።

ምንም እንኳ እርምጃው እየተወሰደ ያለው የህግ የበላይነትን ለማስከበር ነው የሚል ሽፋን ያለው ቢሆንም የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ ሌሎች ብዙ መረጃዎች የሚጠቁሙት ግን በማንነት ላይ የተመሰረተ አድሎዋዊ ማፈናቀል እንደሆነ ነው። በዚህ ዙሪያ እየቀረበ ያለው አንዱ ማስረጃ  እዛው ለገጣፎ ውስጥ ያሉ ግን የአከባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ቤት እየፈረሰ አይደለም እየተባለ መሆኑ ነው።

በነገራችን ላይ የኦህዴድ ሰዎች በዚህ አይነት ሁኔታ የኦነግን አጀንዳ እየነጠቁ የራሳቸው በማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው በዚህ የቤት ማፍረስ ሂደት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይመስልም። ነገ ከነገ ወዲያም ቢሆን አዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊከበር ይገባል በሚል የህግ ሽፋን “ዘመኑ ሰጠን” የሚሉትን ስልጣን ተጠቅመው የአዲስ አበባን ህዝብ መጤና “ሰፋሪ” ነው “በሚል” ለማፈናቀል መሞከራቸውና ጎን ለጎንም መዋቅሩን ሁሉ ኦሮሟዊ ለማድርግ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም።

በተጨማሪም የኦሮሚያ ህዝብ ቁጥር ብዙ ነው በሚል ሂሳብ ያለኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ የኦሮምኛ ቋንቋን የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ለማድረግ ተፍ ተፍ እያሉ እንደሆነ እየሰማን ነው። በቅርብ ቀን ባወጡት መግለጫቸውም በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅምና አፋን ኦሮሞን የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ የማድርገ ጉዳይን በተመለከተ እየሰራንበት ነው ብለውናል።  በጎጥ ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝምም ቢሆን ለድርድር እንደማይቀርብ ቁርጥ ያለ አቋም እንዳላቸው በዚሁ ባወጡት መግለጫ ገልፀዋል። ሌሎችም ኦሮሟዊነትን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ሊያደርጉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ረገድ በነጃዋር በኩል እየተሰራበት ያለው የኦሮሚያ የሚድያ ኢምፓየርን በኢትዮጵያ (Media Empire in Ethiopia) የመፍጠር እንቅስቃሴና የኦሮሞ ባህልን ከፍ ከፍ የማድርግ ጅምሮች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

የብዙ ሰው ልብ እየሰበረ ያለው ደባ ደግሞ የኦህዴድ ሰዎች የኦህዴድ ሊቀመንበርም ስውር (Unofficial) የበላይ ሊቀመንበር በሆኑት አቶ ለማ መገርሳ አስተባባሪነትና በነጃዋር ገፊነት ከላይ በተገለፀው መልኩ ሁሉንም ነገር ኦሮሟዊ ለማድርገ እያደቡ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የሰውን ሃሳብ ወደሌላ አቅጣጫ ለማስቀየር ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መዚቃዎችን እንዲጫወቱ  እየተደረገ መሆኑ ነው። ይህ መሆኑን በደንብ የሚያሳይ አንድ ሃቅ ማንሳት ይቻላል።  ከሳምንት በፊት የኦህዴድ ሰዎች በፌዴራሊዝም ላይ አንደራደርም የሚል ቁርጥ አቋም እንዳላቸው አሳወቁ። በዚህ የኦህዴድ አቋም ላይ የተላያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማጉረምረም ሲጀምሩ ደግሞ እንደተለመደው ዶ/ር አብይ የኢትዮጵይዊነት ሚዚቃ እንዲጫወቱ ተልዕኮ ተሰጣቸውና ኢህአዴግን አፍርሰን ሌላ ከጫፍ ጫፍ የሚያቅፍ አገራዊ ፓርቲ እንመሰርታለን የሚል አዝማች ያለው ዘፈን ይዘው ብቅ እንዲሉ ተደረገ።  በኦህዴድ ሰዎችና ከኋላ ሆነው በሚያሾሩት ጃዋርን በመሳሰሉ  የኦሮሞ ልሂቃን ቤት ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም የማይገባውና እንደፈለጉ እየጎተቱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ሊወስዱት የሚችሉ መስሏቸዋል።

ይህን ሁኔታ በተመለከተ ሌላም ሃቅ ማንሳት ይቻላል። ኢትጵያዊነት እያሉ ዘወትር እየሰበኩ በሌላ በኩል ግን በእርሰዎ ሊቀመንበርነት በሚመራው የኦህዴድ መንግስታዊ መዋቅር ከቢሮዎ ብዙም ርቀት በሌለው ለገጣፎ ከተማ በማንነት ላይ የተመሰረተ የቤት ማፍረስ እርምጃ ሲወሰድ ለምን መፍትሄ አልሰጡም የሚል እንደምታ ያለው ጥያቄ ሲጠየቁ ዶ/ር አብይ የሰጡት መልስ ደግሞ እኔ የኢትዮጵያ መሪ እንጅ ከንቲባ ስላልሆንኩ የተፈፀመውን ነገር አላውቅም የሚል መንፈስ ያለው ነበር። እዚህ ላይ እንደ አንድ ጠቅላይ ሚንስትር በሚያስተዳድሩት አገር እየተፈፀመ ያለን ግፍ አላወኩም በማለታቸው እንዳደጉት አገሮች ከስልጣን ይልቀቁ የሚለውን ጉዳይ ለጊዜው እንተወውና እንደዛ ከሆነ ታዲያ ባለፈው የመከላከያ አባላት ቢሯቸው ድረስ ፑሻፕ ያሰሯቸው ቀን የሰበታና ሌሎችም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ህዝብ መንግስቴ ፈረሰ ብሎ ግልብጥ ብሎ መንቀሳቀስ የጀመረ መሆኑን እንዴት አወቁ የሚል ጥያቄ ቢነሳባቸው ምንድን ነው ጥፋቱ??? እረ እየተስተዋለ!!! ለነገሩ አንድ ወቅት ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የመርሳት ችግር አለበት ብለው ሲናገሩ ስለተሰሙ ትላንት የተናገርኩትን ዛሬ ብቀይር የሚያስታውስ የለም ብለው ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይሁንና በተናገሩበት ወቅት ሳይረሳ ወዲያው ተፅፎም ቢሆን ስለሚቀመጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ማስታወስ ሲጀምር በታሪክ ሊወቅሳቸው እንዳይችል በንግግሮቻቸው ሁሉ ወጥነትን (Consistency) እንደመርህ እንዲይዙ ቢመከሩ የተሻለ ይሆናል።

በመጨረሻም ይህ በዶ/ር አብይ እየተቀነቀነ ያለ የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ሙዚቃ ኦሮሟዊነትን ለማንገስ የማያገለግልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ የኦህዴድ ሰዎች አሁንም ሌላ መሰረታዊ የሆነን የኦነግ አጀንዳ መንጠቃቸው የሚቀር አይሆንም። ይህ በኦህዴድ ሰዎች ከኦነግ ሊነጠቅ የሚችል አጀንዳ ደግሞ “በእውቁና” “በስመ ገናናው” አንቀፅ 39 አንደራደርም የሚል ሊሆን ይችላል።  በዚህም ምክንያት ነው የኦህዴድ ሰዎች በምርጫም ይሁን በሌሎች መንገዶች ኦሮሚያ ውስጥ የበላይ ለመሆን የኦነግን አጀንዳ ለመንጠቅ ወደኋላ አይሉም ማለት የሚቻለው።