February 26, 2019
አዙሪት
ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች። ችግሮቿ መጠነ ሰፊ፣ አድማስ ተሻጋሪ፣ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ የመጣ፣ ውስብስብና አታካች ነው። ይሄ አስተሳስብ የሃገራቸው ህልውና እና መፃይ እጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው እጅግ የበርካታ ወገኖች ደጋግመው የሚናገሩለት ጉዳይ ነው። መጣ ከተባለው ለውጥና ነፃነት ባሻገር፣ ኢትዮጵያን እንደመን አፅንተን እንደ ሃገር እናስቀጥላት የሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት የምስንሰጥበት ወቅት አሁን ነው። እንደ ህዝብ ምን አይነት ሃገር እንድትኖረን እንደምንፈልግ እንኳን ገና ተስማምተን አንድ ገፅ ላይ ለመነብብ አልበቃንም። ውሻል ስርአት አበጅቶ ሃገር እየተባላ፣ ህዝብ እርስ በርሱ አይንህን ለአፈር የሚባባልበት ዘመን ላይ አድርሶን ሲያበቃ መቄሌ ተሸሽጎ ፌደራላዊ ስራቱ አደጋ ላይ ወድቋል እያለ አደጋ ላይ በጣላት ሃገር ላይ ይዘባበታል፣ የሃያ ሰባቱ አስገባሪ ህውሃት። ከሁካታዉ እና ከድል አድራጊነት የስካር የዞረ ድምር ሆሆታ ውስጥ ያልወጣው አዲሱ አገዛዝ ፊዴራሊዝሙ ለድርድር አይቅርብም እያለ ይፎከራል። የትኛው ፌዴራሊዝም? የዘውግ ፌደራሊዝሙ? እኮ ይሄ የሃገሪቱን ጥርስ አራግፎ በድድ በቻ ያስቀራት? ህዝብን ከህዝብ እያባላ፣ ሃገር እያጫረሰ ያለው ፌዴራሊዝም ነው ለድርደር የማይቀርበው? በዚሁ ቀጥለን ሳንደራደር፣ ማሻሻያ ሳናበጅ የት ለመድርስ? ለመፈርስ ወይስ ስንዳማ፣ እንደ ተባለን እድሜ ዘላለማችንን ልቀጥል?
አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍርሃት፣ ከይሉኝንታ፣ ከአድር ባይነት ለአፍታ ገለል ብለን፣ ይህችን ሃገር እንደምን እንደ ሃገር አንድ አድርገን እናስቀጥላት ብለን በአፅኖት የምናስብበት ጊዜ መቷል። ጥሪው ላሸናፊዎቹ ነው። ምርኮ የበዛለትም፣ ድል አድራጊም ዘመኑን ሙሉ አሸነፍኩ ብሎ ዳንኪራ ሲረግጥ አይኖርም። ስረአትን በስርአት መተካት፣ ቡድኖችን አባረን በቡድኖችን ለመትከል እንደሆነ እንግዳ አይደለንም። እናም የቡድኖቹ ድል አድራጊነ የአንድ ሰሞን ሁነት፣ ለቀጣይ ስራ ግብአት የሚሰብስበት እንጂ በራሱ ግብ አንዳይደለ በርካቶች የሚረዱት ቁም ነገር ነው። ተደራድሮ፣ ያለውን አሻሽሎ፣ ሁሉ ባይደስት እንኳን አብዛኛው ህዝብ የሚቀበለው ሃገር፣ ስርአት መገንባት ሃላፊነቱ የሁላችንም መሆኑ ስለምን ተዘነጋን?
ያለፈን ስርአት አብዝቶ መርገም፣ አዘውትሮ መክሰስ፣ በረባ ባረባው ማውገዝ፣ በየአጋጣሚው ማበሻቀጥ የተለመደ ፖልቲካዊ ባህላችን ሆኖ ከተላበስነው ዝንተ አለም ተቆጥሯል። ነገስታቱ እርስ በእርስ ሲጠላለፉና ሲሻሻጡ ለመኖራቸው ታሪክን የኋሊት መለስ ብሎ መጎብኘቱ በቂ አስረጂ ያስገኛል። የጥንቶቹ ገዥዎች ከሃገር ወዳድነታቸዉ በመለስ ለትውልድ ሲያወርሱት የኖሩት “ተረፈ ባህላቸው” በአንዱ መቃብር ላይ የመጪውን ስርአት ዙፋን ማነፅ፣ በቀድመው ሞት የተከታዩን ትንሳኤ ማወጅ ሆኖ ኖሯል። ከተጣባን የአሳዳጅ እና ተሳዳጅ፣ የገዳይና ፎካሪ የፖለቲካ ባህላችን መናጠፍ ተስኖን በአዙሪት ውስጥ ቅጥለናል። ለዚህም ነው ሰርክ ገንቢ፣ ሰርክ አፍራሽ ሆነን የቀረነው። ይሄ ነው የሚባል ዘመን ተሻጋሪ ተቋማዊ ቁመና አተን፣ እንደ ላስቲክ ውስጥ፣ ውሃ ከመጣው ከሄደው ገዥ ጋር ስንዋልል ለመኖራችን፣ ለመጣው ለሄደው ስርአት ስንቀነጠስ ስንበጠስ መቀጠላችን።
