March 9, 2019

መጀመሪያ ሀገር ትኑረን፤ እሷ ካለች ከተማ እንሠራለን! (መንግስቱ ዲ አሰፋ)

ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታዋ (state formation) ያላለቀ “ጥንታዊት ሀገር” ናት። የፖለቲካ ታሪኳ ደግሞ በመዋቅራዊ አድልዎች እና አሠራሮች ነው ተጀምሮ እስካሁን እየተጓዘ ያለው። አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ አልተፈጠረም። ችግሩ ሰፊ እና ታሪካዊ ነው። መዋቅራዊም ነው። እንቅርት ላይ ጆሮ ዳግፍ እንዲሉ ደግሞ አብረን ሆነን ተለያይተናል። አንድ ቋንቋ እየተናገርን ፍላጎታችንን አንዱ ለሌላው ማስረዳት አቅቶናል። በመሪዎቻችን ተከድተናል፣ ተገድለናል፣ ተለያይተናል። በሀገር ልጆች ተብልተናል፣ ተባልተናል። ቅኝ ግዛት ባንገዛም አንገት ቀና የሚያደስደርገን ዳቦ እንኳን የለንም። ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት የሚያኮራንን ነገር አልሠራንም። ታሪኩንም እንሻማለን። ወይ እዳ! ድሮ አንዱ ሌላውን ያበላ ነበር።

ምን ይሻለናል
ሰው ያስፈልግናል። አሳቢ ሰው ያስፈልገናል። የ መላ አማልክት ያረፉበት፣ የመፍትሔ ዛር ሹክ የሚለው አሳቢ ሰው ያስፈልገናል። መንገድ የሚያሳየን፣ ሕዝብ የሚያረጋጋ፣ የጠወለገ ተስፋን የሚያለመልም ሰው…ያስፈልገናል። Ideologue የሆነ ሰው ያስፈልግናል።

ሰው ያስፈልገናል። ሐሳብን ሥጋ የሚያለብስ ሰው ያስፈልገናል። በቃ አለ አይደል ልክ እንደ ጦር መሪ በጥንቃቄ መንገድ ቀይሶ የሚመራ? Strategist የሆነ ሰው ያስፈልገናል።

አዴፓ እና ኦዲፒ

ጫጉላችሁን ጨርሳችሁ ይዋጣልን ዓይነት አያዋጣም። ያመንናችሁ አንድ እናደርጋችኋለን ስትሉን እንጂ የትግል ጓዶቻችሁን ራሱ እኮ እንደ ከዳችኋቸው የረሳን እንዳይመስላችሁ! በፍጹም! የማይታረቁ ሕልም አራማጅ ጽንፈኞች ቡድን ተጽዕኖ ሥር እንደወደቃችሁ እያየን ነው። በሁለቱም በኩል። የፖለቲካ ኃይል አሰላለፋችሁን፣ ሊፍት በር የሚያንኳኳ ካድሬያችሁ ጽፎ የሚያስነብበንን መግለጫችሁን ወዲያ በሉልን። በራችሁን ዘግታችሁ ተነጋገሩ። ኢትዮጵያን እንዴት እናድናት በሉ። Ideoluge እና Strategist ቅጠሩ። የሀሳብ ንጥፈታችሁ ከልክ አልፏል። የሀሳብ ጠኔ የአክራሪነት መነሻ ነው። ለድርድር አልቀርብም…የኔን ምንጥስዬ ከፍታ አስጠብቃለሁ ዓይነት ረብ የለሽ ጩኸታችሁን ታቆሙት ዘንድ በለውጡ ሥም እማጠናችኋለሁ! እንደው በለውጡ…pleaaase! አቋማችሁን ሀገራዊ ማድረግ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ የእርምት እርምጃ ነው። የጦርነት ድቤያችሁን አትደልቁብን። የጦርነት አስከፊነት ያልገባው ሰው ስለሌለ ተጨማሪ ትምህርት አስፈላጊ አይደለም።

እርስ በርስ እንደታባላን የሚገልጹ ስንኞችን የተቀኘነው እኛው አይደለንም ወይ?

