March 7, 2019
በኦሮምኛ አንድ ድንቅ ተረት አለ፡፡ በአንድ የኦሮሞ መንደር ውስጥ ሮቤል መገራ የሚባሉ ጥበበኛ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን የሁለት ጎረቤታሞች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ ያያሉ፡፡ እኒህ ጥበበኛ ሽማግሌም «እነዚህን ውሾች እንገላግላቸው፤ ያለበለዚያ ችግራቸው ለሁላችንም ይተርፋል። በዓለም ላይ ችግር የሚነሣው ከአጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ ውሾች የተነሣ ነው» ይላሉ፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሽማግሌዎች እና መንገደኞችም በሽማግሌው አባባል ተገርመው «ሁለት ውሾች ተጣልተው ምን ሊያመጡ ነው» እያሉ ሳቁባቸው፡፡ በዚህ መካከል ከሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል አንድ ልጅ ወጣና የውሾቹን ጠብ ተመለከተ፡፡ የእርሱ ውሻ የተበደለ ስለመሰለው ፍልጥ አምጥቶ ያኛውን ውሻ ደበደበው፡፡ ወዲያውም ከሌላኛው ቤት ሌላ ልጅ ወጣና ያኛውን ውሻ መደብደብ ጀመረ፡፡ ነገሩ ወደ ሁለቱ ልጆች ተዛመተና በውሾቹ ምትክ ልጆቹ ይደባደቡ ጀመር፡፡

ሽማግሌውም «እባካችሁ እነዚህን ልጆች አስታርቁ!» አሉ፡፡
በሥፍራው የነበሩትም «ተዋቸው! ይዋጣላቸው!» ብለው እንደ ቀልድ አለፉት፡፡
ልጆቹ እየተደባደቡ እያሉ የአንዱ እናት ብቅ አለች፡፡ ወዲያውም ያኛውን ልጅ በፍልጥ ታንቆራጥጠው ጀመር፡፡ የልጇን ጩኸት የሰማቺው ሌላዋ እናትም መጣች፡፡ የልጆቹ ጠብ ቀረና ድበድቡ በሁለቱ እናቶች መካከል ሆነ፡፡
ሮቤል መገራም «እባካችሁ ይህ ጠብ ተዛምቶ ሁላችንንም ከማካተቱ በፊት ገላግለን እናስማማቸው» አሉ፡፡
ተመልካቾቹ ግን የሁለቱን ጠብ እንደ ነጻ ትግል እያዩ ይዝናኑ ነበር፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎችም «ሁለት ሴቶች ተጣልተው የት ይደርሳሉ!» እያሉ ንቀው ተውት፡፡
በግርግሩ የከበቡትን ሰዎች እየጣሰ አንድ ሰው ወደ መካከል ገባ፡፡ ያንደኛዋ ባል ነበር፡፡ እንዴት ሚስቴን ትመቻታለሽ ብሎ ያቺኛይቱን ሴት መደብደብ ያዘ፡፡ ይኼኔ ነገሩን የሰማው ሌላኛው ባልም ሲሮጥ መጥቶ ድብድቡን ተቀላቀለ፡፡ ሮቤል መገራ አሁንም «እባካችሁ ገላግሏቸው፤ ይህ ጠብ ለሀገር ይተርፋል» ሲሉ ተናገሩ፡፡ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡
ሁሉም የራሱን ልጅ፣ ሚስት እና ቤት ብቻ ይጠበቅ ነበር፡፡ ወንዶቹም ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እንዳይገቡ ይቆጡ ነበር፡፡
