ምንጭ – ሪፖርተር


18 March 2019 ዳዊት እንደሻው
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራዉ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ዛሬ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት አራተኛዉ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እነዲራዘም ወሰነ፡፡
ለቆጠራዉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሰራጨት ቢጀመርም፣ እስካሁን ከትግራይ ክልል ውጪ ግብዓቶች እንዳልተጓጓዙ ለማወቅ ተችሏል ።
በተለይም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቆጠራ ኃላፊዎች በክልሉ አሁን ባለዉ ሁኔታ ለቆጠራዉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሰራጨትም ሆነ ቆጠራውን ማከናወን አዳጋች መሆኑን ሪፖርት ማድረጋቸውን ከምንጮች ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም ደቡብን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ክልሎች ሊደረግ የነበረዉ የስርጭት ሥራ በጊዜያዊነት እንዲቆም ተደርጓል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ስብሰባ በእነዚህና በክልሎች የቀረቡ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከተወያየ በኋላ ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ለሥልጠናው ተብሎ የተሰራጩ ታብሌቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሰበሰቡም ለኤጀንሲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መመሪያ ተላልፏል፡፡
