- ምንጭ – ቢቢሲ/ አማርኛ

በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙት የተለያዩ ሃገራት ላይ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሶማሊያ መንግሥት ምስጋና ተችሯቸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስት ዐብይ አህመድ አስተባባሪነት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ፋርማጆና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ ጥዋት በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ የተገናኙ ሲሆን በሃገራቱ ላይ ለተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከርን መፍትሄ ማምጣት ላይ ተወያይተዋል።
•“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁ ስኬት ብዙ ሰው በተስፋ እንዲኖር ማድረጋቸው ነው” ዶ/ር ዮናስ አዳዬ
ይህንንም ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫም ” የሶማሊያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሁለቱን መንግሥታት ስብሰባ በማሳለጥ ለነበራቸው ሚና እናመሰግናለን” የሚል ነው።
በትናንትናው ዕለት ናይሮቢ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር አብረው ሲሆን የሁለቱ ሃገራት መንግሥታትም እንዲወያዩ ጫና ሳያደርጉ እንዳልቀረም ተዘግቧል።
የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ላይ የነበሩ ሲሆን ይህም ሁለቱ ሃገራት በሚጋሩት የባህር ድንበር ላይ ያለው አወዛጋቢው የጋዝ ክምችት ይገባኛል ጥያቄ ነው።
በዚህ እግድ በተጣለበት የጋዝ ስፍራ ነዳጅ እያወጣች ሸጣለች በማለት የምትከሰው ኬንያ ባለፈው ወርም አምባሳደሯን ከሞቃዲሾ አስወጥታለች።
ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ ኃገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋርጦ ነበር።
የሁለቱ ኃገራት መሪዎችን ስብሰባ ተከትሎ በተላከው ጋዜጣዊ መግለጫም ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው ተገልጿል።
•በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት
“ሁለቱ መሪዎች ፍሬያማ የሆነ ስብሰባን አከናውነዋል። ሃገራቱ ግንኙነታቸውን ለማደስና ለማጠናከርም ከስምምነት ላይ ደርሰናል” በሚልም ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት የተሰጠው መግለጫ ያትታል።
ሶማሊያ በባህር ድንበሩ ላይ የሚገኘውን የጋዝ ክምችት ይገባኛል ጥያቄ ለአለም አቀፉ ፍትህ ፍርድ ቤት ያቀረበች ሲሆን ጉዳዩም እየታየ ነው። የየሃገራቱ አምባሳደሮች መቸ እንደሚመለሱም ቀነ ገደብ አልተጠቀሰም።
