February 27, 2019 t

የሰሞኑ ርእስ ደግሞ እነቴዲ ወደአማርኛ ተርጉመው ያቀረቡት የለማ መገርሳ ንግግር ነው። ያው በዚህ ሰአት ብዙ “የግል ፍላጎት” ያለው አካል በብሔር ስላልተጠረነፈ ከግዜው ግርግር አንፃር የኢንሴኪዩሪቲ ስሜት የሚሰማውን የሸገርን ህዝብ ለራሳቸው በሚመቻቸው ሁኔታ ነገሩን ሁሉ ፖለቲሳይዝድ እያረጉ ያስፈራሩታል። ህዝቤም ከሰው እኩል የሰማውን ነገር ወሬውን የነገሩት ሰዎች በተነተኑት መንገድ ተቀብሎ ይረበሻል። ወሬ አምጭው እኛው! ተርጓሚም እኛው! ተንታኝም እኛው ዌል እንግዴህ ለማ መገርሳ በጨፌ ኦሮሚያ ስብሰባ ላይ ተናገረው የተባለውና የምትፈለገው አንቀፅ ብቻ ተቆርጣ በፌስቡክ የተለቀቀችው ወሬው ላይ እንዲህ ይላል …

«ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉትን አምስት መቶ ሺ ሰዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ (በኦሮሚያ ክልል ማለቱ ነው) አስፍረናል። ስድስት ሺ የሚሆኑት ደግሞ አዲስ አበባ ገብተዋል»

እንግዲህ ይሄ ንግግር ነው አቧራ ያስነሳው! ብዙው ሰው አይፈረድበትም ይሄን ንግግር ለብቻው ቆርጦ አውጥቶ፣ በአማርኛ ተርጉሞ፣ እሱ ብቻ ሳይበቃው ንግግሩን ለራሱ በሚመቸው መንገድ ተንትኖ «ኦህዴድ ክዶናል፣ ለማ አታሎናል፣ አብይ አጭበርብሮናል» ብሎ የቀወጠው አካል ላይ ነው ችግሩ ያለው!! (እዚች ላይ አስምርልኝ ባሻዬ!)

በመሰረቱ አንድ መረዳት ያለብን ነገር ለማ መገርሳ የስራ ሃላፊነቱ የኦሮሚያ ክልልን ማስተዳደር መሆኑን ነው። ይህ ማለት ልክ እንደአማራው፣ ደቡቡና የትግራዩ ፕሬዘዳንቶች እሱም የህዝቡን ጥቅም ማስከበር፣ ህዝቡን ወክሎ መደራደር፣ የህዝቡን ጥያቄ ማስፈፀምና የህዝቡን ጥያቄ እንደአጀንዳ ቀርፆ ማስፈፀም ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታው ነው ማለት ነው!
ለማ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው አለ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ እርሱ የሚመራት ክልልና የድርጅቱ ጥያቄዎች የሉትም ማለት አይደለም። ወይም የራሱና የህዝቡን ፍላጎት ሌላው ክልል እንዳይቀየመው ወደኋላ ትቶ ሁል ጊዜ ሁሉንም የሚያስደስት ስራ ይሰራል ማለትም አይደለም። አሁን ባለው የብሔር አወቃቀር ሁሉም ክልል የህዝቡን አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል። አማራ ወልቃይት የኔ ነች ሲል የትግራይ ህዝብ ይከፋዋል አይልም። አፋርና ኢሳ የሚጋጩት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ነው። ደቡብ ክልልና ኦሮሚያ ፣ ሱማሌና ኦሮሚያ ፣ አማራና ትግሬ፣ ሁሉም የማይስማሙበት፣ የሚከራከሩበት፣ የሚጨቃጨቁበት ፣ አልፎ አልፎም የሚጣሉበት የመሬትም ሆነ ሌላ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። በዚህ አግባብ የሐገሪቱን ፖለቲካ ቀረብ ብሎ የሚከታተል ሰው ኦሮሚያ በአዲሳባ ላይ ያላት የአመታት ጥያቄ ዛሬ ሰበር ዜና አይሆንበትም!

