March 2, 2019

በሶማሌ ክልል በተለይም ከሃረርጌ የተፈናቀሉ አዲስ አበባና ዲስ አበባ ዙሪያ መስፈራቸው ሚስጠር አይደለም። ዜጎችን በማንኛውን አገር ኑሮ የመመስረት መብት ስላላቸው አዲስ አበባና አዲስ አበባ አካባቢ መቋቋም ከፈለጉ እነርሱን በዚያ ማቋቋሙ መልካም ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ግዴታ ነው።

ሆኖም ግን የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር ተቃዉሞ ያስነሳበት ዋናው ምክንያት አንደኛ ተፈናቃይች በአዶስ አበባና አካባቢ እንዲመጡ የተደረጉት ፈልገው ሳይሆን በኦህዴዶች አስገዳጅነት መሆኑ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ ማቋቋም ከተፈለገ፣ ሃረርጌ አካባቢ ባሉ ከተሞች ማቋቋም የተሻለ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያለውን የዖርሞ ቁጥር ለማጨመር ሆን ተብሎና ተጠንቶ የተደረገ ነው በሚል ነው ተቃዉሞ የተነሳው።

ያ ብቻ አይደለም፣ የኦሮሞ ክልል መንግስት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ሲያቋቁም ከቡራዩ፣ ከለገጣፎ፣ በኢሊባቡር፣ከጉጂ የተፈናቀሉ ሌሎች ማህበረሰባትን ለማቋቋም አይደለም እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ እንኳን ያደረገው ነገር አለመኖሩ ሌላ የተቃዉሞ ምክንያት ነው።

ተቃዉሞዎችን ተከትሎ አቶ ለማ መገርሳ የሰጡት አስተይየት ባይኖርም፣ የኦህዴድ/ኦዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል፣ አቶ አዲስይ አረጋ ማብራሪያ ሰጠዋል፡

አቶ ለማ በኦሮምኛ የተናገሩትን ትውልዳቸው ወለጋ የሆኑት ፣ አብርሃም አለሙ (ዶክተር) እንደተረጎመው

———————————

የከተማ ፖለቲካን (አርበን ፖለቲክስ) ማጤን አለባችሁ፤ ችላ ልትሉት አይገባም፤” ያላችሁት፣ ትክክል ነው፡፡

የከተማ ፖለቲካ (አርበን ፖለቲክስ) ሊጤን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማእከል (ሴንተር ኦፍ ፖለቲክስ) ከተሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሀገር ፖለቲካ የሚወስነውም ከተማ ነው፤ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተማ ውስጥ ፖለቲካ ማለት አንድ ቁጥር ዲሞግራፊ (የህዝብ ስርጭት) ነው፡፡ እዚያ ላይ አንዱን ወደዚያ መግፋት፣ አንዱን ወደዚህ መጎተት፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን፣ እንደ ኦሮሚያ ብዙ ነገሮች እየሰራን እንዳለን መገንዘብም ያስፈልጋል፤ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የጀመርነው በጣም አበረታች ነው፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ 500000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ እንደምንሆነው ሆነን፣ ገፍተንም፣ ምንም ብለን፣ ከዚህም ከዚያም ብለን፣ የገዳ አባቶችንም፣ ሽማግሌዎቻችንንም ይዘን፣ እንደለመድነው እርቅ ፈጥረን፣ አቅፈን፣ ስመን ወደ ነበሩበት ቦታ ልንመልሳቸው እንችል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መመለስ ይቻል ነበር፤ እኛ ግን ልንመልሳቸው አልፈለግንም፡፡

ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ለኦሮሞ አንድነት፣ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ዛሬም ችግር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ገጠር አላሰፈርናቸውም፤ ከተማ ነው ያሰፈርናቸው፣ እነዚህን ሰዎች፣ እወቁ፡፡ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ አይደለም፡፡

እኒህን ከዚያ የተፈናቀሉትን ሰዎች፣ የዚህን አካባቢ ባህል የማያውቁ ሰዎች፣ በብዙ ነገሮች ከአካባቢው ጋር የማይመሳሰሉ፣ ይቸገራሉ። መቼም ይቸገሩ፣ ዛሬ ችግር የማያጣው ቢሆንም፣ ከተቸገረም እዚሁ ከተማ ውስጥ ይቸገር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በእግሩ የሚቆምበት መሬት ይኑረው፤ እሱ ቢቸገርም ለልጆቹ የሚሆን ስለሆነ፣ ብለን ህዝባችንንም አስቸግረን ካለን ነገር ላይ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሰፈርናቸው፡፡ አብዛኛው የሀረርጌ ሰዎች ናቸው፣ እወቁ፡፡ቦርደዴ ማስፈር ይቻል ነበር፤ ምስራቅ ሀረርጌ ልናሰፍራቸው እንችል ነበር፡፡ ማስፈር ትክክል ከሆነ እንዲያውም እዚያው አካባቢ ነበር ማስፈር የሚገባው፤ ያን ባህል ነው የሚያውቀው፣ ያን አየር ነው የሚያውቀው፡፡ ወደማያውቀው ባህል እዚህ አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ አሰፈርነው፡፡ ቢቸገር ቢቸገር ሁለት ዓመት ነው ሊቸገር የሚችለው፤ ከዚያ በኋላ ሰው ሆኖ ይወጣዋል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ላይ ያለው ፋይዳ፣ ሄዶ ሄዶም በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ስለሚፈይድ፡፡

