
የትግራይና የኦሮሞ ልሂቃንን (የፖለቲካ ድርጅቶችንም ጨምሮ አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ ሁኔታዎች ቢኖሩም በአማራ ህዝህብና መሪዎቹ ላይ ያላቸው በጥላቻ ላይ የተመሰረተ አተያይ ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁለት ምሳሌዎችን አንስቼ ለማስረዳት ልሞክር፡፡
አንደኛው የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በሆነው አጼ ምኒልክ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከልክ ያለፈ መሆኑ ሲሆን ትግሬዎቹ አጼ ምኒልክ አጼ ዮሀንስ መተማ ላይ ከድርቡሾች ጋር ሲዋጋ እሱ ግን ከጣሊያኖች መሳሪያ በመግዛትም ሆነ በርዳታ መልክ እየሰበሰበ ስለነበር የአጼ ዮሀንስን የድረሱልኝ ጥሪ ወደ ጎን ብሎ ለአይቀሬው ሞት አበቃው፡፡
በዚህም አጼ ዮሀንስ ከሞተ በኋላ ስልጣኑን በብቸኝነት መቆጣጠር ቻለና የትግራይን ህዝብ ለሁለት ከፍሎ (በትግራይና በኤርትራ ያለውን ማለታቸው ነው) በማዳከም ስልጣኑን ለማራዘም ጥረት አድረገ ብለው ይከሳሉ፡፡ ሁለተኛው የአማራን ህዝብ እንደ ብሔራዊ ጨቋኝ አድርገው በማሳየት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጀው ማህበራዊ ረፍት ለማሳጣት ጭምር ትህነጎች በፖለቲካ ማኒፌስቷቸው ሳይቀር አስፍረው የትግል መሳሪያ እስከማድረግ ደረሱ፡፡
በዚህም ምክንያት ባለፉት 44 አመታት ተወልዶ ያደገ ትግራዋይ የአማራን ህዝብ በአጠቃላይና መሪዎቹን ደግሞ በተለይ በጠላትነት ስሜት እንዲመለከት እስከማድረግ ደረሱ፡፡ ምንም እንኳ የትግራይን ሪፐብሊክ የመመስረት ህልማቸው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበረ ቢሆንም መሀል ላይ የተውት መስለው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኙን ቦታ በመያዝ ላለፉት 27 አመታት እንዳሻቸው ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ለመኖር ቻሉ፡፡
አሁን ደግሞ በፌዴራል ደረጃ የነበራቸውን የበላይነት በኦሮሞዎች ሲነጠቁ አንቀጽ 39ን ተጠቅመን ልንገነጠል እንችላለን ማለት ጀመሩ፡፡ የኦሮሞቹ ልሂቃን ደግሞ በፈንታቸው አጼ ምኒልክ የኦሮሞን ህዝብና አካባቢ በሀይል ተቆጣጥሮ በመያዝ የኦሮሞን የአስተዳደር ስርአት (ገዳን ጨምሮ) አዳክሟል፣ ህዝባችንንም ጨፍጭፏል፣በዚህም በወቅቱ ጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ተደምሮ ሊሆን የማይችለውን 5 ሚሊዮን ኦሮሞ ተገድሏል እስከማለት ይደርሳሉ፡፡
በዚህም ሳቢያ የኦሮሞ ህዝብ ላለፉት መቶ አመታት በአማራ ገዥ መደቦች ጭቆና ስር ሲማቅቅ እንዲቆይ አድርጓል በማለት ያማርራሉ፡፡ እናም ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ከተቻለ የኦሮሞን ህዝብ ከብሔራዊ ጭቆና ነጻ በማውጣት ራሱን የቻለ የኦሮሞን መንግስት መመስረት ካልሆነም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና የምንጫወትበት ቦታ ሊኖረን ይገባል ሲሉ ግልጽ የሆነ አማራጭ ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡
ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን መቆጣጠራቸውን ካረጋገጡ በኋላ አዲስ አበባ የእኛ ነች፣ ስለሆነም በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስር ትሁን እስከማለት ደረሱ፣ እንዲሁም የኦሮምኛ ቋንቋ የአዲስ አበባ እና የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ መሆን አለበት የሚል የመደራደሪያ ሀሳብም አመጡ፡፡