<<ወላጅ ለሞት ሲጣደፍ ጨቅላ ሕጻናት በትኖ
ዕድሜ ባዛለው ጉልበቱ አያት ከልጅ ልጅ ታግሎ።
በአረጋዊነት ዘመኑ ማረፍ መጦሩ ቀረና
መውለድ እርግማን ሆነ ጽጋ መሆኑ አበቃና>>

ለሌሎች ፖለቲከኞች

እኛ የምናውቀው ፖለቲካ የሸፍጥ ፖለቲካ ነው። ሴራ፣ ግድያ፣ መጠላለፍ፣ መጠፋፋት። ሴራን ይኸው ብላችሁ ልታሳዩን አትሞክሩ። ስናየው እና ስንሰማው እናውቃለን። እንደው በእውቀታችሁ አምላክ ልለምናችሁ፣ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ከዚህ ሴራ ወሬ ውጪ ሀሳብ ከሌላችሁ አትናገሩን። እንደው በምትወዱት ሥልጣን አምላክ፣ በሆዳችሁ አምላክ ሴራ እየሸረባችሁ፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጫችሁ፣ በጅምላ እየፈረጃችሁ ሕዝብን የምትሳደቡ ሰዎች…ልለምናችሁ አደብ ግዙ። ብሔረተኝነት ዳቦ አይሆንም። ትምህርት ቤት አይገነባም። ጤና ተቋም አይሠራም። ኢትዮጵያዊነትን ጨምሮ ማለት ነው። ያው ማንነት ነው። እሱን ፖለቲሳይዝ ማድረግ ሙያህ የሆነው ግን ጊፍቲ ክሪሽና መች ረግማህ ነው ባዛኚቱ?! እየመረጥክ የምትተች፣ እየለየህ የምታዝን ምን ይሉት ውርደት ነው?

ዛሬ ከተማን ለመቀራመት ነገ ሀገር እናጣለን። በተለይ በተለይ የኦሮሚያ እና የአማራ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች አንድ ነገር ላስታውሳችሁ። ታሪካችን የመቃቃር 150 (in modern Ethiopia ማለት ነው) ዓመታት ናቸው። የማይታረቁ ሕልሞች አሉን። በቃ የማይታረቁ ከሆነ አንተ ትሻለኛለህ ብለን ሕልሞቻችንን እናመቻምች። 8.2 ሚሊዬን አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልገው ዜጋ ይዘን እንዴት ከተማን እንሻማለን? እሳቶቻችን አልበረዱም። ሥራ ያልተፈጠረለት ወጣት ወሮ በላ እየተፈጠረ ክልሎቻችንን እያመሱ ናቸው። ፌዴራል መንግሥት ደክሞ ክልሎች ጠንቻቸውን እያፈረጠሙ ናቸው። አንድ ነገር ጣል ላደርግ። ከፌዴራሊዝም ተፈጥሮአዊ ሕጽጾች መካከል አንዱ የሥልጣን ሥርጭት አለመጣጣም ነው (ወይ ማዕከላዊ መንግሥት ወይ ክልሎች ጡምቻቸው ይፈረጥምና) Shared rule and self rule የሚባለው ይዛባል። ያ አደጋ ነው። ክልል ጦር እየተከፈተብኝ ነው የሚል አቤቱታን ሲያቀርብ “ወታደር አላቸው እንዴ?” ካልክ መልሱን እዚያ ውስጥ ፈልገው። አልተዛባም ወይ? ችግርስ አይፈጥርም ወይ?

