February 26, 2019

እርግጥ ነው፤ የአዲስ አበባንና ዙርያዋን የህዝብ ስርጭት ለመለወጥ እየተሰራ ነው፡፡

የአዲስ አበባንና ዙርያዋን የህዝብ ተዋጽኦ Demography ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን አቶ ለማ መገርሳ በአንደበታቸው ያረጋገጡበትን ይህንን Video ይመልከቱ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት ከወራት በፊት በተካሄደ የጨፌ ኦሮሚያ የእርቅ ህዝባዊ ሸንጎ ላይ አዲስ አበባንና ኦሮሚያን አስመልክቶ ከተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አቶ ለማ መገርሳ ሲመልሱ፣ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ 500 ሺህ የሚሆኑ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን በነበሩበት ቦታ ማስፈር ሲቻል በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥና ዙርያዋ መሬት ሰጥተው እንዳሰፈሯቸው አብራርተዋል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የኦሮሚያ መንግስት ሰራተኞችም እንዲሁ አዲስአበባን ጨምሮ በከተሞች ውስጥ መሬት ተሰጥቷቸው እንዲሰፍሩ መደረጉንም አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ማስረጃ እነአቶ ጃwar መሀመድ በየአደባባዩ እየወጡ የሚደነፉት በምርጫም በፍጥጫም ይዋጣልን ይሉት ቀረርቶ በስልጣን ላይ ያለውም ቡድን ግብ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ ይህም ጉባኤ ሲከናወን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቦታው ነበሩ ብቻ ሳይሆን በፊንፊኔ ጉዳይ ለማ ስለሄደበት እኔ አልደግመውም በማለት ወደሌሎች ርእሰጉዳዮች ተሸጋግረዋል፡፡
ጥያቄዎች፣
1 “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ብሎ ያለ ርዕሰ መስተዳድር፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን” የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር በጋራ በቋንቋ ተከልለው ከስር ከስር “ኢትዮጵያ” በማለታቸው ያከበራቸውንና እምነት የጣለባቸውን ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚገፋና ከአገር ባለቤትነት የሚፍቅ ሸፍጥ መስራት ምን ያህል ያስጉዛቸው ይሆን?
2 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም ጉዳይ “በቦታው የነበርኩ ቢሆንም ሲነገር አልሰማሁም፣ አላውቅም” ሊሉን ይደፍሩ ይሆን?
የለማ ቡድን አባላት የሚከተለው መልእክታችን ይድረሳቸው፡፡
ይሄ ጨዋታ ለአሳዳጊያችሁ ለህወሀትም አልበጀ፡፡ ኢትዮጵያ እንደሆነች ሊጥሏት ያሰቡትን ሁሉ ጥላ የምትነሳ ሀገር ናት፡፡ “እፍ ይሏታል እንጂ አያጠፏትም” እንዲል ገጣሚው፡፡
የ3 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ Video ትርጉም በጽሁፍም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተደረገ የጨፌ ኦሮሚያ የእርቅ ህዝባዊ ሸንጎ (አቶ ለማ መገርሳ ከጉባኤው ተሳታፊዎች አዲስአበባንና ኦሮሚያን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች)፦
አብርሃም አለሙ (ዶክተር) እንደተረጎመው

“የከተማ ፖለቲካን (አርበን ፖለቲክስ) ማጤን አለባችሁ፤ ችላ ልትሉት አይገባም፤” ያላችሁት፣ ትክክል ነው፡፡
የከተማ ፖለቲካ (አርበን ፖለቲክስ) ሊጤን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማእከል (ሴንተር ኦፍ ፖለቲክስ) ከተሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሀገር ፖለቲካ የሚወስነውም ከተማ ነው፤ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተማ ውስጥ ፖለቲካ ማለት አንድ ቁጥር ዲሞግራፊ (የህዝብ ስርጭት) ነው፡፡ እዚያ ላይ አንዱን ወደዚያ መግፋት፣ አንዱን ወደዚህ መጎተት፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን፣ እንደ ኦሮሚያ ብዙ ነገሮች እየሰራን እንዳለን መገንዘብም ያስፈልጋል፤ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የጀመርነው በጣም አበረታች ነው፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ 500፣000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ እንደምንሆነው ሆነን፣ ገፍተንም፣ ምንም ብለን፣ ከዚህም ከዚያም ብለን፣ የገዳ አባቶችንም፣ ሽማግሌዎቻችንንም ይዘን፣ እንደለመድነው እርቅ ፈጥረን፣ አቅፈን፣ ስመን ወደ ነበሩበት ቦታ
ልንመልሳቸው እንችል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መመለስ ይቻል ነበር፤ እኛ ግን ልንመልሳቸው አልፈለግንም፡፡ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ለኦሮሞ አንድነት፣ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ዛሬም ችግር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ገጠር አላሰፈርናቸውም፤ ከተማ ነው ያሰፈርናቸው፣ እነዚህን ሰዎች፣ እወቁ፡፡ በአንድ ጊዜ ከ 500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ አይደለም፡፡ እኒህን ከዚያ የተፈናቀሉትን ሰዎች፣ የዚህን አካባቢ ባህል የማያውቁ ሰዎች፣ በብዙ ነገሮች ከአካባቢው ጋር የማይመሳሰሉ፣ ይቸገራል መችም፣ ይቸገር፤ ዛሬ ችግር
የማያጣው ቢሆንም፣ ከተቸገረም እዚሁ ከተማ ውስጥ ይቸገር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በእግሩ የሚቆምበት መሬት ይኑረው፤ እሱ ቢቸገርም ለልጆቹ የሚሆን ስለሆነ፣ ብለን ህዝባችንንም አስቸግረን ካለን ነገር ላይ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሰፈርናቸው፡፡ አብዛኛው የሀረርጌ ሰዎች ናቸው፣ እወቁ፡፡ ቦርደዴ ማስፈር ይቻል ነበር፤ ምስራቅ ሀረርጌ ልናሰፍራቸው እንችል ነበር፡፡ ማስፈር ትክክል ከሆነ እንዲያውም እዚያው አካባቢ ነበር ማስፈር የሚገባው፤ ያን ባህል ነው የሚያውቀው፣ ያን አየር ነው የሚያውቀው፡፡ ወደማያውቀው ባህል እዚህ አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ አሰፈርነው፡፡ ቢቸገር ቢቸገር ሁለት ዓመት ነው ሊቸገር የሚችለው፤ ከዚያ በኋላ ሰው ሆኖ ይወጣዋል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ላይ ያለው ፋይዳ፣ ሄዶ ሄዶም በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ስለሚፈይድ፡፡
ወጣቱንም ስራ እናስይዛለን ብለን በንግድ ስም፣ በሌላም ነገር ስም ብዙ ነገር ስናደርግ ነበር፤ እናም አብዛኛውን ከተማ ውስጥ አስገባነው፡፡ ወደ ከተማ ስናስገባው የሚኖርበት ቦታ ኖሮት ነው፡፡ ከ500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያን ክልል ሰራተኞች ዘንድሮ መሬት የሰጠናቸው ገጠር ውስጥ አይደለም፤ ይብዛም ይነስም ከተማ ውስጥ ነው የሰጠናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ነው የሰጠናቸው፡፡ ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ነው ብዬ አይደለም፤ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሆኖም ችላ ያልነው ነገር አይደለም፤ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ ስንሰራም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህም በዚሁ ረገድ ቢታይ መልካም ይሆናል ብዬ ነው የማየው፡፡

ርዕዮት