March 1, 2019
Source: https://fanabc.com/

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርበኛ እናቶቻችና አባቶቻችን በአድዋ ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ ሚስጥር ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህብረትና በአንድነት ተደምረው ለአንድ ሀገር በመቆማቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 123ኛው የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው እናት አባቶቻችን በአድዋ የተቀዳጁት ድል በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያ እንጅ የቅኝ ገዥዎች ሰንደቅ አላማ እንዳይውለበለብ ያደረገ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ነፃነት ታፍሮና ተክብሮ እንዲኖር ያስቻለ ደማቅ የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚነስትሩ በመግለጫቸው የደምና የአጥንት መስዕዋትነት የተከፈለበት ይህ ድል የዛሬውና የነገው ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ትክሻው ጎብጦ አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር እንዳደረገ ተናግረዋል።
የአድዋ ድል በዓል በዓለም ፊት በኩራት እንድንቆም አባቶቻችን ያወጁልን አክሊልም ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግልጸዋል።
ኢትዮጵያዊውያን በጣሊያን ጦር ላይ የተቀዳጁትና ከኢትዮጵያ ባለፈ ለመላው አፍሪካ ብሎም በባርነት ቀንብር ስር ለነበሩ የዓለም ህዝቦች ተስፋ የፈነጠቀና ወኔ የሰነቀ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም አስረድተዋል።
ድሉ ትናንትን ዘክረን ዛሬን መርምረን ነገን ለማቅናት ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፥ ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሸጋገሪያ የድካም መርቻ ጉልበታችን በዛለ ጊዜም መበርቻ ነው ብለዋል።
ለዚህም ከአድዋ ድል ወዲህ በአድዋም ይሁን በሌላ መልኩ የተቀዳጀናቸው ስኬቶች ህያዋን ምስክሮች መሆናቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው ትውልድ የሚገጥሙትን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በድል በመወጣት የአያቶቹን እና የአባቶቹን ታሪክ የሚደግምበት ጊዜ ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።
አድዋ ከትግልና ድል የሚሻገር ረቂቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህይወታዊ አስተምህሮ የያዘ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፍልስፍና መሆኑንም ገልጸዋል።
የአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በመተባበር የማንነታቸውን ልክ ያሳዩበት የመስዋዕትነት ውጤት መሆኑንም አንስተዋል።
ድሉ የሴት ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ተጋድሎና የላቀ ሚና መገለጫ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የአድዋ ድልን የሚያከብር ህዝብም የሴቶች ክብር የገባው ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
የአድዋ ድል ህዝብና መንግስት ሲተባበሩ የሚበግራቸው ነገር አለመኖሩን ማሳያ እንደሆነም አውስተዋል።
በዓሉን ስናከብርም እንደ አዲስ ትውልድ በድሉ ውስጥ የተካተተውን ምስጢር በመረዳት መሆን ይገባልም ብለዋል በመልዕክታቸው።
በአድዋ ድል ውስጥ ህልውናን አፅንቶ መኖር፣ ዲፕሎማሲ፣ ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ታላቅ ውስጣዊ የህዝቦች ህብረትና አንድነት፣ ጥበብና ተግባቦት፣ ፍቅር እና መስጠት፣ ክብርና ጀግንነት ሞልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑን እረዳለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በመልዕክታቸው አንድን ሀገራዊ ድል ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የግድ እንደሚል እንማራለን ብለዋል።
የሀገር መሪዎች፣ የጦር አበጋዞች፣ ቃፊሮች፣ ወታደሮች፣ ስንቅ አዘጋጆች ሀኪሞች፣ አዝማሪዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ እንጨት ፈላጮች ፣ ውሃ ቀጂዎች፣ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ ታሪክ መዝጋቢዎች ሌላ ቀርቶ ክብቶችና አጋሰሶች እንኳን ሳይቀሩ ለድሉ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አድርገዋል። መደመር ማለት ይሄ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
በጦር መሳሪያ አቅም፣ በሀብት፣ በወታደራዊ አደረጃጀት እና ዘመናዊ የጦር ስልት በወቅቱ ታላቅ ደረጃ የደርሻለሁ ብሎ ያሰበውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ከዚህ በፊት ባልታየና በታሪክ ውስጥ ባልተስተዋለ ጀግንነት፣ አርበኛ እናቶቻችንና አባቶቻችን ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ ሚስጥር ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህብረትና በአንድነት ተደምረው ለአንድ ሀገር በመቆማቸው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ብልህ ትውልድ ከአድዋ የድል መሰዊያ ላይ ሊጭር የሚጋባው ነገርም ይሄን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በህይወት መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመስራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነፃነቷን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል።
በልዩነት ተቆራቁሰን እርስ በእርስ የምንጫረስና የምንጠፋፋ ሳይሆን የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እንድንችል በህብረትና በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ወደፊት መራመድ እንደሚገባ ገልፀዋል።
መሪና ተመሪ በሁሉም ጉዳዮች ባይግባቡ እንኳን የሀገርን ነፃነት፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲን በተመለከተ ጉዳዮች ግን ተግባብተውና አንድ ሆነው ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድል ያስመዘግባሉ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
በደምና አጥንት የተጠበቀን አንድነት ከስነ ልቦናና ከክብር ትሩፋትነት አልፎ ለኢኮኖሚ ፀጋነት እንዲተርፍ በደም ሳይሆን በላብ፣ በአጥንት ሳይሆን በጉልበት የምንከፍለው የመጪው ትውልድ እዳ አለብን ብለዋል።
ይህ የተጋዳሎ ታሪክ በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ በሳይንሳዊ ምርምር እና በጥበባዊ ስራዎች ማረጋገጥ እና ማድመቅ እንደሚገባም ነው በመግለጫቸው የጠቆሙት።
አድዋ እስካሁን በተከናወኑት ስራዎች ብቻ ተዘርዝሮ እና ተዘክሮ የሚያልፍ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ከስነ ጥበብ፣ ከእምነት፣ ከፍልስፍና፣ ከታሪክ እና ከሴቶች ተሳትፍ፣ ከመሪነት ጥበብ፣ ከሀገራዊ አንድነት፣ ከውትድርና ሳይንስ፣ በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል ብሎም ከጥቁር ሀዝቦች የነፃነት እና የትግል ታሪክ ፋና ወጊነት ጋር በማስተሳሰር ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው ስራ እንዲያከናውኑ ጥሪ በማቅረብ በዚሁ ውስጥም መንግስት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።Filed in:Uncategorized
