Finotedemocracy Finotedemocracy and Eprpyouthleague Eprpyouthleague
No photo description available.


“ኢሕአፓ የኢሳያስን የቕኝ ግዛትነት ጥያቄ ሆነ የወያኔን የመገንጠል ቧልት የደገፈበት ወቅት አልነበረም። በዚህም አቋሙ የተነሳ ወያኔም ሻዓቢያም በድርጅቱ ላይ ደም መፋሰስን ያስከተለ ከፍተኛ ጥቃት አድርሰውበታል።”

ከየካቲት 66 ዓም አብዮት መፈንዳት ቀደም ብሎ በአገራችን በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍለ ሀገሮች በህዝቡ ይነሱ የነበሩ የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የብሔር ጭቆናን ያካተተ ነበር። ይህን ጉዳይ በተመለከተ፥ በዚያን ወቅት በውጭና በአገር ቤት የሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎች፥ በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥም፥ ፅሁፍ እያዘጋጁ በርካታ ውይይት አካሂደውበታል። አብዛኛውም የዚያን ጊዜ ተማሪ ጭቆናው በእርግጥም እንደነበር ግንዛቤ የያዘበት ከመሆኑም ባሻገር ተደብቆ እንዲቆይ የተደረገውን የህዝብ ሰቆቃ ይፋ እንዲሆን ማድረግ ይገባል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ እንደነበር የተማሪው እንቅስቃሴ ታሪክ የመዘገበው ነው። በዚያን ወቅት ተማሪ የነበረው ዋለልኝ መኮንን “ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ናት” ብሎ ያቀረበው መጣጣፍ የጥያቄውን ክብደት አመላካች ነበር ቢባል አሌ የሚሉት አይደለም።

ኢሕአፓ ከአብዮቱ መፈንዳት ቀደም ብሎ በ1964 ዓም ሲመሰረትም፥ ከኒሁ ተማሪዎች ተወጣጥቶ የተደራጀ እንደመሆኑ የጥያቄውን መኖር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ይደረጉ የነበሩ የአርነት እንቅስቃሴዎች፥ በእነ ዋቆ ጉቱ ይመሩ የነበሩ የባሌ፥የአሪሲ ተጋድሎዎች፥ ሜጫና ቱለማ በሚል ስያሜም የሚጠቀሱና፥ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩና ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ወደ 60 አመታት ያህል የባእድ ኃይላት ሥር እንዲተዳደር የተገደደው የኤርትራ ህዝብ፥ በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ መሪነት ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ታእዛዝንና ኤርትራ ተመልሳ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሀድ አጥብቀው ይፈልጉ የነበሩ የኤርትራ የአንድነት ኃይላትን ጨምሮ ባደረጉት ትግል በ1952 ዓም ኤርትራ በፈደሬሽን እንድትቀላቀል ሆኖ ነበር።

ይህ ጠቅላይ ሚኒስተር አክሊሉ ሀብተወልድ እንዳይፈርስ በጊዜው ተቃውመውት ነበር የተባለው የፌደሬሽን ትስስር፥ ብዙም ሳይቆይ በጃንሆይ ትእዛዝ በ 10 ዓመታት ውስጥ በ1962 ዓም እንዲፈርስ በመደረጉ እነሆ እርምጃውን በፅኑ የተቃወሙ ኤርትራውያን እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው ዱር ከቤቴ በማለት የአርነት ትግል እንደጀመሩ ታሪክ የመዘገበው ነው።

እነዚህ የአርነት ተጋድሎዎች ኢሕአፓ የፈጠራቸው ሳይሆኑ ፥ ኢሕአፓም ሆነ አብዮቱ በኢትዮጵያ ከመከሳቸው በፊት እየተካሄዱ የቆዩ ናቸው። የኃይለሥላሴ መንግሥት ሁሌም ጥያቄውን ከአገር ማፍረስና አንድነትን ከመናድ ክስ ጋር በማያያዝ በኃይል ለማስቆም ከመጣር በቀር ለጥያቄው መልስ የሚሆነውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማቅረብ ባህርዩ የሚፈቅድለት አልነበረምና የጉልተኛው ሥርዓት እስከ የካቲቱ አብዮት ዋዜማ ድረስ ከድርጊቱ አልተቆጠበም ነበር።