ደርግ በአቢዮት ስም ወደ ስልጣን ቢመጣ የአፄውን ስርአት አስራ ሰባት አመታት በሙሉ ጭራቅ አድርጎ በመሳል፣ ከገጠር እስከተማ ሰልፍ በማስረገጥ፣ ፊውዳል፣ አድሃሪ፣ ጨቋኝ፣ በዝባዥ ሌላም ሌላም ስያሜ በምስጠትና በማሰጠት የሰራው ፕርፖጋንዳ፣ ዘላለማዊ አላደርገውም። ከፊውዳሉ ዘመን በከፋ እንጂ የተሻለ ፀሃይ ለህዝቡ አልወጣለትም። መከረኛው የኢትዮጵያ ህዝብም ከምጡ ወደ ድጡ ብሎ ከመተረትም አልተረፈም። ደርግ ያን ሁሉ ውርጅብኝ በአፄው ስርአት ላይ ሲያዘንብ የነበረው የተሰራ መልካም ነገር ስላልነበር፣ አልያም ሁሉም ነገር ጨለማ ሆኖ ስለኖረ አይደለም። ይልቁንስ የተገነባው የፖለቲካ አስተምሮት፣ አንዱ አንዱን ጥሎ የመፎከር፣ የማዋረድና የማንኳሰስ፣ ዋጋ የማሳጣት ስለነበር ነበር። በራሱም ጥፋት ይሆን በሌሎች ሃሎች የተባበረ ግፊት፣ የደርግ መንግስት ተንኮታኩቶ ሲወድቅ፣ ወያኔ በተራው ደርግን እስኪታክተን ለሃያ ሰባት አመት ሙሉ በተመሳሳይ መንገድ ሊያውም አስር ተጨማሪ አመት ታክሎበት፣ ሲያወግዝ፣ ጭራቅ አድርጎ ስሎ መጣብህ ብሎ ሲያስፈራራ፣ “ነፈሰ በላው” ስርአት ሲለን ኖረ። እራሱን ነፈሰ በላ ከመባል ባያተርፈውም። በተለይ ህውሃት ዛሬም ድረስ የትግራይን ህዝብን እርስት ጉልቱ አድርጎ እንዳሻው የሚያዝበት ደርግ ተመልሶ ይመጣብሃል በሚል ማስፈራርያ እንደህነ ይታወቃል። የጊዜ እንጂ የሰው ጀና የለውም እንዲባል፣ ወያኔም የፈፀመውን በደል፣ የሰራውን ግፍ፣ ያደረሰውን መከራ ሁሉ በሃገር እና በውገን ላይ ሲያፈስ ኖሮ ጊዜው ደርሶ ቢያንስ ከፊት ገፅ ላይ ገልል ብሏል። አኛም እንደተለመደው በተገኘው መደረክና፣ አጋጣሚ ሁሉ ወያኔን በማውገዝና በመስደብ ተጠምድን ድፍን አንድ አመት ሊሞላን ጥቂት ሳምንታት ቀርተውናል። የተለምደው ውግዘታችን እና ክሳችን እስከመቼ እንደሚያከርምን አይታወቅም። ዘላለማዊ ገዥ ሃይል የለም እና አሁን ያውካካንለት፣ የጮህንለት፣ ያጨበጨብንለት ስርአተ መንግስትም ያልፍና የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ የምንልበት ዘምን ለመምጣቱ ነጋሪ ለምሆን ነብይም ጠንቋይም መሆን አያሻም።
ዛሬ ፍንጠዝያ ላይ ነን። ሁሉም ወያኔን ረጋሚ፣ ጥፋትና በደል አመዣኪ ሆኗል። በመሃል ኢትዮጵያ ተረስታለች። ከኖረው፣ ካረጀና ካፈጀው፣ የሄደን መውቀስ የመጣን ማወድስ፣ ሙሾና ማውረድ፣ መወድስ ማቅረብ መላቀቅ ተስኖን ባለንበት እንረግጣለን። ትንሽ ትንፋሽ ሰብስበን ወደ ነገ እንመልከት ያልንም እንደሆነ፣ የሚጠብቀን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ የለም አትፈርስም በሚል መቋመርና እጣ መጣጣል ውስጥ መጠመድን ነው። ፌደራል ስርአት አወቃቀሩ እንዳጠፋን፣ ይዞን ገደል እየወረደ እንዳለ እየታውቀ ጭምር፣ ለድርደር የሚቀርብ አይደለም እንባላለን። ምን ስንሆን ነው የምንደራደረው? ለውጥ የተባለውስ ሂደት የተሻለ ሃገራዊ አወቃቀር፣ የተሻለ መንግስታዊ ስርአት፣ የተሻለ ነገን ሊያሳየን ካልፈቀደ፣ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ውይን ማንቆርቆራችን፣ ከመፈንዳት፣ ከመተርተር፣ ከመበተን ካላተረፈን ታዲያ ምን ሊበጀን? የመሳ መሳማ ምን አለን ያለፍው እንድንልስ ለምን እንደረጋለን? ቀድሞ ነገር ስለሚሻለን ስርአት መቼ መነጋገር ጀመርን? መነጋገር፣ መመካከር ሳይኖር፣ ሃሳብ ለሃሳብ ሳንለዋውጥ፣ አስቀድሞ ነገር ለድርድድር አይቀርብምን ምን አመጣው። መቼ ጭፈራችንን ጨረስን? ህዝብ እኮ ዛሬም ወያኔ አደረሰብኝ ያለውን ግፍ እየረገመ፣ እያወገዘ እንጂ ለነገ ምን ይሻለኛል ወደ ሚለው ገና መቼ መጣና ነው፣ ፌዴራላዊ ስርአቱ የሚጠየቀው በኔ መቃብር ላይ ነው የሚባለው። ይገባናል የኦዴፓ መለስ ለህውሃት ሰሞነኛ ማስፈራርያ እንደሆነም። ሆኖም ስለ ቀጣዩ ስርአት ማውራት አልጀመርንም። ሊህቅ የተባለው የህበረተሰብ አካል፣ ለተሻለ ነገ ምን እንዝይድ፣ ለመጪው ትውልድ ምን መልካም ነገር እናውርስ ከሚለው ይልቅ፣ የተሰራን ሃገር በመናጠቅ ላይ ያዘነበለ ነው የሚመስለው እስካሁን ባለው ሂደት። እንትን ይሚባለው ከተማ የኔ ብቻ ነው፣ እንትንን ተቀምተናል እናስመልስ፣ ጫጫታው፣ እንኪያ ሰላምታው ብቻ ነው የቀጠለው። አፍታ ወስደን መቼ ዛሬያችንን ገንብተን፣ ነጋችንን የተሻለ እናድርግ ወደ ሚለው መጣን? ከውዳሴውም፣ ከወቀሳዉም፣ መለስ ብለን እንደምን፣ የፀና አለት ላይ የቆመች፣ ንፋስ የማያንገዳግዳት፣ ጎርፍ የማይሸረሽራት፣ የጋራ ሃገር፣ እንዲኖረን እንደምን እንትጋ የሚለው የጋራ ሃላፊነታችን መሆን ይኖርበታል። ወቅቱ ቢረፍድም አሁን ነው።
ከሚሻለን እንደር
