ወቅታዊው ትኩሳት እንደ ግርሻ የሆነው የብሔሮች ግጭት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አማራው በኦሮሞው ወገኑ ልጆች አማራ ሆኖ በመወለዱ ብቻ እየተጠቃ ወይም የዘር ጥላቻ ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ ጥቃቱም እስከ ግድያ ድረስ በዘለቀ ርምጃ ጭምር እየተገለጸ ነው፡ ፡ በአንዳንድ ሥፍራዎችም ዜጎች የትግራይ ክልል ተወላጅ ወይም በብሔራቸው ትግሬ በመሆናቸው ብቻ የመሰል ጥቃት ሰለባ የመሆናቸው አዝማሚያ መታየቱ ቢያንስ እየተሰማ ነው፡፡ ‹‹ከክልሌ ውጣልኝ! ወደ መኖሪያ መንደርህና ወደ ትውልድ ቀዬህ ተመለስ! በእኛ ክልል ያፈራኸው ሀብትና ንብረት የአንተ አይደለምና እርቃንህን ቅር! ነፍስህን በጨርቅ ቋጥረህ የመውጣት መብት ብቻ ነው ያለህ…›› የሚለው ግፊትና ትንኮሳ እያሰለሰም ቢሆን ወዲያና ወዲህ እየተፈፀመ ለመሆኑ ሰሚ ያጡት የሰለባዎቹ ድምፆች በራሳቸው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽሞ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን መሰማቱ በራሱ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው እንላለን፡፡ ከፍ ሲል የገለጽነው ችግር እስከዛሬ ድረስ ወጥ የሆነና ተመልሶም እንዳያገረሽ የሚደረግበት ርምጃ ያለመወሰዱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከድርጊቶቹ መደጋገምም ይሁን አሁን አሁን እየተባባሱ የመጡበትን ሁኔታዎች ከማስተዋላችን አኳያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሰን ማንሳት ተገቢ መስሎ ታይቶናል፡ ፡ እውን በአንዳንድ አክራሪ ብሔረተኛ በሆኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ‹‹ መናጢ ደሀና አሮጌ ውራጅ ለባሽ እንኳን ቢሆን መንፈሰ ኩሩና ሌላውን በንቀት የሚመለከት ዘር ነው…›› ተብሎ የተፈረጀው አማራ፤ የኦሮሞው ወገኑ ጠላት ነው? በሌሎች ወገኖቹስ ላይ ‹‹ ጭቁን፣ቢሮክራት፣ነፍጠኛ…›› ተብሎ የሚፈረጀው አማራ፤ ከማንም እና ከምንም የበለጠ ባለጋራ ነው? ለመሆኑ አማራ የሚባለው ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው የኢትዮጵያ ሰው፤ አማርኛ ቋንቋን ከመናገር ውጪ ሌላ የመግባቢያ ቋንቋ ባለቤት ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ጭምር፤ እንደ ‹‹ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች መብት›› ሁነኛ ተጻጻሪ ሆኖ በአንዳንድ ጽንፈኛ ብሔረተኞች የሚፈረጀውና በዚህም አጓጉል ፍረጃ ምክንያትነት ዘወትር በጥርጣሬ የሚታየው ለምንድን ነው? መጽሔታችን ይህን የመሰለውን ጥያቄ መልሳ የምታነሳው፤ የጥላቻው ፖለቲካ የሁላችን ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያ ፍፁም ወደማንጠብቀውና በቀላሉም ወደማንቆጣጠረው ወይም መፍትኄ ወደማናገኝለት ቀውስ የሚመራን መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ብቻ ነው፡፡ ምናልባትም እንዲህ ብሎ ማለት ‹‹እሳት ማቀጣጠልና ነገር ማራገብ ላይ ያተኮረ የግሉ ፕሬስ ተግባር ነው…›› ተብሎ የሚያስተቸን እስካልሆነ ድረስ፡፡ ለሁሉም ከወዲሁ በብሔራዊ ዕርቅም ይሁን በሌሎች የቅድመ ችግር ማስወገጃ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስልቶች፤ የገዥው ፓርቲ ተሳትፎ ባለበት ሁኔታ ነገ ወይም ዛሬ ሳይባል መድኃኒት የሚያስፈልገው ወቅታዊ ትኩሳት ነው አንደኛው ኢትዮጵያዊ ሰው ሌላውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቋንቋውና በዘሩ… ምክንያት ለማጥቃት የሚነሳሳበትና የሚያደባበት አዝማሚያ ነው ብለናል፡፡ ስለሆነም በአገራችን ጥልቅና የማያዳግም መፍትኄ ከሚያስፈልገው ወቅታዊ ትኩሳት አኳያ በተሰማበት አካባቢ ተግባራዊውም ሆነ አልሆነ፤ በቅርቡ ከወደ ሱዳን ካርቱም የተሰማው ደስ የሚያሰኝ ዜና ነው እንላለን፡፡ የተሰማው ዜና ዋንኛ ትኩረት ብሔራዊ ዕርቅን የሚጠይቅ መልዕክት ያቋተ እንደመሆኑ ‹‹በእኛም ሀገርና መንግሥት በሆነ›› ያስብላል፡፡ በድጋሚ አደረጉትም አላደረጉት፤ ዘግይተውም ቢሆን ፕሬዚዳንት ጄነራል አልበሽር ያሰሙት የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ፤ ለኢትዮጵያ በጎውን ነገር ለሚመኙ የሰው ዘሮች በሙሉ የመንፈሳዊ ቅናትን ክብሪት በአዕምሮ ውስጥ የሚያጭር ነው፡፡ መቼም ይሁን መቼ እስካልደረሱብን ድረስ፣ ካልተነኮሱን፣ ካልነካኩን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቤት እስከ አደባባይ የሚስተዋለውን የነገር ፍም፣ ቤኒዚንና ነፋስ እየሰጡት ዝንተ-ዓለም የሚቀጣጠል እሳት እንዲሆን የሤረኛነት ሥራ እስካልሠሩብን ድረስ፤ የጎረቤት ሀገሮቻችንን፣ የሕዝባቸውና የመንግሥታቸው ሁለንተናዊ ሰላም፤ የእኛም ሰላም ነው፡፡ መግባባታቸውና ፍቅራቸውም በእነሱው ሊወሰን የሚችል አይደለም፡፡ ቢያንስ የዕርቀ-ሰላማቸው ካፊያ እኛንም ያረሰርሰናል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህም አሁን ካለንበት አሳሳቢ ሁኔታ አንፃር ከወደ ካርቱም የተሰማው ዜና አዲስ አበባም ላይ በእኛ ባለሥልጣኖች ቢደገም መልካምነቱ ለገዥዎችም ይሁን ለተገዥዎችም ነው፡፡ የሱዳን መንግሥትና የመንግሥቷም ወሳኝ ሰው የሆኑት የአልበሽር የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪና የፖለቲካ እሥረኞችን ሁሉ ለመፍታት የመወሰን እርምጃ፤ የካርቱም ዕልቂትና ውድመት ጠሪ ፖለቲካዊ ግለት ማብረጃ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው አፍሪካ ቀንድ በይበልጥም የኢትዮጵያ፣ የሶማሌያ፣ ችግሯን ለማመቅ የምትንደፋደፈው የኡጋንዳ፣ ከእናት ሀገሯ በ ‹‹ናጽነት›› ስም