ኢሕአፓ በፕሮግራሙ ላይ በግልፅ እንዳሰፈረው በኢትዮጵያ ውስጥ የህዝብ የሥልጣን ምንጭነትና የበላይነት መብት ተረጋግጦ ህዝቧ በእኩልነትና በአንድነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን አጥብቆ ሚታገል በመሆኑ፥ በአገሪቱ የሚካሄደው የሕዝብ ትግል በሂደት የሚደርስበትን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት እየገመገመ እነዚህን የትግሌ አልፋና ኦሜጋ ናቸው ብሎ የቆመላቸውን ትላልቅ ዓላማዎች ለማሳካት ብሎም የአገዛዙን አከርካሪ ለመስበርና ውድቀታቸውንም ለማፋጠን፥ ለዘሌቄታውም ህዝብን የበለጠ ለማቀራረብ ይበጃሉ ያላቸውን አቋሞች እየወሰደ ቆይቷል። አሁንም ድረስ ይህንኑ እያደረገ እንዳለ ልብ ላለ ሁሉ የተደበቀ አይደለም።

በግብታዊነት የየካቲቱ 66 ዓም አብዮት መላ አገሪቱን ባጥለቀለቀበት ወቅትም ህዝብ ካነሳቸው እንደ መሬት ላራሹ፥ ዳቦ ለተራበ፥ የዲሞክራሲ መብቶች ያለገደብ፥ ግዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት ወዘተ…ከሚሏቸው ጋር የብሄር ጭቆናውም ጥያቄ አብሮ መልስ የሚሻው ሆኖ ጎልቶ ወጣ። ኢሕአፓ ራሱን ለሕዝብ ይፋ ባደረገበትም በነሃሴ ወር 1967 ዓም ይህ የሕዝብ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል ነውና መፍትሔውም ከዚህ ሁኔታ መረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ እንደሚያምንም ገለፀ። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትም መከበር እንዳለበት አስታውቆ በመርህ ደረጃም እስከመገንጠል የሚለውንም ሊያካትት እንደሚችል የተቀበለበትም ነበር። በተጨማሪም አብሮ ለዘመናት የኖረ በሁሉም መስክ የተሳሰረና የተዋለደ ሕዝብ ከመለያየት ይልቅ አብሮነቱን የሚመርጥና የሚልቅበት መሆኑን ሳይታክት እንደሚቀሰቅስበትና ለተግባራዊነቱም የሚቻለውን ሁሉ ከማድረግ እንደማይቆጠብ በጊዜው ይፋ አድርጓል።

የኢርትራውን ጉዳይ በተመለከተ ህዝቡ በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ጋር በብዙ ገመዶች የተቆራኘ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱ የተዋለደና አብሮም ታሪክ የሰራ ስለሆነ ወንድምና እህትማማቾች መሆናቸውን ሁሉም በልቦናው የሚያውቀው ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም። ያም ሆኖ ለ60 ዓመታት ክፍቃዳቸውና ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆነ ምክንያት የኤርትራ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ተለይቶ እንዲኖር ተገዶ ስለነበር፥ በፖላቲካው፥በኤኮኖሚውና በማህበራዊ ስነልቦናው እድገት ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለየት ያለ እንደነበር ሀቅ ነው። ያም በመሆኑ በኤርትራ ይደረግ የነበረው የአርነት ተጋድሎ ሌሎች አካባቢዎች ከነበሩት ጋር በመሰረቱ የተለየ ባይሆንም የኢርትራው ልዩ ሁኔታ ግን እጅጉን ውስብስብና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ እንደነበር ኢሕአፓ በጊዜው የተገነዘበው ነበር።

ባንድ በኩል ፋሽስታዊው ደርግ አፄው ይከተሉት የነበረውን በጦርነት የማስቆም አባዜ ይበልጥ አፋፍሞ ቀጥሎበት ፥ በሁለቱም ወገን በወንድማማች ጭቁን ህዝብ ላይ ከፍተኛ እልቂት ማድረሱን ተያይዞት ባለበትና ነፃ እናወጣሃለን ይሉ የነበሩ የኢርትራ ግንባሮች በተለይ ሻዓቢያ ያደርሱት የነበረው ተጨማሪ በደል የኢርትራን ህዝብ እጅግ አስመርሮ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ በመግባቱ ፥ከእንግዲህስ በቃኝ ብሎ በወሰነበት ወቅት ኢሕአፓ ከሕዝብ ውሳኔ ተፃሮ መቆምን አልገፋም። ወደፊት በሁለቱም ሥፍራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኖሮ ህዝብ ለህዝብ መልካም ትስስር እንዲኖራቸው ሊረዳ የሚችል እርምጃ ይሆናል ብሎ ያመነበትም ነበር።