የብዙ ዘመን መንግስታዊ ስርአት ግንባታ ቀደምት ታሪክ አለን የምንል፣ በነፃነት ኮርተን በመኖር ለተቀረው ጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆነናል እያልን፣ ትንሽ ሰጠት ስናረግም ከአለም ህዝብ ለየት ያልን ነን በማለት የምንመካ፣ እኛ ኢትዮጵያን፣ የትላንቱን እያነሳን ከመሸለል በመለስ፣ ነገ እንኳን ሃገር እንደሚኖረን ፈፀሞ እርግጠኛ መሆን ያልቻልንም። ሃገራችን ከነገ ዛሬ አበቃላት እያልን በስጋትና በፍርሃት የምንኖር ጉዶች ነን። የትኛው የፖለቲካ ርዕዮት፣ ምን አይነት የመንግስት አወቃቀር እንደሚበጀን ተስማምተን ያላበቃን፣ ሰርክ አዲስ ሆነን፣ አለባብሰን አርሰን አረም ዋጋ የሚስከፍለን ህዝቦች ሆነናል። የኢትዮጵያን ምድረ ቀድምትነት፣ የቃል ኪዳን ሃገር መሆን፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃንት ያለን ነን ማለት፣ ምንትስ ምንትስ የምንለው ሁሉ ለነገ ሃገራዊ አንድነታችን ዋስትና መቼ ሆነን እና? ተወደደም ተጠላ ስለቀደመ ዘመን ታሪካችን አብዝተን፣ አስውበን ማውራታችን ለመጪው ዘመን ዋስትና ሊሆነን አይችልም። ስለቀድመ ታሪካችንም አብዝትን ማልቀሳችን፣ መቃብር ቆፍርን አፅም መርገማችንም ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመሸጋገር ማሾ አልሆንልንም። ከታሪካችን ብንማር፣ በአግባቡ ልንጠቅምበት ብንችል፣ ነገን ለማበጀት እርሾ፣ ሩቅ ለመጓዝ ስንቅ ሊሆነን ይችል ነበር። ጥያቄው ታሪካችን ከመነታረኪያንት ተርፎ እስከ ዛሬ ምን ያህል ጠቅሞንል የሚለው ነው።
ስለ ሃገራዊ ስርአት ግንባታ ሲወራ፣ ዙራያ ጠቅስ የሆኑ በርካታ ሁነቶች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ቀድሞ ነገር ያለንበት አከባቢ ምን ይመስላል ብለን መጠየቁ የተገባ ነው። ማንም እየተነሳ ሰፈሩን፣ ክልሉን ምድረ ገነት ሊያስመስል ቢሞክርም፣ እውነታው ግን ሌላ ነው። የምንዘነጋው ነገር ግን ከልባችን ልንፅፈው የሚገባው እውነታ የሰፈርነው ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት መካከል ነው። ሊያውም አለም የሚያቀን በምንማቅቅበት የከፋ ድህነት እና ችጋር መሆኑ ሳይዘነጋ። የኛዋን ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀጠናችን እጅግ ደካማ የተባሉ ሃገራት (ስቴትስ)፣ ወይም ውጥነት የሌላቸው ስቴትስ (absence of coherent states) የተከማቹበት፣ ሲፈርሱ ሲሰሩ የሚኖርቡት፣ ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት የበረታበት የመከራ ምድር ነው ያለንበት ሰቅ። የግርጌ ማስታወሻ ፖለቲካ እንደ መውደዳችን የፖለቲካ እሳቤዎቻችንን የሚገልፅ የዳበረ የፖለቲካ ቋንቋ አጠቃቀም እንኳን የለንም። ለዚህም ሲባል ነው state የሚለውን እሳቤ የሚገልጥ አቻ ትርጉም በማጣት የእንጊሊዘኛውን ቃል ለመጠቀም መገዳችን፣ ያው ፌዴራሊዝም፣ ዴሞክራሲ እንደምንለው።
ኢትዮጵያ ሃገር በመሆን ታሪኳ ውስጥ የንበሩትን በርካታ ውጣ ውረዶች አንዳሉ ሆነው በአንፃራዊንት ከወደቁት በላይ፣ ለመውደቅ ከሚንገዳገዱት አቻ ሆኗ ለመቀጠላ ሊመረመሩ፣ ሊነቅሱና ሊተቹ የሚችሉ አያሌ ሁነቶች አሉ። የአረቡ የፀደይ አቢዮት ከፈነዳበት ወዲህ እንኳን ሙሉ በሙሉ የፈርሱ አጎራብች ሃገሮች በዙሪያችን አሉ። እነኚህ በቅርብ አመታት በሃገርነት የምናውቃቸው፣ አንዳንዶቹ እንደውም የሃገራችን ሰዎች ተሰደው የሚሄዱባቸው የነበሩ ናችው። የመን፣ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ ኢራቅ የመሳሰሉት ራቅ ካሉት፣ ድንበር የምንጋራቸው ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የመሳሠሉት ከውደቁ ሰነባበቱ። ጣጣቸው ለኛም ተርፏል። ኢትዮጵያ በበርካታ አህዛዊ የሁነት መለኪያ ኢንዴክሶች ለመፈርከሽ አንድ ሃሙስ የቀራት ለመሆኗ ነጋሪም ምስክር አያሻንም። የተጨናጐለች ሃገር ይዘን በዚያ ላይ እንፎከራለን። እንበተናለን፣ እንቀደዳለን እንሰፋለን የሚሉን በርከተዋል። የፌደራሉ ስርአት አደጋ ላይ ወድቋል፣ የለም የፌደራል ስርአቱ ለደርደር አይቀርብም ይባልልናል። ቀድሞ ነገር መቼ ለአቅመ ሃገርነት የሚያበቃ ቁመና ያለው መንግስትና የፖለቲካ ስርአት ኖሮን ነው ይሄ ሁላ ፉከራ?