ተለይታ በፖለቲካዊ የነገር ማብለያ ምድጃ ላይ በመጣድ ለምትንጨረጨረው ኤርትራ ወቅታዊ ትኩሳት ማቅለያ የሚሆነውን መድኃኒት አመላካች ጭምር ነው የሚል ዕምነት አለን፡፡ በመሆኑም ይኼን ከወደ ካርቱም የተሰማን እና ሱዳንን የመሰለ ሀገር በሀገርነቷና በመንግሥትነቷ ሊያስቀጥል የሚያስችል፣ የሚጣሉት ዝሆኖች መፈንጫና የደም ጥማት ማርኪያ ሆኖ ለሚቀርበው ወንድም የሱዳን ሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላምን ብቻ ሳይሆን ከዘለቄታዊ ሰላሙ ሊያገኝ የሚችለውን የዕድገትና የብልፅግና …ፍሬ ተቋዳሽ ሊያደርገው የሚያስችለውን የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪንና የፖለቲካ እሥርኞችን በሙሉ ከእስራት ነፃ የማድረግን ያህል ዜና መስማት፤ ሌላው ቢቀር ‹‹እንደዚህ ዓይነቱን ይበል የሚያሰኝ ነገር ለእኛም ባደረገው…›› የሚል ቀና ስሜት፤ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጦርነት፣ ከጥፋት፣ ከውድመትና እርስ በእርስ በነገር ከመቋሰል አዙሪት እንድትወጣ ሌት ተቀን ከልባቸው አጥብቀው በሚመኙ ዜጎች ዘንድ እንዲጎለብት የሚያደርግ፤ ወቅታዊ ጉዳይ፣ ወቅታዊ ትኩሳትም ብለን ማመናችን በራሱ ችግር ያለው ሆኖ አይሰማንም፡፡ ዓመታት ያልፈቱት ችግር ያለፉትን ዓመታት ፖለቲካዊ ስንክሳሮች ስንመረምራቸውም ሆነ የአሁኑን ሁኔታ እያስተዋልን ስለመፃኢው ጊዜ ስናሰላስል፤ ኢትዮጵያ ባለቤት ያጣች ሀገር ሆና የምትታየን መሆኑን አንክድም፡፡ ‹‹አገሪቱ የማን ነች?›› ተብሎ ሲጠየቅ በቃል ደረጃ በቅፅበት የሚከሰተው መልስ ‹‹የዜጎቿ ሁሉ›› የሚለው ነው፡፡ ከመኖር ከተገኘው እውነትም ይሁን በየዋህነትም ይባል በተላላነት… ፀንቶ ከኖረው ዕምነት አኳያ ‹‹ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ሁሉ›› የመሆኗ ሐቅ፤ አሁንም በቃል ደረጃ የሚያሻማ አይደለም፡፡ ከቅድመ 1983 ዓ.ም በፊት በነበረው ሁኔታ፤ ሀገሪቱ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁሉ (የኦሮሞው፣ የአማራው፣ የትግሬው፣ የአፋሩ፣ የሱማሌው፣ የወላይታው፣ የጋምቤላው፣ የሸኰው፣ የመዠንገሩ፣ የኮንሶው፣ የከንባታው፣ የአደሬው፣ የአገው፣ የሺናሻው…) ‹‹ነች›› መባሉ፤ በማለት ደረጃ የሚያስማማ ነበር፡፡ በኑሮ ደረጃ፣ በኢትዮጵያ ሀብትና ፀጋ የበለጠ ተጠቃሚ፣ የበለጠ ተገልጋይ የበለጠ ወሳኝ፣ ሰጪና ነሺ፣ አድራጊና ፈጣሪ… በመሆን ደረጃ ግን በተግባር የሚታይ ዜግነታዊ ልዩነት ነበረ፡ ፡ ይህ ‹‹ነበረ›› የምንለው ልዩነት ከዚያም በቀደመው ጊዜ የነበረ እንደመሆኑ መጠን፤ ዛሬ ደግሞ ቅርፁንም ይሁን መልኩን ለውጦ በችግርነቱ ቀጥሏል፡፡ ይልቁንም ‹‹ኢትዮጵያዊነትን›› በራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከማስገባት ተንደርድሮ፤ ጎሣን ወይም ነገድን፣ ብሔርን ወይም ብሔረሰብን በራሱ እንደዜግነት ወደ መቁጠሩ ወይም ወደ መውሰዱ የአክራሪነትም እንበለው የዘረኛ ጽዮናዊነት ጽንፍ እያመራ ይገኛል፡፡ ይህ እያመራ ያለው ሀገራዊ እውነት፣ ማንም ወደደው ወይም ጠላው በዛሬይቱ ‹‹ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ›› ከዳር ምድር እስከ መሀል መዲና በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ የመታየቱም ምክንያት በኢትዮጵያ ለዓመታት ያልተፈቱት ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ሕጋዊና አስተሳሰባዊ ችግር ሰፍኖ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ዛሬም ችግሩ ‹‹እየተቀረፈ ነው…›› ቢባልም እንኳ በይበልጥ መወሳሰቡንና ከናካቴውም ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በእንደዚህ መሰሉ መለኪያ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ፤ ዓመታት ያልፈቱት፣ ይልቁንም ከመጥበሻው ወደ እሳቱ እያመራ የሚገኝ ችግር መሆኑ፤ ከመፃኢው የከፋና አይቀሬ የሚሆን አደጋ እናመልጥ ዘንድ ብሔራዊ ዕርቅን እንመኝ ዘንድ የማያስገድደን ነው ሊያሰኝ አይችልም፡፡ እንደሚስተዋለው በኢትዮጵያችን እጅግ በጣም ብዙ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ‹‹ነበረ›› የሚባለውን ‹‹ብሔራዊ ጭቆና›› ለማስወገድ ‹‹ያስችላሉ›› በሚል ተነስተዋል፡፡ መነሳት ብቻ አይደለም ‹‹በሕገ-መንግሥቱ እና በሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱ›› ቡራኬ፤ ለተነሱትና ‹‹መልካም አማራጭ ናቸው›› ለተባሉት ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ለተባሉ ጥያቄዎች ‹‹ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ›› የተባለ መልስ ተሰጥቷል፡፡ መልሱን እንዲያስፈፅሙ ወይም ተግባራዊ እንዲያደርጉም፤ የነገው ሁነት በትላንቱ እና በመፃኢው ጥሩ መነፅር ለሚመለከቱ ሩቅ አሳቢዎች… ሳይሆን በሌላው ውድቀትና መዋረድ የራሳቸውን ማንሰራራትና ክብር ብቻ ለሚመዝኑ፣ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል›› ለሚሉ፤ ምርኮኛና በልቶ አደር ፖለቲከኞች ሥልጣንና ኃላፊነቱ ተሰጥቷል፡፡ እንደዚህም ስለተሰጠና የአፈፃፀሙንም ሁኔታ ለማረምና ለማስተካከል ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› ወይም ‹‹ቁጭ ብለው የሰቀሉትን….›› እየሆነ አስቸግሯል፡፡ ስለአስቸገረም ‹‹ዴሞክራሲያዊና ሕገ- መንግሥታዊ መብታችንን እንዳሻን የመተርጎም ነፃነት ተጎናፅፈናል…›› በሚሉ ተላሎችና አውቆ አጥፊዎች ርምጃ፣ ጥቂት የማይባሉ የሀገሪቱ ዜጎች ‹‹የእኛም ናት…›› በሚሏት ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የዚህ ወይም የዚያኛው ክልል ተወላጅ ናችሁ አይደላችሁም…›› በሚል ምክንያት፤ የገዛ አገራቸው ተፈናቃይ፣ ስደተኛና ‹‹አቤት…›› ቢሉም መልስ የማያገኙ ዜጎች ሆነዋል፡
