March 18, 2019

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2011(ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሞኑን በአሜሪካ፣ በጃፓን እና በሲንጋፖር ቡናን፣ እንቁላልንና እንጉዳይን በተመለከተ አዲስ ጥናት ወጥቷል።
ታዲያ በነዚህ ጥናቶች ውስጥ ከዚህ ቀደም ይጠቅማሉ ተብለው በተመራማሪዎች የተጠቀሱ የምርምር ውጤቶች በዚህኛው ጥናት በተቃራኒው ቀርበዋል።
ከነዚህም መካከል የኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርስቲ እንቁላል በተመለከተ ይፋ ያደረገው ምርምር አንዱ ነው።
ዩኒቨርስቲው እንቁላል ከፍተኛ የሆነ የኮሌስትሮል ይዘት እንዳለው አስታውሶ፥ በዚህም ምክንያት በልብ ህመም የመያዝ ዕድል እንደሚጨምር አትቷል።
በጥናቱም በየዕለቱ ግማሽ እንቁላል የሚመገብ ሰው በ6 በመቶ በልብ ህመም የመያዝ እድሉ እንደሚጨምርና 18 በመቶ ያለጊዜ መሞትን እንደሚያስከትልም ገልጿል።
ሁለተኛው ጥናት ደግሞ በቡና ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ቡና የፕሮስቴት ካንሰርን ዕድገት ይከላከላል ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ በቡና ላይ አሁን የተገኘው ውጤት ገና በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሲንጋፖር ላይ በተካሄደው ሦስተኛው የእንጉዳይ ጥናት ደግሞ በ600 አዛውንቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ሰርተዋል።
በጥናቱም እንጉዳይ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚከሰት የመርሳት በሽታን እንደሚከላከል ተጠቅሷል።
በሳምንት ሁለት መጠነኛ እንጉዳይ የሚበላ ሰው ከማይበሉት ይልቅ 57 በመቶ የመርሳት በሽታን እንደሚከላከሉ ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ምንጭ፦ሲጂቲኤን