የሁለቱ ባሎች ጠብ ተባባሰ፡፡ ሕዝቡም ከብቦ ያይ ጀመር፡፡ በዚህ መካከል የሰውዬው ወገኖች ነን ያሉ ያንደኛዋን ባል መደብደብ ያዙ፡፡ ተመልካች ሆነው ከቆሙት መካከል የዛኛው ወገን ነን የሚሉ ደግሞ ያኛውን ይዘው ይደበድቡ ጀመር፡፡ እንዳጋጣሚ የሁለቱ ሰዎች ጎሳች የተለያዩ ስለነበሩ ጠቡ ወደ ጎሳ አደገ፡፡ ዱላ እና እጅ ብቻም ሳይሆን የጦር መሣርያም ተጨመረበት፡፡ ቤት ንብረት መዝረፍ፣ ማቃጠል እና መግደል እየተባባሰ መጣ፡፡ መንደሩም የጦርነት አውድማ ሆነ፡፡ ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት ሰዎች ሞቱ፡፡
በስንት መከራ ጠቡ ቆመ፡፡ ሮቤል መገራም አዘኑ፡፡ «ውሾቹ ሲጣሉ ብናስቆማቸው ኖሮ ጎሳዎቹ አይጣሉም ነበር!» አሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ ጉማ ተቀመጡ፡፡ በባህሉ መሠረት ለእያንዳንዱ ለሞተው ነፍስ ከሌላው ወገን ሰው ይገደላል ወይንም መቶ መቶ ከብት ይሰጣል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት መቶ ከብት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በሞቱት ምትክ ከሌላው ወገን ሰው ይገደልም ከተባለ በተጨማሪ አስራ ስድስት ሰዎች ሊገደሉ ነው፡፡ የሟቾቹም ቁጥር ወደ ሠላሳ ሁለት ከፍ ሊል ነው፡፡ ይህ ነገር ሽማግሌዎቹን አስጨነቀ፡፡
ይኼኔ ሮቤል መገራ ተነሡ፡፡ «ቅድሞ እኔን ሰምታችሁኝ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን እንጂ ስለ ሌሎች ግድ ስለሌለን ዕዳው በመጨረሻ እኛው ላይ መጣ፡፡ ውሾቹን ተው ማለት አቅቶን እዚህ ደረጃ ደረስን፡፡ ምንጊዜም ጦርነቶች የሚነሡት ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡ ጎረቤት እና ጎረቤት፣ ጎሳ እና ጎሳ፣ ንጉሥ እና ንጉሥ፣ ሀገር እና ሀገር፣ እስላም እና ክርስቲያን፣ መንደር እና መንደር፣ የሚጣላው ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡ የጦርነት መነሻ ውሾች ናቸው፡፡ ውሾቹ በአጥንት የጀመሩት ጠብ ሕይወት አስከፈለን፡፡ እነዚህ ውሾችኮ ከአጥንት በላይ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ውሾች ናቸው፡፡ ዓላማቸው አጥንት መጋጥ ብቻ ነው፡፡ አገር ቢጠፋ፣ ሕይወት ቢጠፋ፣ ንብረት ቢጠፋ እነርሱ ምን ጨነቃቸው፡፡ እንዴት ከአጥንት በላይ ማሰብ የማይችሉ ውሾች ይህንን ሁሉ ዋጋ ያስከፍሉናል? «እነዚያን ውሾች ለያዩዋቸው ስላችሁ ሁላችሁም የእናንተ ውሾች አለመሆናቸውን ብቻ ነበር የምታዩት፡፡ ሌሎች ተበጥብጠው እኛ እንዴት ሰላም እንሆናለን? ሌሎች እየተዋጉ እንዴት እኛ በደኅና እናድራለን? ሌሎች ተርበው እንዴት እኛ እንጠግባለን? የማይሆን ነገር ነው፡፡ በሉ አሁንም ሌላ ሕይወት ማጣት የለብንም፣ ከብቶቻችንንም ማጣት የለብንም፤ ከሁለቱም ወገን የአንገታችሁን የብር ማተብ አምጡ፤ ያንንም ሰብስባችሁ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፣ ሁሉም ጦሱን ይውሰድ፤ እናንተ ግን ይቅር ተባባሉ!» ብለው አስታረቋቸው ይባላል፡፡
ምንጭ – የዳንኤል ክብረት ዕይታዎች።
