March 7, 2019t
ከላይ የሰቀልከው ብታገኘው ወርዶ
ጠንቀቅ በል ወገኔ አታድረገው መርዶ ።
ሃያ ሰባት ዓመት ሲሸረብ የኖረ
በዚህ በአጭር ግዜ ገሎ ለቀበረ ።
ብቻ በል ተቀበል ሲሉህ እንዳትሰማ
ቢኖር አይግረምህ አይምሮው ጠማማ ።
ደሞ በዚህ ሰዓት ብታገኘው ወርዶ
በዘር ተሸብሽቦ እራሱን አዋርዶ።
አትደንግጥ ብታየው ጭራውን ሲቆላ
ለንዋይ የሸጠ እራሱን የበላ።
ሞልቷል በየ ደጁ ለከርሱ የሚሞት
ገና ሳይናገር ሃሳቡ የሚሸት ።
ሽቅብ የሚገፋው ላንቃው የቀረና
ቅርሻት የበዛበት ገና ብዙ አለና ።
ድንገት ብታገኘው ቢያሰማህ እሮሮ
ኖሮ የሚመስለው ስንት አለ ቆርቆሮ ።
አጥንት የሚቆጥር ወገኑን የበላ
ለስጋው ያደረ ህሊናው የተላ ።
አጥንቱን የሚያሸት ትልቅ ነገር ትቶ
ስንት አለ መሰለህ ሕሊናው ቡትቶ
እንቅፋት የሚሆን እሱ እራሱ ሞቶ ።
ጭልጥ ያልክ ደንቆሮ ማሰብ የተሳነህ
ካልሆንክብኝ በቀር ምነው ታሽካካለህ።
ማሰብ ማገናዘብ ካልመጣልህ ጭራሽ
ሆነህ ከምትቀር የእናትክን ጡት ነካሽ።
ግራ ቀኝህን ተመልከት የሚሉትን ስማ
ሁሉም ተጠራርተው ይሉሃል አሳማ ።
ያደረገህ እሱ ሃገር ሻጭ ነው ባንዳ
ማስተዋልም ጀምር እራስክንም አፅዳ ።
ጭራሽ እንዳትጠፋ ሆነህ ስብርባሪ
ግዜው ይሄኔ ነው ከሌለህ መካሪ ።
ከፊትህ የሚታይ ስንት ያለበት ተስፋ
በኔ በአንተ ግጭት አንገቱን ሲደፋ ።
ምን ይሆን መልሳችን ምንስ ልናወራ
በኔ በአንተ ግዜ ፍቅር ተሰባብራ ።
ሲታወክ ጤናቸው ሲደማ አካላቸው
ህፃናቱ ወድቀው ማልቀስ ሲሳናቸው ።
እስኪ ትንሽ ስማ እነማን ምን አሉ
ሰበኩ ወይ ህብረት ባንድነትስ በሉ ።
ምነው መደናበር ማላገጡን ብትተው
ለአንተም ለወገንህ የሚጠቅም እሱ ነው።
አስተውል ተመልከት ዙሪያ ገባውን
ጠግበው ሲተፉብህ ግማት ቅርሻቸውን ።
ረሃብ ተሸክሞ መቼም ጥጋብ የለ
እነሱ ለበሉት አግሳ የሚልህ የለ ።
ከስርቻ ወጥተን በአደባባይ ሞቀን
ለዜግነት ክብር ሞኝ መስለን ታይተን
ማሰብ ስንጀምር ከቀረጢት ወጥተን
የዜግነት ትግል መንፈሱ ሲገባን
መባነን ስንጀምር መኝታው ሲበቃን።
ህልማችን እውን ሆኖ መተባበር ሲኖር
ያሰብነው ሲሳካ ጨለማው ሲሰበር ።
ያኔ ነው መተንፈስ መረጋጋት ኖሮ
የለውጡን እንቅፋት ጠራርጎ አባሮ ።
ፌብሩዋሪ 2019
ስቶክሆልም
ዝም በል ይሉኛል / ግርማ ቢረጋ /

ፈራ ወይ ገሞራው ወዴት ተሸሸገ
ጥበብን በብዕር ወልዶ ያሳደገ ።
ምነው የትስ ገባ ,,, ሸሸ ወይ ገሞራው
ለሃገሩ ክብር ሞትን የማይፈራው ።
ብዬ በተናገርኩ ዝም በል ይሉኛል
እኮ እንዴት ዝም ልበል
ያጣሁት ታሪኬ ህይወቴ ነው ሀይሉ
እኮ እንዴት ዝም ልበል ?
የታሪኬ መግቢያ መዝጊያውም እሱ ነው
የፈጠረው አምላክ ነብሱን ብቻ ይማረው ።
/ ስቶክሆልም /
ኖቬምበር 2018
711
