ከመንግስቱ ሙሴ ፌስ ቡክ የተወሰደ
==================
የጎንደር ሕዝብን በጣም አውቀዋለሁ። የማውቀውም ክፉ ቀኔን ለማሳለፍ መድረሻ ባጣሁበት ወቅት ነው። ዛሬ እንደታሪክ የሚነገረው የያኔው የቀይሽብር ዘመን በጎንደር ሕዝብ ላይ ቀዩን ሽብር ያካሄዱት ህወሓት እና ደርጉ ተቧድነው ነበር። ይህን ስል ይፋዊ መቀናጀት አልነበረም። ሻለቃ ገ/ሕይወት የተባለ ነፍሰበላ የደርግ አባል ግን በስውር የህወሓት ሰርጎገብ የክፍለሀገሩ ምክትል ነበር። ብዙውን እና ጭከና የተሞላበትን ፍጅት ያካሂድ የነበረው ይህ ሰው ነበር። ኢሕአሰ (የኢሕአፓ ሰራዊት) ከህወሓት ጋር ወልቃይትን ልውሰድ አላስወስድም በተደረገ ውጊያ ማግስት መላ የሰሜን ጎንደርን ሕዝብ የጨረሰ ሰው ነው። የሰሜን አርሷደሮችን ኢሕአሰን ደግፋችኋል በሚል መረጃ ሳይኖረው ገበሬወችን እስከነፍሳቸው በሊማሊሞ ገደል ወርውሯል። ይህ ደግሞ አሉባልታ ሳይሆን ታሪክ እና እውነት ነው። በአርማጭሆ፣ ጸገዴ፣ ሁመራ እና ዳንሻ የገደላቸው አርሷደሮች ተቆጥሮ የሚያልቅ አልነበረም። ባጋጣሚ ኬላ ላይ ተይዠ ለሁለት ቀን ሁመራ ፖሊስጣቢያ ከጓደኛየ ከለማየሁ (አሌክስ አሁን ዴንማርክ) ከሚኖር ጋር ለሁለት ሌሊት አድረናል። የፖሊስጣቢያውን የሞላው የወልቃይት፣ የጸገዴ እና የታች አርማጭሆ አርሷደሮች ቁጥር እጅግ ብዙ ነበር። ምክንያቱን ለማወቅ እኛም ያው እንደነሱ እንመሳሰል ስለነበር ባደረግሁት ሙከራ አንድም ደረቅ ወንጀል ሰርቶ የተያዘ አርሷደር አልነበረም። ስለፖለቲካ የማያውቁ ገበሬወችን በሬያቸውን እያስፈታ በጥርጣሬ ያሰራቸው ገ/ሕይወት መሆኑን ነግረውኛል። ሁሉም ያገኘኋቸው አርሷደሮች ከዚያ እስርቤት መፈታታቸውን እጥረጠራለሁ። ምክንያቱም ገ/ሕይወት ፈራጅም አሳሪም ስለነበር የያዛቸውም ለህወሓት ይቃወማሉ በሚል ስለነበር ነው።
ፈጣሪ ደግ ነው ሁሉን ያያል እና ገ/ሕይወት ብዙ ሳይቆይ በሄሊኮፕተር አደጋ ሞተ እና የደርጉ ምክትል አባል ስለነበር በክብር መንግስታዊ አቀባበር በተፈጸመለት ማግስት የሀሓት ሬዲዮ እንባ በማውጣት ሙሾ ማውረዱ ተሰማ በይፋም ጓዳቸው እና ቆራጡ ታጋይ ገ/ሕይወት ማለፉ ለድርጅቷ ጉዳት መሆኑን የወያኔ ሬዲዮ ገለጸ። ደርጉም በክብር የቀበረውን እሬሳ አውጥቶ ማቃጠሉ ተሰማ። ባጭሩ ይህን ሁሉ ለመዘርዘር ያነሳሳኝ የጎንደር ሕዝብ መከራ በተለይም የምእራብ ጎንደር ሕዝብ ከዘመን ዘመን ያላቋረጠ መከራን ለማሳየት ነው።
የጎንደር ሕዝብ አንድ አይነት ነው። በባህል፣ በወግ፣ በልማድ፣ በቋንቋ እና በእምነቱ ሦስቱን የቆዩ እምነቶች ተቀባይ ነው (ተዋሕዶ፣ እስልምና፣ እና ይሁዳዊ) በይበልጥም አሁን ጠላት በለኮሰው የማንነት ጉዳይ ማንነቱ ተመሳሳይ የሆነን ሕዝብ እርስ በእርስ የማባላቱ ተግባር በሕዝብ የታለመ፣ የታቀደ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እነፊታውራሪ አየለ እና እነ አሞራው ውብነህ (ራስ ውብነህ) ቢትወደድ አዳነ የመሳሰሉ ቁንጮ የኢትዮጵያ አርበኞች የወጡት በዚሁ ቀጠና ነው። ጠላት ሀገራችንን በወረረበት ግዜ የሀገር እና የሕዝብ አለኝታ በመሆን ጠላትን ያባረሩ፣ ነጻነትን ያስመለሱ አርበኞች ሀገር ነው። ለንጉሠነገስቱ መመለስ ከጎጃም አርበኞች ጋር በመሆን የባለትልቁ ድርሻ ተካፋዮ ናቸው። ባጭሩ በእምነት፣ በሀገር ፍቅር፣ እና በማንነት አንድ እና ልዩነት ያልነበራቸው ማለት ነው። ለዚያም ነበር የስራቸው (የአርበኝነቱ ተጋድሎ የተሳካላቸው)። ዛሬ የነዚያ ጀግኖች ምድር እየታመሰች ነው። የውጭ ጠላት የለኮሰው ሳይሆን የሀገር ፈልፈላ የጀመረው ጉዳይ ነው። ብዙ ሰው ሕይወት አልፏል። እጅግ የሚያሳዝነው አቅመቢስ እናቶች፣ ሴቶች እና ሕጻናትን የታቀፉ ቀያቸውን ለቀው ጎንደር ከተማ እና በአካባቢ ቀበሌወች ተሰደዋል። ይህን መከራ እና መፈናለቅል የሚጽፈው የለም። እንደልማድ ይታይ ወይንም ግድ ያለመኖር የማህበራዊ ሚዲያው አክቲቪስቶች በሌሎች ወገኖቻችን የሚፈጸም መፈናቀልን ባስተጋቡበት ይህንም ቢመለከቱት ይበልጥ ትኩረት ያገኛል። ለ4 አስርት አመታት ማንም ሳይጮህለት እና ሳያውቅለት ያለቁ የወልቃይት ሕዝብ ዛሬ በቀሪ የጎንደር ሕዝብ እንዲፈጸም አንፍቀድ። አቤት ብሎ መጮህ፣ ከፍ አርጎ ድምጽን ማሰማት የወገን ሕይወትን መፈናቀልን እንዲቆም አጋዥ ነው። ጎንደርን ለመጎብኘት ባጋጠመኝ እድል ያየሁት ይህ የወገኖቻችን የእርስ በእርስ መጨራረስ እና የውስጥ ስደት ከምር ልቤን ነክቶታል።
በአንጻሩ የመንጋ ፖለቲካ አራማጅ እና ለሞቀው ዘፋኝ የመሆን አክቲቪስትነት ዋጋ የለውም። እነእከሌን አትናገሩ ብሎ አፋችንን በእጅ እንድንጨብጥ የሚፈልጉ መባዛት አላማ ሊያስቀይር አይገባም። ለጎንደር ሕዝብ ያለኝ የግል ፍቅር ጎንደሬ ሆኘ አይደለም። ግን በክፉቀን ስለማውቀው እና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋሻ እና መከታ ስለነበረ ነው።፡
ይህን የዛሬ እፎይታ በፋናወጊነት ነፍጠኛ እየተባለም በቀለ ገርባ ይፈታ ብሎ በዚያች ክፉ ቀን መፈክር ይዞ የወጣ ሕዝብ ነው። የኦሮሞ ደም ደሜነው ያለ ሕዝብ ነው። ስለኢትዮጵያዊነት ከፍ አርጎ ሰንደቁን ያውለበለበ በአደባባይ የኢትዮጵያዊነት ነባር ሰንደቅ የሰቀለ ነው። እናም ዛሬ ሁሉም ከጎኑ ሊቆም ይገባል። በውስጥ በሌለ ልዩነት የተነሳሳው እሳት የሀገር ጠንቅ መሆኑን ሊስተዋል ያለዚህ ሕዝብ የሀገር ደጀንነት ያለመኖሩን ማወቅ። ለሁሉም ጥልቅ የሆነ እውቀት በውስጥ ገብቸ እንደዚያ የወጣትነት ዘመኔ የታቹን ሕዝብ አይቸ ዘርዘር አርጌ ባቀርበው ምን ያህል ደስ ባለኝ። ግን እኔም ከ38 አመታት በኋላ ሀገሬን በመርገጤ ብዙ የአካል እና የግዜ ጉድለት ስለአለ አለመቻሌ ያሳዝነኛል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