አንድ አስቂኝ ምሳሌ ልስጥህማ ..

እግዜርም ሰይጣንም እንደሚያውቁት እንግዲህ ፌደራሉ አመታዊ ቀለብ ለክልሎች ሚሰፍረው በብሔርና በህዝብ ቁጥር መጠን እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ምክኒያቶች ላይ ተመስርቶ ነው። ይሄን የሚያውቁት ብሔር ብሔረሰቦቻችንና የብሔረሰቦቻችን ኤሊቶች ታዲያ እቺን ስለሚባንኑ ኦሮሞው ስልሳ ሚሊዮን ነኝ ይላል። አማራ ሃምሳ ሚሊዮን ነኝ ይላል። ሃዲያ አስር ሚሊዪን ነኝ ይላል ትግሬውም 8 ሚሊዮን ነኝ ይላል። እግዜር ያሳይህ ጎበዝ እነዚህ አራት ብሔሮች ብቻ ነን ያሉትን ቁጥር ብንደምረው 118 ሚሊዮን ይጠጋል (የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በሙሉ ሲደመር ግን 100 ሚሊዮን ነው ሁሉም ቁጥራቸውን የሚያበዙት ለምንድነው ነው? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ!

ብራዘር ብሔር ብሔረሰቦቹም ሆኑ መሪዎቹ ሁሉም ማለት ይቻላል የሌላውን ፍላጎት ወደኋላ ትተው የክልላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ይሯሯጣሉ። የፌደራሊዝም ሳይሆን የዘር ፌደራሊዝም ባህሪው ነው!! በዚህ ሁሉም የራሱን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ደፋ ቀና በሚልበት የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ደግሞ የኦሮሚያ ክልሉ መሪ ለሚቾ በቀራጮች መሃል ኢየሱስን እንዲሆን መጠበቅ የዋህነት ነው! ከለማ ከምንጠብቀው ኦነስቲ አንፃር ህግን እስከተከተለ ድረስ ለሚያገለግለው ህዝብ ጥቅም መከበር ቀን ተሌት ቢሰራ ምንም አይገርም! አይደንቅምም!

በዚህ አግባብ ታዲያ ለማ 500 ሺ ተፈናቃይ ኦሮሞን በአዲስ አበባ ዙሪያ (በኦሮሚያ መሬት ላይ) ቢያሰፍር ምኑ ነው ሃጢአቱ? መሬቱ የኦሮሚያ ከሆነና ኦሮሚያ ደግሞ ራሷን በራሷ ታስተዳድራለች ካልን በገዛ ክልሉ ለፖለቲካ ጥቅምም በለው ለኢኮኖሚ ጥቅም በሚመራው ክልል ውስጥ ለምን ለአዲሳባ ቅርብ የሆነ መሬት ላይ የራስህን ህዝብ አሰፈርክ ይባላል እንዴ?
ባይልልን ነው እንጂኮ የጌዲኦ ተፈናቃይ ትግራይ ቢሰፍር፣ የጎንደር ተፈናቃይ ለገጣፎ ቢሰፍር፣ የሱማሌ ተፈናቃይ ባህርዳር ቢሰፍርኮ ክብራችን ነበረ! ግን በዚህ ጎጠኛ ዘመን ይሄን ለማድረግ የሚያስችል ቅን ልብ የለም!! ስለዚህ ክልሎች የራሳቸውን ህዝብ ለፖለቲካም በለው ለኢኮኖሚ ጥቅም የራሳቸው መሬት ላይ ስትራቴጂክ በሚሉት ቦታ ያስቀምጣሉ!! በዚህ አግባብ ስሄድ የለማ ጥፋት አልታየኝም!!

ስድስት ሺዎቹ አዲሳባ የገቡ ኦሮሞዎችስ?

