ኢትዮጵያን ቦዝኒያ አናድርጋት

አዲስ አበባን ለማትረፍ ከሳሪያቮ ትምህርት እንውሰድ
================================
የሰሞኑ የአዲስ አበባ እና በሀገሪቱ ዙሪያ የሚታየው ውጥረት እጅግ አስፈሪ እና ጥንቃቄ ሊሰጠው የሚገባ ነው። በእርግጥ ነው ኢትዮጵያ አትጠፋም ዘመነ መሳፍንት እና አናርኪ ግን በሀገሪቱ ሊነግስ ይችላል። በአዲስ አበባ ዙሪያ የምናየው ጤናማ ያልሆነ የከተማ አስተዳዳሪወች እና የክልል መንግስታት ተግባር የሚያሳስብ ከመሆን አልፎ የዜጎችን በሰላም የመኖር፣ እና ሰርቶ የመግባት ነጻነት እየተጋፋ ነው። የሚቀርቡ ምክንያታዊ መከራከሪያወች ከክልል ገዥወች እና ከከተሞች ከንቲባወች የእኛ የሚሉትን ሕዝብ ሊያሳምን ይችላል። በታሪክ እና በህግ አኳያ ግን የዜጎችን የመኖር መብት የሚጋፋ ነው። ይህ አድራጎት የዘር ፖለቲካ በነገሰበት እና የአካባቢ የዘር መሳፍንቶች ኃይል በያዙበት ጎራ ለመለየት እና ለጦርነት ለመጋበዝ ቀላል ምክንያት እየተፈጠረለት ነው። ከሁሉም በላይ ገንዘብ እና ወታደራዊ ድርጅት አዘጋጅቶ ወደምሽጉ ያፈገፈገ ህወሓት የተባለ ዘረኛ ባለበት የሁለት ድኩላወች ግጭት ለበይው እንዲያመች እንዳይሆን በጥብቅ ሊታሰብ ይገባል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ወር ባልሞላው ግዜ ከለገጣፎ፣ ለገዳዲ መፈናቀል (የዘር ማጽዳት ዘመቻ) ተሸጋግሮ ዛሬ እና በሰሞኑ የተከሰተው የሱሉልታ ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ብሎም ለሀገሪቱ ቀጣይነት ሌላ አደጋ እየመጣ ለመሆኑ ግፍ ከተቀበሉት እሪታ እና ለቅሶ ማየት ይቻላል። የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) አለማቀፍ ወንጀል ነው፡፡ በተለያዩ የአለማችን ጠርዞች ታይቷል አስቀያሚነቱ ሀገርን ጭምር ማፍረሱ መሆኑ ደግሞ የቅርብ ግዜዋ ዮጎዝላቪያ ትልቅ ምሳሊያችን እና አስተማሪ ልትሆን ይገባል፡፡