ለአፍታ የሃገራችንን እጣ ፈንታ እናስብ። ለምን ዘመናዊ ስቴት መንገንባት አልሳካልን አለ፣ ለምን ድሃ ሆነን ቀረን፣ ለምን እድሜ ዘላለማችንን እንደተጋደልን እንኖራለን? ለመን አሳዳጅ እና ተሳዳጅ ሆንን? ለምን ሲባል ነቃይ አፈናቃይ፣ አፍራሽ ደምሳሽ መሆን ዝናችን ሆነ? ምንስ ጎደልን ብለን ካልጠየቅን፣ ካልመረመርን፣ ስለምፍትሄው ካልተንጋገርን፣ መላ እንምንታ ብለን ካልተነሳን፣ ወደድንም ጠላን እንደ ጎረቤቶቻችን ታሪክ ሆንን ለመቅረት ያለን እድል ፈንታ ከግምትም በላይ ነው።
ፊውዳሊዝም የተባለው ስርአተ ማህበር አልበጀንም በሚል ገፊ ምክንያት፣ ለለውጥ የተነሳሱ አብዮተኞች ከንግስታት አገዛዝ ወደ ሪፐብልክነት ሃገሪቱን ቢያሸጋግራት፣ አህዳዊ የመንግስት ስርአት ጨቋኝ ነው በሚል አመንክዮ የጎሳ ፌደራሊዝም ብንተክል ይሻላል ብለው ፌደራሊስቶቹ በክልል ቢሸነሽኑን፣ ኢትዮጵያን እስከ አሁን በተጓዘችባቸው ለውጦችና አብዮቶች የሚሻላትን፣ መካከለኛውን መንገድ ለመያዝ አልቻለችም። በዚህ ሁሉ ሙከራችን ከመከራ ልንታደጋት፣ ከችግሯ አላቀን፣ ከአደጋ ሰቅ ውስጥ ልናወጣት ፈፅሞ አልተቻለንም። ዛሬም ሞት፣ ዛሬም ስደት፣ ዛሬም መፈናቀል፣ ጥላቻና ዛቻ አልቀረም። እንደውም እየባሰበት እንደሄደ የሚያመለክቱ በርካታ እውነታዎች መሬት ላይ እየተካሄዱ ነው። ክልል ብለን የፈጠራቸው የአስተዳደር መዋቅሮች ብዝሃነትን የሚፃርሩ (against heterogeneity) የሆኑ፣ በአንፃሩ ደግሞ በየአከባቢው አንድ አይነትነት (homogeneous) የሆኑ ማህበረሰብን ለፈጠር በሚደረገው ሙከራ የኛ አይደለም ያሉትን ህዝብ በጅምላ የሚያፈናቅሉ እና የሚያሳድዱ ናቸው። ፌደራሊዝም የሚባለውም እሳቤ ለሃገሪቱ ክሽፈትን፣ ለህዝቡም ሰቆቃን እና መከራን ነው ያተረፈለት። በርግጥ ከዚህ ሁሉ ሂደት ያተረፉ የለም ማለትም እንዳይደለ ልብ ሊባል ይገበዋል።
መሰረታዊ ችግራችን ምንድን ነው የሚለው ሃሳብ ላይ ትኩረት ሰተን ምክረ ሃሳብ ከማቅረብ እና እውነተኛ ጉድለታችንን ለመሙላት ሃይላችንን ከማዋል ይልቅ፣ ወቅታዊና እለታዊ በሆኑ ተግዳሮቶች ላይ አተኩረን ዘመናችንን እንፈጃለን። ለዋናው ጉዳይ መልስ ሳንሰጥ የቱንም ያህል በሌሎች ጉዳዮች ላይ ብንታትር፣ በከንቱ እንባዣለን። በስካሁኑ ጉዟችን የሚገባንን፣ የሚበጀንን ፖለቲካዊ ስርአት (political order) በተገቢው መንገድ መትከል አልቻልንም። ፖለቲካዊ ስርአቱን ባግባቡ አስቀድመን ሳናቆም፣ ፌዴራሊዝም ብንለው አህዳዊ፣ ዴሞክራሲ ብለን የይስሙላ ምርጫ ብናካሂድ፣ ልማታዊ መንግስት ብንለው ኒዮ ሊብራሊዝም፣ የሳትነው ጉዳይ አለ። እሱን ሳንመልስ የፈለገ ብንታትር፣ ካርታ እንደጠፋበት መርከብ ተንከራተን ስናበቃ መጨርሻችን መስምጥ ይሆናል። በአስቸኳይ ወደ መሳያ ተረጴዛው ተመልሰን፣ የገደፍነውን፣ የሳትነውን አብይ ጉዳይ መርምረን ልናገኘው ይገባል። እሱን ማድረግ ካልቻልን የውደፊት ጉዟችን ተወደደም ተጠላም ወደ በርባርስ ነው።
ሶስቱ ምሰሶዎች
ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁር ፍራንሲስ ፉኪያማ Political Order and Political Decay በተባለው ዝነኛ መፀሃፉ በሚገባ ዘርዝሮ እንደሚያስረዳው የትኛውም ሃገር የተረጋጋ የፖለቲካ ስርአት መስርቶ ወዲፊት ለመጓዝ እንዲችል ሶስት መሰረታዊ የፖልቲካ መዋቅሮች ላይ አጥብቀው መስራት እንዳለባቸው አፅኖት ሰቶ ይመክራል። በዚሁ አግባብ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር አንድ አድርጎ ለማስቀጠል የሚፈልግ የትኛውም የፖልቲካ ሃይል፣ የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ መስራት ግድ ይለዋል የሚል እኔም ፅኑ እምነት አለኝ።
1ኛ. ዘመናዊ ስቴት (modern state) መስራት:- በዚህ አግባብ “ዘመናዊ” የሚለው አገላለፅ የጊዜን ቅርበት ሳይሆን ሁኔታና ይዘትን የሚያመለክት ነው። በመሰረቱ ቻይና የአለማችን የመጀመራውን ዘመናዊ የስቴት መዋቅርን ለማበጀት የቻለችው ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ በሶስተኛው መቶ ክፍለዘምን፣ ሲሆን የአውሮፓ ሃገራት ዘመናዊ የስቴት ስርአትን ለመመስረት ሙከራ የጀመሩት ከቻይና 18 ያህል ክፍለ ዘመኖችን ዘግየተው ነበር። ጥንተ የሃገርነት ታሪክ አለን የምንል እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ ዘመናዊ የስቴት ስርአትን መገንባት አልቻልንም። የኛን ሃገር የስቴት አይነት ከመዘርዘራችን በፊት አስቀድመን ዘመናዊ ስቴት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቂው ጀርመናዊ ፈላስፋና ሶሲዮሎጂ ሙሁር ማክስ ዌበር ዘመናዊ ስቴት ለሚለው እሳቤ የስጠው ብይን ብዙ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎችን የሚያስማማ ነው። በዌበር ብያኔ ዘመናዊ ስቴት የሚባለው ተቋም እንደ ተቋም በአንድ ሏላዊ የግዛት ወስን ውስጥ የሃይል የመጠቀም ብቸኛ የሆነ ወይንም ሞኖፕሊ የሆነ ፍቃድ ያልው፣ ይሄውም ተቋም በህዝብ ቅቡሉነት ያገኘና እና ህጋዊ የሆነ መሆን ይኖርበታል። ይሄ ትርጓሜ ዘመናዊ ስቴትን ከሊሎች ማንኛውም አይነት መሃበራዊ ስብስቦች የሚለየበትን ቁልፍ ባህርይ ይሚያስቀምጥ ሲሆን፣ የሄውም ሃይል የመጠቅም አቅሙን የሚያረጋግጥ ነገር ግን ደግሞ የህዝብ ቅቡሉነት ያለው (have legitimate and legal authority) መሆን እንዳለበት ያስረዳል። ስለስቴት ስናወራ ስለ ሃይል ማናገራችን ነው። ማንም ሰው የሃገሪቱን ህግ ሲትላለፍ ይዞ የማሰርና ህግን የማስከብር ሃላፊነት የተሰጠው ነው። ሌሎች ተቋምት ይህን ማድረግ አይችሉም። በዚህ ሚዛን ሃገራችን አሁን ያለችበትን ሁነት እንገምግም። ህጋዊ ሆኖ የሃይል ሞኖፖሊን አስጠብቆ የቀጠለ ስቴት ኢትዮጵያውስጥ አለ? መልሱ ግልፅና ቀጥታ ነው።
ዘመናዊ ስቴት የሚባለውን ተቋም፣ የለውጥ የተባለው ሃይል ወደ ስልጣን ስለመጣ አይደለም ያጣነው። ቀድሞ ነገር ዘመናዊ ስቴት የሚባል ተቋም ገንብተን አናውቅም። ታዲያ ኢትዮጵያ ምን አይነት ስቴት ሆና ኖረች ከትባለ መልሱ ሁልት ነው። አንድም የርስት ስቴተ (patrimonial state) ሲቀጥልም፣ የፖሊትካ ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት ኒዮ ርስት ስቴት (neo patrimonial state) ኖሯት ነው እስከ ዛሬ የዘለቀችው። ይህን ጉዳይ ጉዳይ የበለጠ እንዳሰራድ ይፈቀድልኝ።
ኢትዮጵያ እስከ 1966ቱ የአብዮት ዋዜማ ድረስ የነብበረችው የርስት ስቴት ስርአት ውስጥ ነው። ነገስታቱ፣ ሞኳንንቱ፣ መሳፍንቱ እና ሹሞቻቸው ሃግሪቱን እንደገዛ የግል ንብረታቸው የሚያበዩት ስርአት ። ኑጉሱ ውይንም ንግስቲቱ፣ አልያም የሱልጣኔቱ እና ኪንግደሙ ባለ አባት ሆኖ ግዛቴ ባለው መሬትና ህዝብ ላይ እንዳሻው የሚያዝበት፣ ልጁን ሲድር አንዱን አውራጃ ከነ ህዝቡ በስጦታ መልክ ለሙሽራው፣ ለሙሺሪት የሚሸልምበት፣ ሃገር የግል ሃብት የሆነችበት ዘመን ነበር። ማን ይጠይቀዋል። ሃገረ ግዛቱ ከዘር ማንዘሩ እየተዋራረሰ ያኖረው ርስተ ጉሉቱ ነውና። አብዮት መቶ ያንን ስርአት እስኪንደው የነበረ እውነታ ይሄው ነው። በተሪካችን ዘመናዊ ስቴት ለመስረት ሙከራ ያደረገው የደርግ መንግስት ነበር፣ መሬትን ከግል ይዞታነት ወደ ወል ንብረትንት በመለወጥ፣ ጭሰኛና አራሹን ከባለ አባቶች ጭብጥ ውስጥ ፈልቅቆ ነፃ በማውጣት። ደርግ ዘመናዊ ስቴት የመግንባት ህልሙ ባጭሩ ተቀጨ በሚታውቅ ምክንያት።
የዘመናዊ ስቴት ምስረታ ፕሮጀክቱ ተጨናግፎ በኒዮ ርስትት ስቴት የተተካው ወያኔ ኢህዴግ ወደ ስልጥን ሲመጣ ነው። በሚያስገርም መልኩ የባለአባቱ ዘመን፣ እራሳቸውን በጎሳና በቋንቋ ባደራጁ ጎበዛዝት ተተክቶ ሃግሪቱ የዘረኞቹ ርስት ጉልት ሆነች (re-patrimonialism) መሆኑ ነው። እነኚ ሃይሎች ወደ ስልጣን የመጡበት ዋንኛ ምክንያት እራሳቸውን በሃብት ለማክበር ነው። ሃገሪቱን ፌደራሊዝም በሚል ፈሊጥ በቋንቋና በጎሳ ሸንሽነው ሲያበቁ፣ ህዝብን ከህዝብ እያባሉ እነርሱ ግን ወደ ስልጣን የመጡበትን አላማ በማሳካት ላይ ይገኛሉ። ሃገርና ህዝብን መዝረፍ፣ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በሃብት ማደርጀት። ፖለቲካዊ ስልጣናቸው የሃብት ምንጫቸው ሆኖ ዝልቋል። መሬት ዘርፎ፣ ሃገርን ብቁማ አርዶ፣ ሃገርን በእዳ አሲዞ፣ የደሃን መቀንት አስፈትቶ፣ ዜጎችን ከመሬታቸው ነቅሎ ያልከበረ፣ እጁ በስርቆትና በሙስና ያልተጨማልቀ የኢህዴግ ባለስልጣ አንድስ እንኳን አለ ቢባል የሚታመን አሆንም። ሁሉም ባንድም በሌላም መልኩ እራሳቸውን ወይም ቤተሰባቸውን በሃብት አንበሽብሸዋል። ልዩነቱ ሃብቱ ፊት ለፊት የመታየቱ እና ያለመታየቱ ጉዳይ ብቻ ነው። ግመል የሰረቀም፣ መርፌ የሰረቀም ሌባ ያው ሌባ መሆኑ ግን መረሳት የለበትም።
