

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዲጠናከር ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው የንግድ ግንኙነት ሊጀመር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ
On Mar 18, 2019469
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2011(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዲጠናከር ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው የንግድ ግንኙነት ሊጀመር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።
አሜሪካ በሚገኘው የኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህሩና የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ብዙ ታሪክ እንዳለው ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ አሁናዊው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት የተሻለ እንደሚጠናከር እምነታቸው የጎላ ሲሆን÷ ሁለቱ ህዝቦች በሁለት ሀገር የሚኖሩ አንድ ሀዝቦች ናቸው በማለት ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት ኤምባሲዎቻቸውን አዲስ አበባና አስመራ ላይ መክፈታቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ዳግም ለመጠናከሩ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
ፕሮፌሰር ብሩክ ይህን የመንግስት ለመንግስትና የቆየ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ በጥቅም ለማስተሳሰር የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት ባይ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ አባይ ይመር በበኩላቸው፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲሻሻል ለማስቻል በሀገራቱ መካከል የነበረውን የጥላቻ ግንብ መፍረስ ከበርሊን ግንብ መፍረስ ጋር ያዛምዱታል።
እንደ አዲስ መልክ የተጀመረው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት የታሰበውን ውጤት ያመጣ ዘንድ ግን የሀገራቱ ቀጣይ አካሄድ ጥንቃቄ የሚሻው መሆን እንዳለበትም ይገልፃሉ።
አሁን ላይ ህብረተሰቡ በኢትዮ ኤርትራ የግንኙነት መስመር ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ፣ በየጊዜው የሚደረጉ ስምምነቶች ለህዝቡ በግልፅ ይፋ ማድረግና ጊዜን ጠብቀው መብራራት እንዳለባቸውም ነው አቶ አባይ የሚናገሩት።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአንድ አመት የዲፕሎማሲ መንገድ ከኢትዮ ኤርትራም አልፎ የምስራቅ አፍሪካን ጂኦ ፖለቲክስ በአዲስ መንፈስ ያስተሳሰረ መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።
በስላባት ማናዬ
