March 19, 2019

ዮሀንስ መኮንን

አዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በቄሮ እና በአዲስ እበባ ወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽፎ እንዳንበብኩ ግጭት ተፈጥሮበታል የተባለበት ቦታ ድረስ በአካል በመገኘት ጉዳዩን አጣርቼአለሁ:: ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ያላቸው ሰዎችንም አካባቢው ላይ አግኝቻቸዋለሁ:: ነገሩ እንዲህ ነው።


ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ወጣቶች የጫት መሸጪያ ሱቅ ያላቸው ሲሆን በአካባቢው በብዛት ለሚኖሩ የሶማሊ ስደተኞች (ከሞቃዲሹ የመጡ) እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች ከሐረር አካባቢ የሚመጣ ጫት በመሸጥ ይተዳደራሉ::

ትናንት አቢ ጌቱ/ጉታ የተባለ የታክሲ ሾፌር (እናቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረባ ናት) የአከባቢው ነዋሪ ጋር “የሱቅ በር ዘጋህብን” በሚል ከጫት ሻጮቹ ልጆች ጋር ጭቅጭቅ ይፈጠራሉ:: ባለሱቆቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ባለታክሲውን የአዲስ አበባ ልጅ (እርሱም በብሔሩ ኦሮሞ ነው) በቡድን ሆነው ይመቱታል:: በዚህ የተበሳጩ የታክሲ ሾፍሩ ሠፈር ልጆች የጓደኛቸውን ጥቃት ለመመለስ ተሰብስብው መጥተው ግጭት ፈጥረው ነበር:: ፖሊስም ፈጥኖ ጉዳዩን ያበርደዋል::

ይህ እንግዲህ አልፎ አልፎ አዲስ አበባ ውስጥ የሚከሰት የተለመደ ተራ የሠፈር ልጆች የቡድን ግጭት ነው:: በግጭቱ ቄሮ የሚባል የወጣቶች ቡድንም ሆነ የብሔር መቧደን የሚመስል ግጭት ቦሌ ላይ አልታየም አልተከሰተምም::

ይህንን ጉዳይ ለማጣራት 30 ደቂቃ እና ቅን ልብ ብቻ ነው የሚፈልገው:: በርካታ ተከታይ ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ አፍንጫቸው ስር የተፈጸመን ግጭት አንዲት እርምጃ ተራምደው ከማጣራት ይልቅ በሬ ወለደ አይነት ዜናን ያለምንም ሃፍረት በመቅዳት (copy paste) ሲቀባበሉ ማየት ያሳዝናልም ያሳፍራልም::
የሚዲያ ዋንኛው ተግባር ነገርን ከሥሩ ፈልፍሎ አጣርቶ ማኅበረሰቡን ማሳወቅ ሊሆን ሲገባው ያልነበረ ግጭትን ማራገብ ያልነደደ እሳት ማንደድ ማንን ይጠቅማል?

ሌሎች ደግሞ ሆነ ብለው ግጭቱን የብሔር መልክ እንዳለው አስመስለው ምኞታቸውን ጽፈዋል:: የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያ ወጣቶችን እሳት ውስጥ ማግደው የፖለቲካ ግለት ለመፍጠር የታለመ ከንቱ ሙከራ ነው:: እርማችሁን አውጡ:: በአዲስ አበባ ልጆች እና በኦሮሞ ቄሮዎች መካከል እንዲነሳ የናፈቃችሁት ግጭት አልተከሰተም::

በዚህ አካሄድ በየማኅበራዊ ሚዲያው የምናያቸውን ዜናዎችን ከተአማኒ ምንጮች ሳናረጋግጥ Like, Share እና Tag ማድረግ ሀገሪቱን የብሔር ግጭት አስነስተው ለማንደድ ለተሰለፉ ዘረኞች ቤንዚን እና ክብሪት እንደማቀበል ነውና ብንጠነቀቅ እላለሁ::
Share በማድረግ የግጭት ሴራውን እናክሽፍ!”

P.S: የተወሰኑ ወጣቶች በፖሊስ እንደተደበደቡ እና የተወሰኑትም ወደ እስር ቤት እንደተወሰዱ ለማወቅ ችያለሁ!