ዘመናዊ ስቴት አስፈላጊነቱ ሃገርና ገዥዎችን መነጠል ነው። ዘመናዊ ስቴቱ ሁሉንም ዜጎች በዜግነታቸው እኩል የሚመለከታቸው፣ ጎሳዬ ሃገር ይገዛል እና እኔ የተሻልኩ ዘር ነኝ ሳይባል፣ ዘመዴ ባለ ስልጣን ነው እና ድንዳሻኝ እሽኮለሌ እላለሁ ስይል ሁሉም እኩል በዜግነቸው የሚኖሩበት ሃገር ለማበጀት የሚሰራ ተቋም ነው። ዛሬ በቋንቋና በዘር የተሽነሽኑት ክልሎች ዘጎችን ፈፀሞ በእኩልነት በማይያበት ሁኔታ የለም። የኒዮ ርስት ስርአት ደጀቶ በወጣብት ሃገር፣ የህዝብና የግል ንብረት ድንብሩ የቱ ጋር እንደሆነ ባለ ስልጣናቱ በውል ለይተው አያውቁም፣ ማውቅም አፈልጉም። ግንባታዎች የሚሰወሩበት፣ መርክብና አውሮፕላን በግለሰቦች የሚዘረፉበት ሃገር፣ የጠገበው የዘረፉት ሲያስተፋቸው ቆሻሽኋል፣ በስብሳችኋል ተብለው ሲገፉ፣ የራበው ዘራፊ በተራው በተተካበት ሁኔታ ሃገር አለን ተብሎ፣ በዚህ እደራደራለሁ በዚያ አልደረራድርም ይባላል።
ዛሬ ዛሬ ፍንትው እያለ የመጣው እውነታ የለውጥ አራማጅ ተብየው ቡድን ከምር የዴሞራሲ፣ የሰባዊ መብት፣ የእኩሉነት፣ የዚጎች ክብር አሳስቦት ሳይሆን፣ ሌሎቹ ሲዘርፉ እና ለብቻቸው ሲከብሩ እኛስ ልምን የድርሻችንን እናጣለን የሚል ቁጭት ይዟቸ የሚያስመስል ምልክቶች እየታየ ነው። ባይሆን ኖሮ የለውጡ መሪዎች ስልጣን ላይ በወጡ አመት ሳይሞላቸው የቀደምቶቻቸውን ስራ ሲደግሙት ባላየን። በህገ መንግስቱ፣ በፌደራል ስራቱ አንደራደርም እያሉ የልዩ መበት ተከራካሪዎች ባልሆኑ። ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ የኒዮ ርስት ስርአቱ ቀጥሏል።
2ኛ. የህግ የበላይነት (Rule of law): የህግ የበላይነት ልሚለው የህግ እሳቤ በርካታ ማብራሪያ አባሪዎች ታጅቦ የህግ ባለሞያዎች ሲቅርቡ አናውቃልን። በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ዋንኛ የስልጣን ተጋሪዎች የስልጣን ጣሪያና ወሰን የማይገድብ ከሆነ እሱ የህግ የበላይነት ነው ሊባል አይችልም። ህጉ ተራ ዜጎችን፣ ማስገደድ፣ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ብቻ መርጦ ይህን አድርጉ፣ ከዚ ተነሱ፣ ከዚ ተነቀሉ የሚል ብቻ ከሆነ እሱ ትክክለኛ ስያሜው በህግ መግዛት (rule by law) መሆኑ የሚታመን ነው። በሃገራች ታሪክ የህግ የበላይነት የተከበረበትን ዘመን በድፍረት የሚነግረን ቢገኝ ለመደነቅ ዝግጁ እንሁን። የህግ የፍትህ ሃገር ኖርን አያውቅም፣ አሁንም የለንም። ህጉ ላለው ሆነ ቂም ለበቀያ ተብሎ ሲዘፈን ኖረ፣ ዛሬም ህጉ ለባለ ጊዜዎች መሸለያ ከምሆን አላለፈም። ሲቀጥልም ህጉ ዘር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ ዘውግ እና ማንነት እየለዩ መጥቀሚያ እና መጉጃ ከምሆን አለዘለለም። ዛሬ እንኳን ለውጥ መቷል በሚባልበት በዚህ ዘመን፣ ኢፍታሃዊነት እና ኢእርታዊነት ገንግኖ የመንግስት ካድሬዎች እና ባልስለጣኖች የማይደፈሩ፣ የማይጠየቁ ሆነው መቀጠላችው የየለት ውሎ አዳራቸው አስረጂ ይሆናል። ትላንት ሲበድሉት፣ ሲዘርፉትና ሲያንገላቱት የነበረውን ህዝብ በለውጥ ስም ማሊያ ገልብጠው እነእርሱ ግን ከነ ግብራቸው ሳይለወጡ ዛሬም በህግ ስም ህዝቡን ፈዳውን እያበሉት ይገኛሉ። ከሰሞኑ በየአከባቢው የሚታየውና የሚሰማው የሄው ጉድ ነው።
3ኛ.ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት (Democratic acountablity):– ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት የምነለው የምነግስት ሹማምንት ለሾማቸው መንግስት ተጠያቂ ብቻ የሚሆኑብት ሳይሆን ይልቁንም መንግስት እራሱ ለሰፊው ህዝብ የሚጠየቅበት አግባብ ነው። የነፃ እና ፍታዊ፣ የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ተካሂዷል የሚለው መስፈርያ ቢቻ ለአንድ ሃገር ዴሞክራሲያዊንት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም መንግስት ለዜጎቹ ጥያቄዎች አግባብ ያለው ምላሽ በቅቱና በአግባቡ መስጠት ይጠበቅበታል። በዚህም መለኪያ ያየነው እንደሆነ መቼውንም ጊዜ በነፃ እናበፍታዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት አልነበረንም፣ ዛሬም የለነም። ምድብለ ፓርቲ ስርአት ስሙ እንጂ በተግባር መቶ በመቶ ኮሮጆ ገልብጦ ተመርኩ ያለ የአውራ ፓርቲ ስርአት ነው እየገዛን ያለው። መንግስት ተብየውም መቼም ቢሆን ለህዝብ ጥያቂና ፍላጎት ቅድምያ ሰቶ የሚሰራበት ዘመን አልነበረም። ያለፉትን አመታትም ሆነ ዛሬ ድረስ ጎሳውን ለመጥቀም የሚሰራ መንግስት እንጂ ሁሉንም ዜጋ በእኩል አይን አይቶ ሳያዳላ የሚያገለግል፣ ፍትህ የሚያሰፍን፣ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መንግስት አላበጀንም።
ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ምሶሶዎች እንደ ተቋም በጋራ መቆም መቻል፣ ማለትም ሃለኛና ዘመናዊ ስቴት በአንድ በኩል ሲኖር፣ ይሄ ሃይለኛው ስቴት በህግ የበላይነት የሚዳኝ እና በዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት የሚቅነበብ ሲሆን ያን ጊዜ ዘመናዊ ፖለቲካን ማራመድ፣ ስኬታማ ፖሊስን ማስፈፀም ይቻላል። የኛ ሃገር ትልቁ ተዳሮት ይሄው ነው። ከጋሪው ፈረሱ የሚቀድምበት ብሂል። አስቀድምን ፖለቲካዊ ስርአቱን ሳናበጅ፣ የተውሶ ጥብቆ አምጥተን ያለ ልካችን እናጥልቅህ ስንለው ወጥሮን ይከርምና ሲተረተር መበተን። አስቀድሞ አቅም ያለው የደረጀ ስቴት መፍጠር ያስፈልጋል፣ ዜጎቹን በሙሉ፣ ዘር ጎሳ ሳይለይ፣ ከውስጥም ከውጪም ከሚቃጣ የትኛውም አይነት ጥቃት የሚከላከል ጥርስ ያለው ስቴት፣ ለዜጎቹ አስፈላጊውን ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብ የሚችል፣ ዜጎቹን ቤት ንብረታቸውን ደምስሶ ሜዳ ላይ የሚበትን ሲሆን ከወደቁበት አንስቶ አስፈላጊወን መጠለያና መሰል አገልግሎቶችን የሚያቀርብ፣ ህዝቡ በችጋር ሲቀጣ ምን ተዳዬ ብሎ፣ የገዛ ጥሬውን ብቻ እያለመ የማይኖር ስቴት ያስፈልገናል። ስቴት ከዜጎች የሚሰበስብ ታክስን ለግል ጥቅሙ የሚያውል ሳይሆን የተገኘውን ሃብት መልሶ ለህዝብ መገልገያ የሚያበጅ መሆን ይጠበቅበታል። ይሄ የምንለው ዘመናዊ ስቴት በየትኛውም አጋጣሚ በዜጎች ፍቃድ ክበብ ውስጥ ሆኖ የሚቅጥል፣ ለህግ ተጥያቂ መሆኑ የግድ ነው።
የሃገር ተቋማቱ ሲሰሩ ጠንካራ ስቴት ኖሮ በህግ የማይገዛ፣ ለሕግ የበላይንት ቁብ የሚስጥ፣ በዜጎች ፍቃድ ተዳዳሪ ሆኖም ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ፣ ከሶስቱ አንዱ ከተዛነፈ የሚከተለው እውነታ የሚገመት ነው። ጠንካራ ስቴት ካለ ዴሞክራሲ እና የህግ የበላይንነት በቀላሉ አንባገንን ይሆናል። ጨቋኝ እና አፋኝ። ቻይናን፣ ራሺያ እና ሌሎቹም የኢዢያ ሃገራት ግልበትኛ ገዝዥዎች እናስብ። ዜጎቻቸውን ከየትኛውም አይነት ጥቃት ይከላከላሉ፣ አስፈላጊውን አገልግሎት ለዜጎች ያቀርባሉ። የይስሙላ ምርጫም ያካሂዳሉ፣ የገዥዎቹ ስልጣን ግን በህግ የተገደበ፣ በዜጎች ፍቃድ የታጠረ አይደለም። ህንድ፣ አፍጋኒስታን ናጄሪያ ግሪክ እንሂድ፣ በአንፃራዊነት፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሂዳሉዳሉ፣ መድበለ ፓርቲ ስርአት አላቸው፣ ፕሬሱ መንግስትን ይተቻል፣ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሲሸንፍ ስልጣን ያስረክባል። ይሁና ዘመናዊ ስቴት መሆን አልቻሉም። ናጄሪያና አፍጋኒስታን ዜጎቻቸውን ከአሸባሪ ቡድኖች ጥቃት መከላከል አልቻሉም፣ ህንድና ግሪክ የተሻለ ቢሮክራሲ መስርተው ህዝባቸውን በአግባቡ ማስተዳደርና የሚስፈልገውን ማህበራዊ አገልግሎት ለህዝባቸው ማቅረብ አልቻሉም። የበርካታ ሃገራት ከባድ ፈተና ዘመናዊ ስቴት መስርቶ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና የህግ የበላይነት ያለበትን ስርአት ማፀናት ነው።
እኛስ የቱ ጋር እንገኛለን ብለን እንጠይቅ። ዘመናዊ ስቴት ባይኖረንም አንባ ገነኖች መፍጠር ችለናል። እነኚ አንባ ገነን መንግስታት ዜጎቻቸውን ከጥቃት፣ ከችጋር፣ ከእርዛት፣ ከስደት፣ ከመፈናቀል ያላስጣሉ የከሸፉ ግን በራሳቸው፣ ለራሳቸው ጥቅም ሲሆን ጉልበታም ናቸው። አሁንስ? ለውጥ ያለ ይመስለናል። ለውጡ የሰው ይሆን የስርአት አለየለትም። በቀደሙት ሶስት አስር አመታት የይስሙሏ ምርጫ ይካሄዳል፣ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ይሉት አይነት ቀልድ የቀለዳል፣ ለህዝብ ፍላጎት ተገዥ የሆነ መንግስት ሊኖረን አልቻለም። የቢሮክራሲዎቹ ስንኩልነት ዜጎችን ደም እንባ ሲያስነባ ሆኖ ይኖራል። አሁንም ቀጥሏል። ከሁሉም ሳንሆን አለን።
