የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኒውዮርክ ታይምስና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን እየወጣ ያለው ዘገባ የተሳሳተና የተዛባ መሆኑን ገለጸ፡፡ ዘገባው የአየር መንገዱን ያሳዘነ መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ የቦይንግ 737 ማክስ አብራሪዎች ቦይንግ ባወጣውና በኤፍ ኤ ኤ በፀደቀው በቦይንግ 737 ኤን ጅ እና በቦይንግ 737 ማክስ ያለውን ልዩነት ስልጠና በሚገባ የወሰዱ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የአየር መንገዱ መረጃ እንደሚያመላክተው ቦይንግ 737 ማክስ ወደ አየር መንገዱ ከመግባቱ አስቀድሞና በረራ ከመጀመሩ በፊት ስልጠናዎቹ ተጠናቀዋል፡፡
በቀጣይነትም በኢንዶኔዥያው ላየን ኤር የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የአሜሪካው ኤፍ ኤኤ ያወጣው ተጨማሪ መመሪያ ለሁሉም አብራሪዎች እንዲያውቁት መደረጉንና ደረጃውን የጠበቀ አስፈላጊ ገለፃ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም መሰረት የመመሪያው ይዘት ሙሉ በሙሉ በስልጠና ማንዋል፣ በኦፕሬሽን ዝርዝር መመሪያዎችና በዕለት ተዕለት ስራዎች ዝርዝር መመሪያዎች መካተቱንም አየር መንገዱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአለም አቀፍ የአደጋ ምርመራ ስነ-ስርዓትና ህጎች መከተል ስላለበት የምርመራውን ውጤት በትዕግስት እየተጠባበቀ ሲሆን÷ የሀገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የአደጋውን መንስኤ መላምት ከማስቀመጥና በተሳሳተ መረጃ ህዝብ ከማሳሳት እንዲቆጠቡም አሳስቧል ።
