6 ማርች 2019

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 91,000 መድረሱን፣ ከነዚህ መካከል በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ግጭት የተፈናቀሉት ደግሞ ከ50 ሺ በላይ እንደሚሆኑ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እነዚህ ተፈናቃዮች በተለያዩ አካባቢዎች በ13 ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፖችና በግለሰብ ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬከተሩ፣ ጊዜያዊ እርዳታ ለማድረግ ከፌደራል መንግሥት ጋር በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።
• “በምን ማስተማመኛ ነው የምንመለሰው” የሞያሌ ተፈናቃዮች
በግጭቱ ከሰዎች በተጨማሪ 116 ሺ ከብቶችም ስለተፈናቀሉ ለሰዎቹ ከሚቀርበው እርዳታ በተጨማሪ ለከብቶቹም መኖ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
“ግጭቱ ሁሉንም ተፈናቃዮች ቤት ንብረት አልባ አድርጓቸዋል” ያሉት አቶ አሰማኸኝ፣ በሁለቱ ዞኖች በአጠቃላይ 5,600 ቤቶች መውደማቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት አጋር አካላትን በመፈለግ የተጎጂዎቹን ቤት ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አክለዋል።
በአቶ አሰማኸኝ ገለጻ እያንዳንዱን ቤት ለመሥራት በአማካይ 70,000 ብር ያሰፈልጋል። ስለዚህም የወደሙትን 5,600 ቤቶች ለመገንባት 392 ሚሊዮን ብር ያሰፈልጋል።
• የማንነት ጥያቄዎች የጎሉበት የአማራ ክልል ከተሞች ሰልፍ
ከተፈናቃዮቹ መካከል ሴቶችና ህጻናት እንደሚገኙ ገልጸው “ሁሉንም ነገር ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም በግጭቱ የተፈናቀሉ ከ50 ሺ በላይ ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንደሚያደርጉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩት ችግሮች ዳግመኛ እንዳይከሰቱ በርትተን እየሠራን ነው ብለዋል።
አብዛኞቹ ተፈናቃዮች አርሶ አደሮች በመሆናቸው የመኸር ዝግጅት ከመድረሱ በፊት ቤታቸውን ሠርቶ ለመመለስ የታሰበ ሲሆን፣ በ30 ሚሊዮን ብር ቆርቆሮ ተገዝቶ ሥራው ተጀምሯል።
አራትና ከዚያ በታች ቤተሰብ ያላቸው ግለሰቦች ከነበርና መስኮቱ ባለ 43 ቆርቆሮ ቤት ይሠራላቸዋል። ከአራት በላይ ቤተሰብ ያላቸው ደግሞ ባለ 63 ቆርቆሮ ቤት እንደሚሠራላቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
እስካሁን ከ50 በመቶ በላይ የሚሆው (ከ150 ሺ በላይ ቆርቆሮ) ተገዝቶ ወደ አካባቢው መላኩን ገልጸዋል። ቤቶቹን ለመሥራት የሚያስችል የእንጨት ግዥ የሚያከናውን ኮሚቴ ወደአካባቢው ተጉዟል።
አቶ አሰማኸኝ “በአጭር ጊዜ ቤቶቹን ሠርተን ዜጎቹን ወደቀያቸው እንመልሳለን” ብለዋል።
የገንዘብ መዋጮን በተመለከተ ከተለያዩ አካላትን ድጋፍ ተጠይቆ እስካሁን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሰበሰብም “በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈለገናል” ብለዋል አቶ አሰማኸኝ።
