March 1, 2019e

ዶ/ር አብይ እንዳለው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች ተዋህደው አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ የመሆን ሐሳብ አላቸው። ያ ከሆነ ብዙ የሚለወጡ መልካም ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።

በዘረኝነትና በጎሰኝነት የተመታው አንዱ ክልል ቢኖር የኦሮሞ ክልል ነው። በኦሮሞ ክልል ላለፉት ሃያ ሰባት አመትታ አፓርታይድ ነው የነበረው። አሁንም እንደዚያው ነው። እንደ ሸዋ ባሉ አካባቢዎች ብዙ የሌላው ማህበረሰብ አባላት አሉ። በኦሮሞ ክልል የተካለሉ፣ በቀድሞ ሸዋ ግዛቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ኦሮሞዎች አይደሉም ተብሎ ነው የሚገመተው።

እስከ አሁን ባለው አሰራር የኦህዴድ አባል መሆን የሚችለው ኦሮሞ የሆነ ብቻ ስለሆነና ኦህዴድም ገዢ ፓርቲ ስለበረ፣ በሁሉም የስልጣን እርከን የሚቀመጡት ኦሮሞዎች ብቻ ነበሩ። አሁንም በክልል፣ በዞኖ፣ በወረዳ፣ በከተሞች፣ በቀበሌ ሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉት ሁሉም ኦሮሞዎች ናቸው። ለምሳሌ በአዳማ ፣ በጂማና ቡራዮ ልዮ ዞኖች፣ በአሰላ፣ በሰበታ፣ በቦሾፍቱ…. ከተሞች፣ አብዛኛው ነዋሪ ሕብረብሄራዊ ቢሆንም፣ የነዚህ አካባቢዎች መስተዳደሮች፣ የቀበሌ ጽ/ቤቶች የሚሰሩት ኦሮሞዎች ብቻ ናቸው።

አሁን ኢሕአዴግ ሁሉን አቃፊ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ከሆነ ግን ማንም ዜጋ ይሄን ፓርቲ መቀላቀል ይችላል። የግድ ኦሮሞ ብቻ በኦሮሞ ክልል በሃላፊነት ላይ አይቀመጥም። ያኔ ሃላፊነት በብቃት ይሆናል። ለቦታው የሚመጥን፣ ሕዝብ የመረጠው ሃላፊነት ላይ ይቀመጣል ማለት ነው። ኦሮሞ ይሁን ኦሮሞ አይሁን።

ከዚህም የተነሳ፣ በኦሮሞ ክልል ሕብረ ብሄራዊ የሆነ ማህበረሰብ በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ፣ አሁን ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ በሃላፊነት ላይ የተቀመጡ የኦህዴድ ሰዎች በብዛት ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው የግድ ነው የሚሆነው። ብቃት ያለው ኦሮሞ ብቻ ይሆናል የሚቆየው። ኦህዴድንም ተጠቅመው እኩልና ዘረኛ ተግባራት የሚፈጸሙ አካላትም( እነ ጃዋር) ቀዳዳዎች ይደፈንባቸዋል።

ትልቁ ጥያቄ እንግዲህ “የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮቻቸው ዶ/ር አብይ እንዳለው ይዋሃዳሉ ወይ ?” የሚለው ነው። ብአዴን/አዴፓ፣ ደሃዴን፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የሃረሬና የቢኔሻንጉል አጋር ደርጅቶች የዉህደቱ አካል ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። ኦህዴድ/ኦዴፓ፣ ሶዴፓ (የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) እና ሕወሃት ጋር እርግጠኛ አይደለሁም።

ዉህደቱን ከመለስ ዜናዊ ጊዜ ጀምሮ ሕወሃቶች ደጋፊ ነበሩ። ዉህደቱ ከማንም በላይ የትግራይን ህዝብ የሚጠቅም ነው። ከእልህ ፖለቲካ ከወጡና የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ካስቀደሙ ፣ ሕወሃትም የዉህደቱ አካል ሊሆን ይችላል። አንድ የትግራይ ተወላጅ የአዲሱ ፓርቲ አባል ሆኖ ብቃት ካለው የባህር ዳር.፣ የነቀምቴ ከንቲባ መሆን የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠርለታል ማለት ነው።

ኦህዴድ/ኦዴፓ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ዉህደቱን ይቃወም የነበረ ደርጅት ነው።በመሆኑም አብዛኛው የኦህዴድ አባልና አመራር ለሕዝቡ ጠቃሚ ቢሆንም የነርሱን ስልጣን የሚያሰጋ ነው። ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ብቃት ሳይኖራቸው ማማ ላይ እንዳይቀመጡ ያስገድዳቸዋል። ከሌላው እኩል መታየት ይጀምራሉ። በመሆኑም እነዚህ የኦህዴድ አባላትና አመራሮች በዉች ካሉ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄረተኞች ጋር በመሆን ኦህዴድ ከስሞ በአገር አቀፍ ድርጅት ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እነዚህ ቡድኖች በውስጠ-ኦህዴድ ትግል አሸናፊ ሆነ ከወጡ ኦህዴድ/ኦዴፓ ለሁለት ይልከፈላል። በነ ዶ/ር አብይ የሚመራው ቡድን ዉህደት ሲመሰርት፣ ሌሎች እንደ ኦሮሞ ድርጅት ምን አልባትም ኦነግንና ኦፌኮን ተቀላቅለዉ ይቀጥላሉ።

በነሙስጠፋ የሚመራው ሶዴፓ የዉህደቱ አካል ፣ በነ አቶ ሙስጠፋ ደርጅታዊ ጥንካሬ የሚለካ ነው የሚሆነው። አቶ ሙስጠፋ የዉህደቱ አካል የመሆን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል። ግን ሌላዉን ይዞ አብሮ መሄድ ስላለበት እንዳሰበው ማድረግ ለጊዜው ሊያስቸግረው ይችላል።