February 28, 2019 t

የለውጡ ኃይል የነውጥ ኃይል እንዳይመስል ከባድ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ሰዓት ላይ እንገኛለን፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ሀገራችን ዙሪያዋን ተወጥራ በጭንቅ በተያዘችበት ሰዓት በፖለቲካዊ መፍትሔ ሳይሆን በተዓምራዊ ኃይል ሀገራችንን ከከበባት የስጋት ባህር ከፍሎ የሚያሻግረን ሙሴ ስንመኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ሙሴ ይሆነናል ብለን ተስፋ የጣልንበት ሰው ወደስልጣን ወጣ፡፡ ደስ አለን “ያሰብኩት ተሳካ ያለምኩት ደረሰ” ብለን አዜምን፡፡

የለውጡ ሐዋርያት “ኢትዮጲያዊነት ሱስ ነው!” በምትለዋ ቃል ብቻ ከነሱ ሱስ እንዲይዘን አደረጉ፡፡ በየዕለቱ የማይጠበቁና እውነት የማይመስሉ ድንቅ ድንቅ ሥራዎችን እያከታተሉ በደስታ አሰከሩን፡፡ ዓለም ጉድ አለ! “ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዴሞክራሲ አረአያ፣ ተስፋ ልትሆን ነው” ተባለ፡፡

ከዚህ ሁሉ አስደሳች ክንውን ጎን ለጎን የብዙኀን መፈናቀል፤ ስርዓት አልበኝነት፤ የሐይማኖት ተቋማትን ማፍረስና ማቃጠል፤ ቤት ማፍረስ ዜጎችን ከጎዳና ማንሳት በዛው እጅ ለጎዳና መዳረግ፤ ግማሹን ማሰር ግማሹን ማባበል፤ ፍትህና ይቅርታ ድብልቅልቁ ወጥቶ ግራ አጋቢ ስዕል እያየን ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ሒደት “ለውጡ እንዳይደናቀፍ” በሚል ሰበብ ከአድናቆት ውጪ ገንቢ ሂሶችን ማቅረብ ሌላ ስም ስለሚያሰጥ ዝምታን የመረጡ ብዙ ሆነዋል፡፡

ይህ በግዳጅ ሳይሆን በፍቅር የመናገር ነፃነትን ማፈን ነው!
ሀገራችን አትረፊ ተብላ የተወሰነባት ይመስል አንዱ እሳት ሳይበርድ ሌላ እየተጫረ ልባችንን የስጋት ቀጠና አድርጎብናል፡፡

እናንት የለውጥ ኃይሎች፦ የኢህአዴግ መሪና አባላት ብትሆኑሞም ቅሉ የወደድናችሁ ኢትዮጵያን ስለወደዳችሁልን ነው፡፡ በዘረኝነትና በጥላቻ የተከፋፈለውን ህዝባችንን ወደ አንድነት ታመጡልናላችሁ ብለን ስላመንናችሁ ነው፡፡

ከአንድ ምንጭ ጣፋጭና ሬት ስለማይቀዳ ትክክለኛ ምስላችሁን አሳዩን፡፡ ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁላ ስለሚያቦካ ከወገንተኝነት ሰፈር ወጥታችሁ እውነተኛ የኢትዮጵያን ተስፋ ሆናችሁ አሳዩን፡፡ በእናንተ ተስፋ ለመቁረጥ ጊዜው ገና ቢሆንም የማይመቹ አስጊ አዝማሚያዎችን እያየን ዝም አንልም፡፡

አላማችን ግለሰቦች ሳይሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ አዲስ አበባን አዲስ የጭቅጭቅ አጀንዳ ለማድረግ ለምን ይሄ ጊዜ ተመረጠ፡፡

ባለው የሽግግር ጊዜ ሀገር የማረጋጋቱንና የዜጎችን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ያለው ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምርጫ ማራዘም መፍትሔ አይሆንም፡፡ አሁን ላይ መነሳት የሌለባቸው አስጊ ጉዳዮችን ከምርጫ በኃላ የተመረጠው መንግስት ሊሰራቸው የሚችሉ ናቸው፡፡

አባካችሁ የለውጡን ኃይል የነውጥ ኃይል ከመሆን አድኑት!! በኢትዮጵያ ይሁንባችሁ ግራ አታጋቡን፡፡