እነዚህ ወገኖች በአስተሳሰብ ደረጃ አንድ በመሆናቸውም ልክ እንደ ትግራይ ልሂቃን ሁሉ የመጀመሪያ ምርጫቸው የኦሮሞን ህዝብ ከኢትዮጵያ በመገንጠል ራሱን የቻለ አገር ማድረግ ቢሆንም አሁን ላይ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን መቆጣጠር እስከቻልን ድረስ የኦሮሞን ህዝብ ይበልጥ የሚጠቅም ነገር ለመስራት ሲባል አብረን ብንቆይ ችግር የለውም ይልቁንም ይኸን ሁኔታ ማጠናከር አለብን የሚለውን አማራጭ በመያዝ ስለአንድነትም መስበክ ጀምረዋል፡፡
ሌላው በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸው ጥላቻ የሚገለጸው ሲሆን የአማራን ህዝብ ትግሬዮቹ ትምክህተኛ ሲሉት ኦሮሞዎቹ ደግሞ ነፍጠኛ እያሉ ስለሚሰብኩ ትውልዱ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ደረጃ የአማራን ህዝብ በጥርጣሬ አይን እንዲያይ ለማድረግ ሞከሩ፣ እናም የአማራ ህዝብ በሁለቱም ብሔሮች ልሂቃን አማካኝነት በተሰራው ያልተገባ ፖለቲካዊ ሴራ ምክንያት በህዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ችለዋል፡፡
ይህን ፖለቲካዊ ሁኔታ ተከትሎ በአንድ በኩል የአማራ ድርጅቶችን በጠላትነት መፈረጅና የአማራ ህዝብም በየትኛውም አካባቢ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖረው በማድረግ የማዳከም ስራ እየሰሩ መሆኑን በግልጽ እየተመለከትን ነው፡፡ ለዚህም እንደ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰደው የትግራይ ቴሌቪዥን እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በአማራ ክልል ህዝቦች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠርና እርስ በርስ በጥርጣሬ አይን እንዲተያዩ ለማድረግ የሚሰሩት ስራ ነው፡፡
ምክንያቱም እንዚህ የመገናኛ ብዙሀን በጣቢያዎቻቸው የአማርኛ ፕሮግራም በመክፈት በአማራ ክልል ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በማጉላት በዜና መልክ ከመዘገብ አልፈው የቅማንትና የአገው ተወካይ ነን የሚሉ ወገኖችን በመጋበዝ አማራ ክልል ውስጥ ጭቆና እንዳለ፣ የእነዚህ ብሔረሰቦች መብት እንደማይከበር አድርገው ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ሌላው ማሳያ ደግሞ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ኤርትራ የነበረው የኦነግ ሰራዊት በዛላንበሳ አድርጎ ሲገባ በትህነግ አመራሮች አማካኝነት ግብዣ እየተደረገለት እንዲያልፍ ሲደረግ በተቃራኒው የአዴሀን ሰራዊት በሁመራ በኩል ሊገባ ሲል ግብዣ ሊደረግለት ቀርቶ ኮከብ ያሌለበትን ሰንደቅ አላማ ይዘህ መግባት አትችልም ተብሎ ተከለከለ፡፡
እናም የአማራ ልሂቃን (የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር) የእነዚህን ወገኖች አንድነት በአግባቡ ተገንዝበውና በኢትዮፕያ ፖለቲካ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙትን የተቀነባበረ ሴራ መርምረው አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡
ይኸ ሁኔታ ጊዜ የሚሰጥ ስላልሆነም በመካከላቸው ያለውን መለስተኛ ልዩነት ወደ ጎን በመተው ልክ የትግራይና የኦሮሞ ልሂቃን እየፈጠሩት እንዳለው ጊዜያዊ አንድነት የአማራ ልሂቃንም ራሳቸውን ወደ አንድ አምጥተው የአማራን ህዝብ መታደግ ይገባቸዋል፡፡ቀጥሎ በምትመለከቱት ምስል ላይ እንደሰፈረው ይኸ መንግስት ወዴት እያመራ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡
