ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

27 February 2019
የባዮ ቴክኖሎጂ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል
በኢትዮጵያ የባዮ ቴክሎጂ መስክ ከዚህ ቀደም በዘረመል ምሕድስና (ልውጠ ህያው) ተሻሽሎ ለምርት መዋል እንዲችል በምርምር ከተፈቀደው የጥጥ ምርት በተጨማሪ በበቆሎ፣ በእንሰትና በድንች ዝርያዎች ላይ የልውጠ ህያው ምርምር እየተካሄደባቸው እንደሆነ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው የምክክር መድረክ ወቅት እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ ጥጥ ልውጠ ህያው ምርምር ተካሂዶበት ወደ ምርት ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ምርቱ በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር በሳይንሳዊ ምርምር ከመረጋገጡም በላይ፣ የጥጥ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃው ቦልዎርም የተሰኘ ህዋስ ጥጡን እንዳያጠቃ በማስቻል ስኬታማ ውጤት እንደተገኘበት፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ታደሰ ዳባ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡
የጥጥ ምርትን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችል የዘረመል ምሕንድስና በማካሄድ የተገኘው ውጤትም በመስክ መረጋገጡን ሲያብራሩም፣ በአገሪቱ ጥጥ አምራች በሆኑ ሰባት አካባቢዎች ልውጡ ጥጥ ተዘርቶ ከነባሮቹ ዝርያዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ከምርምሩ ውጪ ባሉ አካላት መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ በገዋኔና በሌሎችም አካባቢዎች የተዘሩት የልውጠ ህያው ጥጥ ዝርያዎች ተዋህሳያንን በመቋቋም ውጤት ማሳየታቸው ቢረጋገጥም፣ ‹‹ቢቲ ጥጥ እንደ ከሸፈ አስመስለው የሚያስወሩ የተለየ ፍላጎት ያላቸው አካላት ናቸው ችግር እንዳለበት የሚያስወሩት፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለንግድ እንዲውሉ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ፈቃድ የተሰጣቸው የጥጥ ልውጠ ህያው ዝርያዎች ከሱዳንና ከህንድ የመጡ ስለመሆናቸው ማብራሪያ የሰጡት፣ በኮሚሽኑ የደኅንነት ሕይወትና የመጤ ወራሪ ዝርያዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጉዲና ናቸው፡፡ እንደ አቶ አሰፋ ማብራሪያ፣ እስካሁን ወደ አካባቢ እንዲለቀቅ ፈቃድ ከተሰጠው የልውጠ ህያው ጥጥ ባሻገር፣ ለበቆሎ ዝርያዎችም በዘረ መል ምሕንድስና ድርቅና ተባይ መቋቋም የሚችሉበት ምርምር እንዲካሄድ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በእንሰት ላይም የቅድመ ምርምር ጥናት እንዲካሄድ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ በድንች ላይም ምርምር እንደሚጀመር ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በእንሰት ላይ በተለይ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የኮባ ቅጠልን በማጠውለግ የሚያደርቀውን በሽታ የሚቋቋም የልውጠ ህያው የእንሰት ዝርያ ለማውጣት እንደሚታሰብ ታደሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ በኡጋንዳ እንዲህ ያለውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ሰፊ ሥራ መከናወኑም አብራርተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ መረቀቁን አስታውቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመላከቱት፣ በስምንት ማዕቀፎች ላይ የተመሠረተ የባዮ ቴክሎጂ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል፡፡ ፖሊሲው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና እንዲሁም በአካባቢ ላይ ትኩረት የሚሰጡ ይዘቶች ያሉት ሲሆን፣ ለእነዚህ መስኮች ረቂቅ ፍኖተ ካርታዎችም መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ኢንስቲትዩትን በመወከል በባዮ ቴክኖሎጂ መስክ ስላሉ ዓለም አቀፍ ክንውኖች የወሰኑትና የቀድሞው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ እንዳለ ገብሬ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ግብርና እየተሞከሩ ከሚገኙት ምርቶች ባሻገር በቀንድ ከብት ሀብት፣ በባዮ ፊውልና በሌሎችም በርካታ መስኮች ውጤት የሚያስገኙ የባዮ ቴክሎጂ ምርቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
ይሁንና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ዘንድ ባዮ ቴክኖሎጂን በተመለከተ፣ በተለይም በልውጠ ህያዋን መስክ የሚታየው ፅንፈኝነት ከግል ጥቅም የሚመነጭ መነሻ ምክንያት እንዳለው እንዳለ (ዶ/ር) ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ሁሉ ታደሰም (ዶ/ር) በሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ ከመከራከርና ከመነጋር ይልቅ በአሉባልታ ወሬዎች የሚመሩ የሳይንሱ ተቃዋሚዎች እውነታውን ስለማያመላክቱ፣ ከፀረ ዘረመል ምሕንድስና አቀንቃኞች ጋር በግንባር መነጋገር ከባድ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ FacebookTwitterLinkedInShare