የዮጎዝላቪያ ጦርነት ጅማሮ

የ 1984 የክረምት ኦሎምፒክን ቦዝኒያ ሄርሶጎቪና ሪፖብሊክ ሳሪያቮ ከተማ አስተናገደች፡፡ ይህች ውብ የሆነች ህብረቀለማት ያላት ሪፖብሊክ እና ከተማዋ በአውሮፓ ከሚጠቀሱ በአለም ድንቅ ከሚባሉ ከተሞች ውስጥ ናት፡፡ ዋና ከተማዋ ሳሪያቮ እና ሪፓብሊኳ ቦዝኒያ ሄርሶጎቪና ሌላው ድንቅ የሚያሰኛቸው ልዩ ባህርያት በሀይማኖት እና የተለያዩ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ዝቦች በአንድ የሚኖሩባት መሆኑ ነበር፡፡ ይህች ድንቅ እና ፍልቅልቅ ከተማ ናት የመጀመሪያዋ የዘር ፍጅት እና ዘርን የማጥዳት ዘመቻ የተጀመረባት፡፡ በአንድ የሚኖሩት የእኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሰርቦች፣ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ኮሮሽያውያን፣ እና እስልምናን የሚከተሎ ዜጎች እኔ ልውሰድ እኔ ልውሰድ በሚል ዜጎችን ከከተማዋ ለማስለቀቅ ወደጦርነት ገቡ፡፡ በጀርመን እና የጣልያን ፋሽስት ፓርቲወች ከተነሳው የሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የቦዝኒያ ሄርሶጎቪና ጦርነት በአውሮፓ የመጀመሪያ እና እጅግ የከፋ ሆነ፡፡ ንጹሀን ዜጎች በማያውቁት እና በማይገባቸው ጦርነት ተቀቀሉ። በቦዝኒያ ተደባልቀው የሚኖሩ የተጋቡ እና የተዋለዱ ሚና ለይ በሚል ታረዱ። ትዳር ፈረሰ፣ መጠጊያ ጠፋ፣ በሰለጠነው አለም ፊት እጅግ ኋላቀር የሆነው የዘር ፍጅት ተከሰተ። አንዴ በቦዝኒያ የተነሳውን እሳት ማንም ለማብረድ የሚችል ጠፋ። ከእጅ ያመለጠ ሆነና እርስ በእርስ ተው የሚል ሽማግሌ ቀርቶ አውሮፓ ልታቆመው የተሳናት መተላለቅ ታየ። የሳሪያቮ ፍጅት እና በሪፓብሊኳ ይገባኛል በሚል በኩⶂቶች እና ሰርቦች የተጀመረው ጦርነት ቡድን እየተጨመረለት ወደሌሎች ተሸጋገረ። በይፋ ዮጎዝላቪያ ጠፋች፣ ዜጎቿ በማያውቁት እና በማይገባቸው የዘር እሳት ተለበለቡ።

አዲስ አበባ

በሰሞኑ የምናየው፣ የምንሰማው እና አቅም አልባ ዜጎች እየደረሰባቸው ያለው ግፍ እና መከራ ማንም የፈጠረው ሳይሆን አዲሶቹ የዘመነ መሳፍንት የጎጥ መሳፍንቶች ተግባር መሆኑ ሊሰመር ይገባል። እነዚህ የዘር እና ጎጥ መሳፍነቶች ህወሓት የተባለች ሀገር ጠል ድርጅት መሀከላዊውን መንግስት አቸንፋ ስልጣን ከተቆጣጠረች በኋላ ህግ ደንግጋ ይህ ለእኔ፣ ይህ ለእናንተ በሚል ድልድል ያደረገች ሲሆን ሉአላዊ የሆኑ የዘር ሪፖብሊኮች መስርታ አንዱ ከሌላው አብሮ እንዳይኖር አስተምራ የአቋቋመችው ስራት ነው፡፡ ዛሬ ተከታዮቿ ከሷ ልቀው ቢያባርሯትም ያስተማረቻቸውን እና ደንግጋ የሰጠቻቸውን ህግ በቡራኬ የተቀበሉትን አትንኩብን አልፋ እና ኦሜጋችን ነው በሚል ይህ መሬት በህገመንግስቱ የተባረከልኝ ስለሆነ ከክልሌ ውጡ የሚል ልክ በኮሮሽያውያን እና በሰርቢያውያን የተሰራውን እየደገሙት እናያለን።
እነዚህ የዘር እና የክልል መሳፍነቶች ልክ እንደፈጣሪያቸው ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ማለት ህወሓት ነው ብላ እያስተማረች እንዳለው እነሱም ይህ ሕዝብ ማለት የኔ ድርጅት ነው በሚል ሕዝብ ከሕዝብ ለማባላት ቆርጠው መነሳታቸውን ስናይ ያላወቁት እና ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር የኋላ ኋላ ድል መሆናቸውን እና ይህ ተግባራቸው ሀገር የሚያፈርስ፣ ማንም ሊገታው የማይችል ጦርነት የሚቀሰቅስ መሆኑን ነው። ልክ እንደዮጎዝላቪያውያን ሰርቦች እና ኮሮሺያኖች በቦዝኒያ የጀመሩት ውጊያ ቦዝኒያ አንዱ ያቸነፈ ይጠቀልላል ከሚል የደንቆሮ ስራ ሲሆን መላ ዮጎዝላቪያ መቃጠል ስትጀምር የጀመሩትን ማቆም ሳይችሉ እራሳቸውንም ለብልቦ፣ ሀገር አፍርሶ ታላቅ ያሏትን ከምድረገጽ አጥፍተው በህይወት ያሉት እና ከጦርነቱ የተረፉት የዘር መሳፍንቶች ቀሪ ህይወታቸውን በአለማቀፍ ወህኒቤት ፈጽመዋል።

መፍትሄ

ከምንም እና ማንም ነገር በፊት የሀገሪቱ ዋና አጥፊ የህወሓት/ኦነግ ህገመንግስት ተብየው ስለሆነ ይህን ህገመንግስት የሚያስቆም አስቸኳይ ስራ መጀመር። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስለ የሽግግር መንግስት በተጠየቁበት ግዜ ኢሕአዴግ እና እኔ እናሸጋግራችኋለን ብለው ነበር። ያዳመጣቸውም ዜጋ ቃላቸውን ስላመነ ይሁን ብሎ አልፏል። አሁን ግን የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተለወጠ የእርሳቸው ፓርቲ እና የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች ቃሎቻቸውን አጥፈው ቀዝቃዛውን የዘር ማጽዳት ቆሻሻ ስራ እያካሄዱ በመሆኑ እና ሁኔታው ከእጅ ከመውጣቱ በፊት ከዚህ በፊት በተቃዋሚወች በተለይም በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ቀርቦ የነበረው ሊያስማማ የሚችል ከሁሉም stakeholders የተውጣጣ የሚያሸጋግር የእርሳቸውን ፓርቲ ጨምሮ እንዲቋቋም ቢሆን የተሻለ አማራጭ መከተል ይቻላል፡፡ ሁሉም ያገባኛል የሚል የተካተተበት አሸጋጋሪ አካል ካለ ቀውሱን ሊገታም የተሻለ አቅጣጫ ሊያሳይም ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 አመታት የተመሰረቱ የዘር የፖለቲካ ድርጅቶች ማንንም ሳይሆን እራሳቸውን እና አባላቶችን እንጅ መላ ህብረተሰብን የማይወክሉ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ላይ ማስተማር ህዝብን ማሳወቅ እና አብሮ የኖረውን ዜጋ እኔ እወክላለሁ በሚል አንዱን ማፈናቀል ሌላውን መሬትህ ተወሰደ፣ ባእድ ሰፈረብህ ብሎ መቀስቀስ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ ይህ መጨረሻው የማያምር የእልቂት እና ሀገር የማፍረስ ተግባር መሆኑን የከተሞች፣ ቀበሌወች ሹማምንት እና የክልል አስተዳዳሪወች ሊያውቁ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን በዘራቸው እጅግ የተቀላቀሉ አባት ጠርተው አያት የማይደግሙ ግን የዘር ንጽህና እያነሱ ለማጫረስ መሞከር ከባድ ታሪካዊ ወንጀል መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል። ጠ/ሚ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ በዘር ከተዋቀረው ፓርቲያቸው ይልቅ ምሁራንን ማማከር በይበልጥም የኖሩበትን ዴሞክራቲክ ማህከላዊነት የሚሉትን መጋፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በቡራዩ፣ በለገጣፎ ያየነው በሱሉልታ እንዳይደገም ሁሉም ዜጋ ሊተባበር እና የተቻለውን ሁሉ ሊሰራ ይገባል።