በግሌ የአዲሳባን ኑሮ ከቻሉት ሌላው ተገፍቶና ህግ ተጥሶ አይሁን እንጂ አይደለም ስድስት ሺ ስድስት መቶ ሺ ኦሮሞዎችም ፒያሳ መሃል ቢሰፍሩ ቅር አይለኝም። አዲሳባ የአፍሪካ ርእሰመዲና ነች እያልን ከኢትዮጵያ የተሰደዱ ስድስት ሺ ሰዎች ለምን ገቡ? ብሎ ማኩረፍ ምን ማለት እንደሆነም አይገባኝም።

ዲሞግራፊውን ለመቀየር ነው ምናምን የሚሉ ሰዎች አሉ። እንደኔ እነዚህ ስለዲሞግራፊ የሚያወሩ ሰዎች ጂኦግራፊ ፔሬድን የቀጡ፣ ስለስታትስቲክስ የማይባንኑ ሰዎች ይመስሉኛል በሚሊዮን የሚቆጠር የሸገር ኦሮሞ ላይ እንኳን ስድስት ሺ ስልሳ ስድስት ሺ አዲስ ገቢ ቢጨመር ይሄን ያህል የተጋነነ የዲሞግራፊ ለውጥ የሚያመጣው በምን ስሌት ነው ባሻዬ? (ሳትሰድበኝ አስረዳኝ እስቲ ባይሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ሸገር የሁላችን እስከሆነች ድረስ ሌሎች ክልሎችም «እኛም ተፈናቃይ አለን። አስርም ሃያም ሺ አዲሳባ ላይ አሳርፉልን» ብለው ቢልኩ ያባት ነው። ዝም ብሎ ግን ነገርን ከስሩና ከውሉ ሳያጠኑ የብሔር ታፔላ ብቻ እየመዘዙ ህዝብን ማሸበር ነውር ነው።

እኔ አዲሳባ ተወልጄ አዲሳባ ላይ ነው ያደግኩት። እስከማውቀው ድረስ የአዲሳባ ህዝብ በሰላምና በእኩልነት ይኑር እንጂ ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ሌላው ዘር ለምን አዲሳባ ገባ ብሎ የሚያለቃቅስ ህዝብ አይደለም። የአዲሳባ ሰው በሃይለስላሴ ግዜ መሬት ላራሹ ብሎ ገጠር ላለ ወገኑ የጮኸ፣ የደርግን ስርአት በቃህ ብሎ በከተማ ውስጥ ትግል ፋታ የነሳ፣ ኢህአዴግን በዘጠና ሰባትም ሆነ ከዚያ በፊት አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ነፍሱን የገበረ፣ አብይን ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ኦሮሞ ነው ገለመሌ ብሎ ወደብሔር ስሌት ሳይወርድ ከሁሉም ቀድሞ ወጥቶ የደገፈ ስልጡን ማህበረሰብ ነው። ይሄ ስልጡንና ከሁሉም ጋር ተፋቅሮ መኖር የለመደ ነዋሪ የሱ ህልውና እስካልተነካ ድረስ አንድን ብሔር ለይቶ የመጥላትም ሆነ ለይቶ የመውደድ ሞራልና ስብእና ይዞ አልተገነባም!

ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ሆይ ይሄን ህዝብ ተዉት! ጥያቄና ሃሳባችሁን የአዲሳባ ህዝብ ጥያቄ አስመስላችሁ አብረውት ከኖሩ ወገኖቹ ጋር አታነካኩት! የሸገር ሰው የኦሮሚያን ህዝብ አምኖ ኦሮሚያ መሬት ላይ ሃብትና ንብረቱን የሚያፈስስ፣ ሺህ ገበሬዎች በተፈናቀሉበት መሬት ላይ ኮንዶሚሚየም ተሰጥቶት ሲኖር ኦሮሞ ለምን መጣህብኝ? ሳይል ተቀብሎ እንዳኖረው የማይረሳ እራሱ ለምቶ ኦሮሚያንም አብሮ ማልማት የሚያስችል አቅም ጉልበትና ፍላጎት ያለው ከኦሮሚያም ሆነ ከየትኛውም ክልል ጋር የሚጣላበት ኢምንት ምክኒያት የሌለው ህዝብ ነው።

ባይሆን «አዲሳባ የኔ ነች ፣ ያንተ አይደለችም» የሚለውን ሙግታችሁን በጠረጴዛ ዙሪያ ፍቱ! አይዟችሁ ጠረጴዛ አይባላም!