እንዴት ካለንበት የኒዮ ርስት ስቴት ወደ ዘመናዊ ስቴት እንሸጋገር የሚለው ፈታኙ ጥያቄ ነው። ቀድሞ ዴሞክራሲ፣ ቀጥሎ ዘመናዊ ስቴት፣ አለያም ደግሞ አስቀድሞ ዘመናዊ ስቴት በመቀጠል ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንገባ ትብሎ የተቀመጠ አንዳይነት ሞዴል የለም። ሁለቱም በየተራ መምጣት ይችላሉ። አሜሪካንን የመሳሰሉ ሃገራት አስቀድመው ዴሞክራሲ ነበራቸው፣ ዘመናዊ ዴሞክራሲ ባይሆንም። ዘመናዊ ስቴት ግን እስክ 1865 እንደ ኢሮፓውያኑ አቆጣጠር ድረስ አመኢሪካን ሊኖራት አልቻሉም ነበር። በደቡብ እና በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች መካከል የተካሂደውን ጦርነት አብርሃም ሊከን መርቶ የመገንጠል ጥያቄን ከምድሪቱ እስከ ወዲያኛው እስካሶገደው ጊዜ ድረስ የተለያዩ ግዛቶች የየራሳቸውን የርስት ስቴት መስርተው ፌደራል መንግስቱ አቅመ ቢስ ሆኖ ቆይቷል። ከጦርነቱ በኋላ ግን አሜሪካኖች፣ ዘመናዊ ስቴት እና ዘመናዊ ዴሞክራሲን ገንብተው ለበርካቶች ምሳሌ ሆነው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቀጥለዋል። ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ ሃገራትን እንውሰድ። አስቀድመው ዘመናዊ ስቴት መስርተው በሂደት ዴሞክራሲን ገንብተው የተሻለ መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘግበው ህዝባቸውን አበልፀገው የሚዘመርላቸው ሃገራት ከያቅጣጫው ለምሳሌ የመዘዛሉ።
አሁንም አለመሸም። ዘመናዊ ስቴት መስርቶ ዜጎቹን የሚያከብር፣ ደህነነታቸውን የሚጠብቅ፣ አስፈላጊውን ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚውን የሚያበለፅግ ፣ ጥርስ ያለው፣ ጠንካራ፣ የሚፈራ ተቋም ሆኖ በተጓዳኙ ደግሞ የህግ የበላይነትን የሚያከብር፣ ዴሞክራሴያዊ ተጠያቂነት ያለው የፖለቲካ ስርአት መገንባት ይቻላል። ሁሉም ሃገርሮች ሶስቱን ተቋማት በአንድ ጊዜ አልገነቡም። ዴንማርክን የመሰሉ ለፍፁምነት የተጠጋ ዘመናዊ ስቴት መፍጠር ከባድ ነው። በጣም ሃብታም፣ የዳበረ ዴሞክራሲ፣ ህዝቡ ደስተኛ የሆነበት፣ በጣም ዘቅተኛ ሙስና ያለበት ለሃሳባዊ ሃገርነት (ideal state) ማምጣት ከባድ ነው። የሆነው ሆኖ ከዛ በመለስ ባሉት መለኪያዎች ተቋማት ላይ በመስራት የተሻለ ሃግር መራት መቻል ግን ሌሎቹ ችለውበታል፣ እኛ እንሞክረው ሲባል ግን ታአምር መስሎ የሚታሰብበት ምክንያት ሊኖር አይገባም። ዋናው ነገር ሃገር እንዲኖረን ተቋማቱ ይኑሩን። ከዛ በፌደራሊዝሙ ጉዳይ አይደለም በምንም ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር መደራደር የማይቻልብት ምንም ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። አሁን ያለው ስርአት የበሰበሰ (political decay) ያጋጠመው መሆኑን እራሱ ኢህዴግ በአደባባይ ሲነግረን ቆይቷል። የመስበሱንም ውጤት አይተነዋል። የፖለቲካ መበስበስ መቼ እንደሚመጣ ባጭሩ ላስረዳና ላብቃ። ስርአትን የሚያበሰብሱት ሁለት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። አንደኛ ተቋማት ተቸካይ ሲሆኑ፣ ዘመኑን ዋጅተው፣ በውቅታዊ ሁኔታዎች እና ውጤቶች ተመረተው ለአዲሱ ሁኔታና ፍላጎት ለውጥ ለማድረግ ሳይፈልጉ ሲቀሩ ነው። ሁለተኛው የፖለቲካ መሪዎች የህዝብን ፍላጎት ወደጎን ገፍተው ለጠባብ ቡድናቸው ፍላጎት፣ ለጓደኛቸው፣ ለጎሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሃገርን መሰዋት ሲጀምሩ ነው። ያንግዜ ዋልተኝነት (polarization) በተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ቡድኖች መካከል ይሰፍናል። በዋልትኞቹ መሳሳብ የፖለቲካ ስርአቱ በስብሶ ይወድቃል። የአለማችን ታላላቅ ስልጣኔዎች እና አገዛዞች ከጥትን እስከ ከዛሬ ተንኮታክተው የወደቁት ዘመኑን በመዋጀት፣ ለውጥን ለመከተል ባለፍቀዳቸው ነው። የዘውግ ፌደራሊዝም የተባለው የኢሃዴግ “ስልጣኔም” በስብሶ ውጤቱ ህዝብን ከህዝብ በማባላት፣ ሃገር በማመስ ታይቷል። የበሰበሰ ስርአት በተሰጠው እድል ተጠቅሞ ሊታደስ፣ ሊስተካከል፣ አዲስ ስብእና ሊላበስ ካልፈቀደ የወድቃል።
አበቃሁ። ቸር ይቆየን1
ኢትዮጵያ ለዘላለም ታፍራና ተከብራ ትኑር!
