ከቁም ነገር ዝግጅት ክፍል የተወስደ
ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመረው የበጎ ሰው ሽልማት በየዓመቱ የሚካሄድ ፕሮግራም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ ስለዝግጅቱ በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለፕሮግራሙ አዘጋጆች ከጋዜጠኞች የቀረበ አንድ ጥያቄ ነበር፡፡ ‹ የበጎ ሰው ሽልማት ከሚሸልማቸው ዘርፎች መሀከል የዓመቱ የሰላም ሰው የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ የለም፤ ለምንድነው?› የሚል፡ ፡ ከፕሮግራሙ አዘጋጆች መሀከል አንዱ የሆነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹ ለዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የዓመቱን የሰላም ሰው፤ ለመሸለም ዝርዝራችን ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰላም ሰው ብለን የምንሸልመው መስፈርቱን የሚያሟላ ሰው ባለማግኘታችን ልንሸልም አልቻልንም፡፡››
ሀገሪቷ ካሏት 90 ሚሊየን ህዝብ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት አንድም የሰላም ሰው መፍጠር አለመቻላችን ማህበረሰባችን ህመም ላይ መሆኑን አመላካች ይመስላል፡፡ ያስፈራል! በእርግጥ ያስፈራል!
ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ ይኖር የነበረ ህብረተሰብ በድንገት ለፍጅት ሲጠራራ ማየት ያስደነግጣል፡፡ በሀይማኖታችንም ሆነ በባህላች ያልታየ፤ ያልተሰማና፤ ፈፅሞ ይሆናል ብሎ ለመገመት የሚያስቸግሩ ነገሮች ከጥቂት ወራት ወዲህ በሀገራች ክልሎች እዚህም እዚያም እያየን ነው፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች በተፈጠሩ አለመግባባቶች የሰው ህይወት ከመጥፋት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ህግን ለማስከበር ሀላፊነት ባለበት የፀጥታ ሀይልም ሆነ በህብረተሰቡ መሀከል የተፈጠረው አለመግባባት መተኪያ የሌለው የሰው ልጅ ህይወትን ቀጥፏል፡፡ የዚህ አይነት ችግር በሀገሪቱ ሲከሰት የአስታራቂነት ሚናቸውን መወጣት የነበረባቸው አካላት በራቸውን ዘግተው ሁኔታውን እያዩና እየሰሙ ዝም ማለታቸው አሳሳቢ ነው፡፡
ማንም ሰው የማይሞትባት ወይም የማይገደልባት ኢትዮጵያን መገንባት የሁላችንን ሀላፊነት ነው፡፡ በተለይም የሀይማኖት አባቶችና ምሑራን፤እንዲሁም የኪነጥብብ ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከፍ ያለ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ የሚገባበት ሰዓት ላይ እንገኛለን፡፡
በቅርቡ በመንግስት ተመሠረተው የሰላምና የእርቅ ኮሚሽንም ገለልተኛና በጉዳዩ ላይ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸውን ሰዎች ከማካተቱ አንፃር የተአማኒት ችግሩን በአፋጣን ፈትቶ ወደ ስራ ሊገባ ይገባል እንላለን፡፡፡
ከቁም ነገር ዝግጅት ክፍል የተወስደ