በጀበሃና በሻዓብያ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሻዓቢያ የበላይነት ተጠናቆ የኢሳያስ አምባገነንነት በተረጋገጠበት፥ በወዲያ ፋሽስታዊው ደርግ በዚህ የኢሳያስ አምባገነንነት ጨርሶ ለዴሞክራሲ መስፈን አደገኛ ጠንቅ በሆኑበት ፥ የህዝቡም ፍዳ አላባራ ባለበት፥ ኢሕአፓ እንደ ድርጅት ሁኔታውን በጥልቀት መርምሮና ገምግሞ ጦርነቱ እንዲቆምና ሰላማዊ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ከኢትዮጵያ ጋር ኢርትራ ተመልሳ በፌደሬሽን ትስስር እንድትፈጥር የሚል አቋም ወስዶ ነበር። ሀቁም ይህ ነበር። ኢሕአፓ የኢሳያስን የቕኝ ግዛትነት ጥያቄ ሆነ የወያኔን የመገንጠል ቧልት የደገፈበት ወቅት አልነበረም። በዚህም አቋሙ የተነሳ ወያኔም ሻዓቢያም በድርጅቱ ላይ ደም መፋሰስን ያስከተለ ከፍተኛ ጥቃት አድርሰውበታል።

ኢሕአፓ ዛሬም ድረስ የአስመራን አገዛዝ እውቅና አይሰጥም። በሟቹ በወያኔ መሪና በአምባገነኑ ኢሳያስ መካከል በነበረ የጥቅም ግጭት የተነሳ ባድሜን አስታኮ የተደረገውን ጦርነት አጥብቆ ተቃውሞታል። አቋም ወስዶም መግለጫ አውጥቷል። ወያኔም ሆነ የሻቢያው ኢሳያስ በከንቱ ህይወታቸው ለተቀጠፉት ሁሉ ተጠያቂዎች መሆናቸውንም ተናግሯል። በወያኔዎች ጥቅም ላይ ተመስርቶ በኤርትራውያን ወንድሞቻችን ላይ የተደረገውን ኢሰብአዊ ከአገር መባረርም ተቃውሟል። በነዚህና በመሳሰሉት ኢሕአፓ በወሰዳቸው ጠንካራና ግልፅ አቋሞች ጠላትነቱ ከሻአብያ እንጂ ከኤርትራ ህዝብ እንዳልሆነና እንዳልነበረም ቁልጭ ባለ መልኩ አሳይቷል።

ኢሕአፓ አገር ማፍረስን ዓላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ከጭቆናና ከብዝበዛ ተላቆ ዴሞክራሲያዊት ሥርዓትን እንዲመሰርትና የነፃነት አየር ከዳር እስከዳር የሰፈነባት አገር ሆና በሁሉም መስክ እራሷን ገንብታ እንድትገሰግሥ ነበር ራእዩ። ዛሬም ይሄው ነው። መስዋእትነቱም ሁሉ የተከፈለውና ዛሬም ድረስ እየተከፈለ ያለው ለዚሁ ነው።

እናም ኢሕአፓን ከሕዝብ ነጥሎ ለማግለል በሚል እሳቤ የደርግ ኢሰፓ ርዝራዦች፥ የወያኔ ዘረኛ አፈቀላጤዎች ፥ ጎጠኞችና ሌሎችም ወሽካቶች እያደረጉ ያሉት ፍሬ ቢስ ፍብረካዎች እጅጉን ከእውነት የራቁና ውሃ የምይቋጥሩ ከመሆን አያልፉም።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለበለጠ መረጃ አንባቢያን የድርጅቱን (ድረ ገፅ EPRP.com) ይጎብኙና የድርጅቱን ልሳን ዴሞክራሲያ ቅፅ 15 ልዩ እትምን እንጋብዛለን። በዚያውም “ ማን ያውራ የነበረ” የሚለውንም አምድ 11.2 ና 11.3 ይመልከቱ።

መልካም ንባብ!!

ይቀጥላል…..