እኔ ልቤ ልክ የዛሬ 8 ወር ገደማ እንዳለው ነው ያለው። አብይን ለመነቀስ አልዳዳኝም። የማያውቀውን የሚነቀስ ሰው አይደለሁም። ሰዎች ደካማ ፍጡራን እንደሆኑ፣ ከድካማቸው ከተማሩ ደግሞ የተሻሉ እንደሚሆኑ የማምን ሰው ነኝ። አብይ ሥልጣን ሲይዝ ” we’ve found a leader whom we measure against a good yardstick, his words” የሚል ቃል ለ The Economist መስጠቴ ትዝ ይለኛል። Tom Gardner is my witness. ዛሬም የአቅም ውስንነት እና የአሠራር ክፍተቶችን እንጂ ሴራ እና ሸፍጥ አይተየኝም። ሴራ እና ሸፍጥን ማወቅ ከፈለግክ ዝም ብለህ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ታሪክ አንብብ። መልኩ ሌላ ነው። እኔ ሴራ እና ክህደትም አይሰማኝም። የምጠበቀው የተረጋጋች እና ተቋማዊ ቁመናዋ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚበቃ ኢትዮጵያን እንዲፈጥርልኝ ነው። የተለየ ጥቅም እና ፍላጎት የለኝም። የአሠራር ችግሮች አሉ? አዎ። የአቅም ውስንነት አለ? ድብን አርጎ! በኔ ግምት ከቤተመንግሥቱም ሀሳብ ነጥፏል። ሀሳብን አካል የሚያለብሰው ሰው እንደሌለ እየተሰማኝ ነው። There’s no ideolugue. Neither a strategist. አብይ ቶሎ ሊያስብበት ይገባል። መካሪ/አማካሪ የለውም። Look at his Chief of Staff. His Ambassadors are nobodies. ከዚያ በተረፈ ግን ሥሜት ጊዜያዊ ነው። ሥሜታዊ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚም እንደዚያው። ችግርን ትልቁ ምስል ስናየው የማይታረቁ ሕልሞቻችን ስበታቸው ተካሮ ሀገራዊ አንድነት ድባቡን ደመና በክፍፍል ነፋስ እየተወሰደ ነው። ሰበር ዜና ራሱ እየሰማን ነው። ዝም ብሎ በአጋጣሚ የሚሆን ነገር የለም። በዚያም ጎራ ደግሞ እሳት አለ። የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ አዲስ መልክ መያዙ ነው እንግዲ። ወደ ዝርዝር አልገባም።

በመጨረሻም

ሁሌም በሀሳብ እና ፍላጎት ልዩነቶች ውይይትን እንልመድ። ሚዲያ እያነፈነፍን የሴረኞችን ሴራ አንጋት። ለኛ የሀገር ጉዳይ ስሜት ሊሆን ይችላል። ሴረኛ ግን ትችቱ በስሌት ነው። ተቃውሞው በስሌት ነው። ሀዘኑም ሰብዓዊነት ሳይሆን የፖለቲካ ገበያ ነው። መፈናቀል እና ግዲያ ለሱ asset ናቸው። ችግር ላይ ተረማምዶ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልግ ፍጡር ነው። ፈውስ እንጂ ሌላ ምን እመኝለታለሁ?!
የኢትዮጵያ ተስፋ በያንዳንዳችን እጅ ነው ያለው፤ በሰውኛ አነጋገር ማለት ነው። ዘመኑን የሚመጥን የሀሳብ ፍጭት ያለበት ፖለቲካን ለማካሄድ እንዘጋጅ። ሁሌም ጭለማ እና ተስፋ መቁረጥ አይሰማን። ሁሌም ጥላቻን እናስወግድ። አዴፓ እና ኦዴፓ ራሳችሁን ፈትሹ! የሕዝብን ጥቅም እንጂ የሌላን ጫና ችላ በሉ! ታሻግሩናላችሁ ብለን ነው እንጂ የጮርቃ ካድሬዎቻችሁን መግለጫ በየተራ ልታስግቱን አንፈልግም። እንዳልኩኣችሁ ተነጋግሩ። አብይ ብቻውን አሳቢም (ideolgue) እና ሀሳብን አካል የሚያለብስ (strategist) ሊሆን አይችልም። ከፈለጋችሁ ድርጅታችሁ የገፈቸው እና ዳር የያዙ ግን ብቃት ያላቸው፣ የተማሩ፣ ልምድ ያላቸው እና ሀገር የሚወዱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሰዎች በዓለም ላይ ሞልተዋል እና ቅጠሩዋቸው። ሀገርን አድኑ። እሷ ካለች ከተማ እንሠራለን። ከተማ እየተቀራመጥክ በብዙ መስዋዕት የተጠበቀች ሀገርን አታፈርስብን! ልቡና ግዛ!

Image may contain: 1 person, stripes