ወጣቱንም ስራ እናስይዛለን ብለን በንግድ ስም፣ በሌላም ነገር ስም ብዙ ነገር ስናደርግ ነበር፤ እናም አብዛኛውን ከተማ ውስጥ አስገባነው፡፡ ወደ ከተማ ስናስገባው የሚኖርበት ቦታ ኖሮት ነው፡፡ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያን ክልል ሰራተኞች ዘንድሮ መሬት የሰጠናቸው ገጠር ውስጥ አይደለም፤ ይብዛም ይነስም ከተማ ውስጥ ነው የሰጠናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ነው የሰጠናቸው፡፡ ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ነው ብዬ አይደለም፤ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሆኖም ችላ ያልነው ነገር አይደለም፤ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ ስንሰራም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህም በዚሁ ረገድ ቢታይ መልካም ይሆናል ብዬ ነው የማየው፡፡

———–

አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ የሚከተለውን ምለስ ሰጥተዋል

Addisu Arega Kitesa

ሠሞኑን አንዳንድ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች የክቡር ፕረዝዳንት ለማ መገርሳን ንግግሮች ከተነገረበት አዉድ ዉጪ እና ትርጉም ጭምር አጣምመዉ በማቅረብ ፕረዝዳንት ለማን የአሻጥር ፖለቲካ አራማጅ አስመስለዉ በማቅረብ የማጥላላት ዘመቻቸዉን ተያይዘዉታል፡፡ ለአብነትም በአንድ መድረክ ስለ ከተማ ዲሞግራፊ የተነገረዉን ንግግር በአሻጥር ፖለቲካ ተርጉመዉ እያራገቡት ይገኛሉ፡፡

በዚህ መድረክ አንዱ ተሳታፊ በኦዲፒ የእስካሁን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የኦሮሞ ህዝብ በኢኮኖሚ ሆነ በማህበራዊ እድገቱ እምብዛም እንዳልተሻሻለ አሁንም በገጠር በሞፈር እና ቀንበር እያረሰና የከብት ጭራ እየተከተለ እየኖረ እንደሆነ፣ ኦሮሞነት በገጠር እና በኋላ ቀር ኑሮ እየተመሰለ ነዉ የሚል ጠንከር ያለ ትችት አዘል ጥያቄ ከአንድ ተሳታፊ ለክቡር ፕረዝዳንቱ ተነስቶ ነበር፡፡ ለዚህም ጥያቄ ፕረዝዳንት ለማ ማብራሪያ ሲሰጡ ይህንን ችግር እንደ ፓርቲ ለመቀየር መስራት አለብን ከሚል ቅን ሀሳብ በመነሳት ኦሮሞነት በኋላ ቀር እና በገጠሬነት ብቻ ሳይሆን የከተማ ዘመናዊ ኑሮም መገለጽ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በዚህም ረገድ ኦዲፒ ጠንክሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝና ከኢትዮጵያ ሶማሌ በኦሮሞነታቸዉ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ጭምር በኦሮሚያ ከተሞች በህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲሰፍሩና የከተማ የኑሮ ዘይቤን እንዲለማመዱ መደረጉን፤ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች በከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታን እንዲያገኙ መደረጉን፤ በኦሮሚያ ከተሞች የኦሮሞ ህዝብ ወደ ከተማ ኑሮ እየተሰባጠረ መምጣቱን፤ ወደ ፊትም የኦሮሞ የስነ ህዝብ ስብጥር (ዲሞግራፊ) በገጠር ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበትና ህዝባችን በከተማም መኖር እንዳለበት ለዚህም ኦዲፒ ጠንክሮ እንደሚሰራ አጥብቀዉ ምላሽ ሠጥተዋል፡፡

የሚገርመዉ ጉዳይ ኦሮሞ ህዝብ አኗኗር በኋላ ቀር የገጠር ኑሮ ብቻ መታወቅ የለበትም፣ ህዝባችን ኑሮዉ መሻሻል አለበት ገጠርም ከተማም መኖር አለበት የሚል ሃሳብ እንዴት የአሻጥር ፖለቲካ ሊሆን ይችላል? የኦሮሞን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል እና ወደ ከተሜነት ማዘመን የክልሉ መንግስት ግዴታ ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት የማንም ፈቃድ እና ቡራኬ አያሻዉም፡፡

ክቡር ፕረዝዳንት ለማ መገርሳ ኢፍትሃዊነት እና የአሻጥር ፖለቲካን የሚጸየፉ፣ በህዝቦች ወንድማማችነት ፣እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በጽኑ የሚያምኑ ይንንም በተግባር ታግለዉ ጠንካራ ሥብዕናቸዉን በተግባር ያረጋገጡ የህዝብ ልጅ ናቸዉ፡፡ አምርረዉ የሚጠሉትንና ሲታገሉት የነበረዉን የሴራ እና የአሻጥር ፖለቲካ በማራማድ የኦሮሞን ህዝብም ሆነ በግላቸዉ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚያስብ ስብዕና ፈጽሞ የላቸዉም፡፡

ነገር ግን ፕረዝዳንት ለማ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕረዝዳንት እንደመሆናቸዉ የኦሮሞን ህዝብ ኑሮ ለመለወጥ መስራት ግዴታቸዉ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም ፕረዝዳንቱ የኦሮሞን ህዝብ የልማት እና የለዉጥ አጀንዳዎች ባነሱ ቁጥር በአሻጥር ለመክሰስ መሯሯጥ ኢአመክኖአዊ እና ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ 90