(እሁድ የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. March 08, 2015፦) የቀድሞ የኢትዮጵ ብሄራዊ ባንክ ገዢ የነበሩትና፤ በኢትዮጵያ ለባንክ ስራ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት፤ አቶ ተፈራ ደግፌ፤ ባለፈው አርብ ማርች 6 ቀን፤ 2015 ዓ.ም. ቫንኩቨር በሚገኝ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው፤ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አቶ ተፈራ ደግፌ በ1918 በሸዋ ክ/ሀገር፤ በአንኮበር ወረዳ፤ ገንዳ ውሀ በተባለ አካባቢ የተወለዱ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህታቸውን በኮተቤ፤ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በካናዳ ካልጋሪ፤ በቫንኩቨርና በአሜሪካን ሚሺጋን ተምረዋል።
በ1938 ዓ.ም. በ19 አመታቸው ለትምህርት ወደካልጋሪ ካናዳ የተገጓዙት አቶ ተፈራ፤ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደአገራቸው በመመለስ፤ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ውስጥ የኢትዮጵያ የባንክ ስራ ስርአትና ከዘረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
አቶ ተፈራ ደግፌ፤ በኢትዮጵያ ስቴት ባንክ፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ባንክ፤ በሲቪል አቪየሽን፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ በአብዮቱ ማግስት በቀድሞው መንግስት ለሰባት አመት ታሰርው ነበር። በአብዮቱ ወቅት በተደጋጋሚ ለአለምአቀፍ ስብስባ ወደውጭ ወጥተው እዚያው የመቅረት እድል ቢኖራቸውም፤ ወደአገራቸው የተመለሱት አቶ ተፈራ ደግፌ፤ አብዮቱ በባተ በሁለተኛው አመት የለምንም ማብራሪያ ለሰባት አመታት ታስረው ነበር። ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተሰጣቸው ምክንያት ለአብዮቱ እንቅፋት እንዳትሆን የሚል እንደሆነ ተገልጾዋል።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ፤ አቶ ተፈራ ደግፌ በቫንኩቨር በሚገኘው የብሪቲሽ ኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ ህግ ፋክልቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ ረጅም ግዜያቸውን የኖሩት በቫንኩቨር ካናዳ ነበር።
አቶ ተፈራ ካናዳዊቷ ባለቤታቸው ከጥቂት አመታት በፊት በሞት የተለይዋቸው ሲሆን፤ ከትዳራቸው ያፈሩዋቸው አንድ ወንድና ሴት ልጆቻቸው በካናዳ ይኖራሉ።
የአቶ ተፈራ ደግፌ የቀብር ስነስርአት በመጪው ማክሰኞ፤ ማርች 10 ቀን በቫንኩቨር ይፈጸማል። አቶ ተፈራ ደግፌ በእስር ጊዜያቸው አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ ከታላላቅ ሰዎች ጋር የታሰሩ ቢሆንም፤ በስደት የሚገኙ ጳጳሳት በቀብራቸው እንዲገኙ የተደረገው ሙከራ እስካሁን አልተሳካም።
አቶ ተፈራ ደግፌ ባለፈው አመት በቶሮንቶ የሚገኘው ቢቂላ የሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው የመጀመሪያ ሽልማት ላይ በህይወት ዘመን አስተዋጽኦ የተሸለሙ ሲሆን፤ በሽልማታቸው ወቀት ያደረጉት ንግግር በዚህ ቪዲዮ ላይ ከ35ኛው ደቂቃ ጀምሮ ይገኛል።
አቶ ተፈራ ደግፌ A Tripping Stone, and Minutes of an Ethiopian Century የተሰኙ ሁለት መጻህፍት ጽፈዋል።