March 3, 2019e

‹‹ባለፉት ዓመታት የነበረው ‹ራሳችሁን ቻሉ› አስተምህሮ ዛሬ በቀላሉ እንዳንተቃቀፍ አድርጎናል፡፡›› ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ

‹‹ይህ ትውልድ የዓድዋን ድል መድገም የሚችለው ለሀገሩ አንድነት ዋጋ ሲከፍል ብቻ ነው፡፡›› ኡስታዝ አቡበከር

(አብመድ) በግዮን ቀለም ሰው መሆን ክቡር ዝግጅት ላይ የታደሙት ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝና ኡስዝ አቡበከር የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ዓድዋን መነሻ ጭብጥ በማድረግ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ ዳስሰዋል፡፡

የፕሮፊሰር ሹመት ሲሻኝ ዋና ዋና ሐሳቦች፡-

የዓድዋ ድል በደግነት የተገኘ ቱሩፋት ነው፡፡
ዓፄ ምኒልክ ደግነታቸውን በሕዝብ ልብ አኑረው ባንክ ላይ እንደሚገኝ የገንዘብ ወለድ ትርፍ ከሕዝቡ አግኝተዋል፡፡
ጣልያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ገዥዎችን በጉቦ እና በሥልጣን እንሰጥሃለን ሰበብ ያግባቡ ነበር፡፡ ያኔ ከግል ጥቅም ይልቅ የሀገር ፍቅር ያነሆላላቸው ዜጎች ‹‹እምቢ›› ብለው በአንድነት ድል አድርገዋል፤ ዛሬስ?

ለኢትዮጵያውያን ከችግር ጊዜ መውጫ ቀዳዳቸው ቀድሞ የነበረው ባሕላቸውና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ነው፤ ነገር ግን ባለፉት 40 ዓመታት እነዚህ እሴቶች ተሸርሽረዋል፡፡ ሰዎች በአንድነት ሲሰባሰቡ ‹‹ተበተኑ›› እየተባሉ አብሮነት ጠፍቷል፤ ይህም አሁን ካለንበት ሁኔታ ላይ ጥሎናል፡፡

በአሁኑ ዘመን የሰው ልጅ ለብቻው የትም ሊደርስ አይችልም፤ ወደ ቀደመው የዋሻ ስልጣኔ ዘመን ሊመለስ ካልሆነ በቀር፡፡ ይህ ዘመን የአብሮነት እንጅ የብቸኝት አይደለም፡፡

በዓለም ላይ የተሳካላቸው ስልጣኔዎች አንድነትን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ከስልጣኔ ግርጌ ያሉ ሀገራት ደግሞ ዕድገታቸው ዓለም ላይ ተፅዕኖ የሚያደርስ አይደለም፤ ከእልቂት እንኳ ሊያድናቸው አይችልም፡፡

ዋግ ሹም ጓንጉል ከዓፄ ምኒልክ ተኳርፈው በሽፍትነት ሕይወት ርቀው ይኖሩ ነበር፤ ጣልያኖች ኢትዮጵያን መውረራቸውን ተከትሎ ግን ‹ጃንሆይ ይቅር ይበሉኝ› ብለው የዘመቱ የጀግና ምሣሌ ናቸው፡፡ ሀገር ከሐሳብ ልዩነት በላይ መሆኑን አሳይተዋልና፡፡

ገንዘብ ወረቀት ነው፤ ገንዘብን የሁሉ መግዥ ማድረግ ስላለብንና ሁላችን ስለተማመንንበት ግን እየተለዋወጥንበት ነው፡፡ አንድም ‹‹ገንዘቡ አያስፈልገኝም›› ብሎ እንዲሁ የሚኖር ወይም የተለዬ መገበያያ የሚጠቀም የለም፡፡ በአብሮነት በገንዘብ ተስማምተን እንደምንጠቀው አንድነትንም ገንዘብ ማድረግና መስማማት አለብን፡፡

ባለፉት ዓመታት የነበረው ‹‹ራሳችሁን ቻሉ›› አስተምህሮ ዛሬ በቀላሉ እንዳንተቃቀፍ አድርጎናል፡፡ ዓድዋ ግን ከመቃቃር ይልቅ የአንድነት አሸናፊነትን ዓሳይቷል፡፡

የኡስታዝ አቡበክር አነቃቂ ሐሳቦች ይዘት፡-

ዓድዋ የአንድነት ኃይልና የክብራችን መለኪያ ነው፡፡

ዛሬ ዳግማዊ ምኒልክ የሉም፤ ያለነው እኛ ነን፤ እነሱን እያስታወስን፡፡ የምናስታውሳቸው ደግሞ ይህንን የመሠለ ታሪክ ስለሠሩ ነው፡፡ እኛ አሁን ካለንበት የእኔነት ስሜት ወጥተን ኢትዮጵያዊነት ስሜት ገንኖ ሊልቅ ይገባል፡፡

ይህ ትውልድ የዓድዋን ድል መድገም የሚችለው ለሀገሩ አንድነት ዋጋ ሲከፍል ብቻ ነው፡፡

መስዋዕትነት የሚከፈለው ራስን አቅልጦ ሌሎች እንዲኖሩ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ይህ መስዋዕትነት የሚከፈለው ደግሞ ‹‹ለእኔ ብቻ›› ከሚል ስሜት ወጥቶ ለእኛ የሚል ስሜት ሲፈጠር ነው፡፡

የሰው ልጅ ያለልዩነት ሐሳብ ወደዚች ምድር ላይ አልመጣም፤ ነገር ግን ለጋራ ማንነት ፍላጎቶች ሊገሩ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በሰዎች የምትከበር አገር እንድትሆን መሥራት ይኖርብናል፡፡

እንኳን ተለያይተን ተሳስበንና ተከባብረን ለመኖር ብዙ መስዋዕትነት ያስፈልጋል፡፡

ከራሳችን ጋር ታግለን የምናስቀራቸው የግል ስሜቶች ሀገርን በክብር የሚያኖሩ ናቸው፤ ስሜታችን ካልገራን ደግሞ ሀገርን ያፈርሳሉ፡፡

ክብር እንዲሁ ተቀጥፎ የሚበላ ቅጠል አይደለም፤ ትውልዱ ዛሬ የትናንቱን ታላቅነት ለማስመለስ የምሥጢር ቁልፉ አንድነት መሆኑን አምኖ ሊሰራ ይገባል፡፡

የሌሎች ወንድሞቻችን መውደቅ እኛ ቁመን እንድንሄድ አያደርግም፤ ይልቁንም እያሳሳቀ ይወስዳል፡፡
► መረጃ ፎረም – JOIN US