March 18, 2019 e

የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራ ለድርድር አይቀርብም:- የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት
የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ሕገ ወጥ ግንባታዎች ከፈረሱባቸው የማህበረሰቡ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ጠይባ ከእነዚህ የማህበረሰብ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፣ መንግስት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት ስላለበት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሕገ ወጥ ግንባታዎችን በሕግ አግባብ እየተከላከሉ መሄድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ስራ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑና በፕላን እንዲመሩ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ከከተሞች ፕላን ጋር የሚቃረን ሕገ ወጥ ግንባታዎች ሕጋዊ አግባብ እንዲይዙ እየተሰራ ነው ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡

የኦሮሚያ ከተሞች በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባቸው ከተሞች መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ የከተሞች የልማት ስራ ሲሰራም ሆነ ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድ የብሔር ልዩነት በማድረግ አልተከናወነም፣ ለወደፊትም አይከናወንም ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን በእኩል ያገለግላቸዋል፤ የክልሉ መንግስት ብሔር ብሔረሰቦችም በሕጋዊ መንገድ ሰርተው ሀብት ማፍራት እንዲችሉ የማገዝ አቋም እንዳለው ም/ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ውስጥ ስህተት የተፈጠረ እንደሆነ የክልሉ መንግስት አጣርቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ በቤቶቹ ላይ ሕጋዊ መረጃ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል መረጃውን የማቅረብ ሙሉ መብት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሕገ ወጥ ድርጊቶች ከመሰራታቸው በፊት ማስቆም የተሻለ አማራጭ ነበር ያሉት ወ/ሮ ጠይባ፣ በሕገ ወጥ ግንባታ ንግድ ላይ የተሳተፉ የመንግስት መዋቅር አካላት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ አካላት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እንዲደናቀፍ ለበርካታ ዓመታት አብሮ የኖሩ ሕዝቦች እንዲጋጩና በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ እየሰሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ጠይባ ገልጸው፣ እነዚህ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በነዋሪዎቹ ላይ የመብት ጥሰት ያደረሱ የጸጥታ አካላት ላይ የማጣራት ስራ ተሰርቶ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል ም/ፕሬዝዳንቷ፡፡

ቤት ከፈረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ማጣራት ተደርጎ የድሃ ድሃ ለሆኑት የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡

እየተከናወነ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ለማደናቀፍና ለፖለቲካ ፎጆታ ማዋል የሚፈልጉ አካላት ጉዳዩን የብሔርና የሃይማኖት መልክ ለማስያዝ የሚያራግቡት ወሬና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚያካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ተቀባይነት እንደሌለውና የክልሉ መንግስት እነዚህን አካላት ለሕግ ለማቅረብ ይሰራል ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም አስቀድሞ ሕገ ወጥ ግንባታዎች እንዳይገነቡ የማድረግ ስራና ሕገ ወጥ ግንባታዎችንም ሕጋዊ አግባብ እንዲይዙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ወ/ሮ ጠይባ ገልጸዋል፡፡

የአሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ODP) ማዕከላዊ ጽ/ቤት የገጠር አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ የተወሰደው እርምጃ በሌሎች ከተሞች ከተወሰደው እርምጃ የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ አዲሱ አክለውም አንዳንድ አካላት ግን ይህንን ሁኔታ ለፖለቲካ ፍጆታ እያወሉት ነው ብለዋል፡፡