…እኛ በአብዛኛው (ሰዋዊ ባሕሪ ነው ቢባልም) ትላንት አውቆም ይሁን ሳያውቅ… የጎዳንን፣ ‹‹በእንጀራችን ላይ ቆሞ ነበር…›› የምንለውን፣ የመሰከረብንን፣ የተኮሰብንን፣ ያስተኮሰብንን፣ አንድ ጥቅም ያሳጣንን ወይም ያጓደለብንን ብቻም ሳይሆን ‹‹እንደዚያ ለማድረግ አስቦ ነበር ወይም ከማድረግ የማይመለስ ሰው ነበር›› በማለት የምንገምተውን ወይም የምንጠረጥረውን ዜጋ፤ ገብቶትም ይሁን ሳይገባው…
፡ የእንደዚህ ዓይነቱም ሁነት ግፊት የሀገሪቱ ‹‹ዳር አገር…›› ናቸው ከሚባሉት አካባቢዎች እየተነሳ አድማሱን በማስፋፋት ለአዲስ አበባ ከተማ እጅግ ቅርብ በሆኑትና እንደ አምቦ ባሉት የኢትዮጵያዊነት ማዕከሎች ሳይቀር በተግባር መታየት ጀምሯል፡፡ ይህ አሳሳቢና ፍፁም አስጊ ሊሆን የሚችል ‹‹የዴሞክራሲያዊ መብት›› አተገባበር በአምቦ ሲፈፀም ከታየ፣ እነ አቶ ፀጋይ ዳምጤን ከዳኖ ወረዳ … ካፈናቀለ፣ ለመደብደብ፣ ለእንግልት ካደረገ፤ ከዚህም አልፎ ተርፎ ለአንድ ሰውም ቢሆን በዘር የተነሳ ለሕይወት መጥፋት ሰበብ ከሆነ፤ በአምቦ የተፈፀመው ነውረኛ ድርጊት ነገ ወይም ዛሬ ‹‹ፊንፊኔ የኦሮሞ ነው!…›› በሚል ሰበብ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ ላለመሆኑ ምን ዓይነት መተማመኛ ማግኘት ይቻላል? የስጋቱ ጉዳይ ከሆነ ምልክቱ እየታየ ነው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች፤ ነገር ግን ሊናቁ የማይገባቸው የኦሮሞ ልጆች ከወደ ዳር ሀገር ተቀምጠውም ይሁን በቅርብ ሆነው በውክልና የሚያስተዳድሩትንና የሚያዙበትን ቤትና ንብረት ‹‹ለምን ለአማራ አከራያችሁት? ለምንስ ነፍጠኛ እንዲገለገልበት ታደርጋላችሁ?…›› በማለት፤ ውክልናውን በሰጧቸው ወዳጆቻቸው ወይም የቤተሰቦቻቸው አባላት ላይ ተግሣጽና ቁጣ አዘል ማስጠንቀቂያ ሲሰጡም ‹‹ሆደ ሰፊው›› የአገራችን ዜጋ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ እያለፋቸው ነው፡፡ ታዲያ ይኼን የመሰለው ቀላል የሚመስል ግን ቀላል ያልሆነ፣ ብልጭ ድርግም ሲል… የሚስተዋል፤ ነገር ግን ውስጥ ውስጡን የሚፍምና የሚግም ከዘረኛው ፖለቲካ ማህፀን የሚቀፈቀፍና ዓመታት ያልፈቱት ችግር፤ በብሔራዊ ዕርቅ መውረድ አማካይነት ማርከሻ የማያስፈልገው ነው አይባልም፡፡ በበቀል መንገድ ላይ ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሰው መንገድ ጤነኛ አልነበረም፡፡ ‹‹ኧረ ጤነኛም ነበር…›› ከተባለ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው ‹‹የጦርነት ታሪክ ነው›› ባልተባለ ነበር፡፡ እዚህ ያደረሰን መንገድ ጤነኛ ባለመሆኑ የተነሳ፤ የመንግሥትነትና የአገር ገዥነት ሥልጣኑ በጉልበት እየተያዘ፣ በጦርነት የሚቀማና በነፍጥና በነፍጠኞች ብዛትና ኃይል እየተጠበቀ ለዝንተ ዓለም ፀንቶ የሚቆይ እየመሰለ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ የሦስት ሺህም፣ የመቶ ዓመትም ይሁን የሉሲን … ያህል የመንግሥትነትና የሀገርነት ታሪክ ይኑራት፤ የተጓዝንባቸው መንገዶች በአያሌው ወደ ጦርነትና ወደ ውድመት የመሯት የበቀል መንገዶች ናቸው፡፡ እንዲህ ብሎ ማለት፤ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ በአንደኛውም ወቅት ቢሆን ከበቀልና ከቂመኝነት አዚም የፀዳ የዕርቅና ከልብ ለመግባባት የመፈለግ፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት የመተያየት፣ ተከባብሮና ተፋቅሮ የመኖር ስሜት የተንፀባረቀበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ አልተፈጠረም ማለት አይደለም፡፡ የቅርብ ጊዜው የሀገርነትና የመንግሥትነት፣ የገባሪና የአስገባሪነት፣ የገዥና የተገዥነት ዶሴያችን እንደሚመሰክረው እውነት ከሆነ ግን፤ ዛሬ ላይ ያደረሰን የበቀል መንገድ ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ፣ ከማኅበረሰብ እስከ ላይኛው መንግሥታዊ ቅርፅ ድርስ፤ አመለካከቱ ‹‹ልኩን አሳየዋለሁ!…›› በሚለው ጉልበትንና ኃይልን በተከታዩ ላይ ከማሳየት ፍላጎት ወይም ከበቀል ዕንቁላል ከሚፈለፈልና አስተማሪ መሆን ከማይችል መርህ የሚመነጭ ነው፡፡ እኛ በአብዛኛው (ሰዋዊ ባሕሪ ነው ቢባልም) ትላንት አውቆም ይሁን ሳያውቅ… የጎዳንን፣ ‹‹በእንጀራችን ላይ ቆሞ ነበር…›› የምንለውን፣ የመሰከረብንን፣ የተኮሰብንን፣ ያስተኮሰብንን፣ አንድ ጥቅም ያሳጣንን ወይም ያጓደለብንን ብቻም ሳይሆን ‹‹እንደዚያ ለማድረግ አስቦ ነበር ወይም ከማድረግ የማይመለስ ሰው ነበር›› በማለት የምንገምተውን ወይም የምንጠረጥረውን ዜጋ፤ ገብቶትም ይሁን ሳይገባው… ያላጨበጨበልንን፣ ያልፈከረልንን፣ ያልሳቀልንን …ወገን፤ በጨዋነትና በትህትና፣ በአስተዋይነትና በብልሃት፣ በመተውና በመርሳት፣ ከዛሬው በጣም ጥሩ አጋጣሚ ለነገ እጅግ በጣም ብዙ ትርፍ ሊያስገኝ በሚችል ጥበብ ለማስተማር የምንፈልግ ወይም ተነሳሽነቱ ያለን አይደለንም፡፡ ዛሬ ደግሞ ልክ እንደትላንቱ ያለፈው እየተናፈቀ የአሁኑ የሚረገምበት ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ባለወር ተራው ያለፈውን ሥርዓትና የሥርዓቱን አራማጆች ብቻ ሳይሆን ‹‹ተቀናቃኝ ናቸው›› የሚላቸውን ሁሉ፤ ከማውገዝ፣ ከማጥላላት፣ ከመወንጀልና ወህኒ ከማውረድ አልፎ ራሱንና ራሱን ብቻ የተቀደሰና ፍፁም የተሻለ አድርጎ በመስበኩ ተግባር ተጠምዶ የሚታይበትም ነው፡ ፡ ዛሬ ‹‹ተቃዋሚ›› ወይም ‹‹የሥርዓት ለውጥ ናፋቂ›› የሚባለው የፖለቲካ ድርጅትም ቢሆን በውስጡ እርስ በእርስ፣ በውጪ አንደኛው ከሌላው፣ በጋራ ደግሞ ሁሉም ከገዥው ፓርቲና መንግሥት ጋር የሚናከስና ‹‹ጠብና ልዩነት›› አለኝ ባይ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ዛሬ መነሻው የበቀልተኝነት ዘር የሆነው ቂመኝነትና ከፍፁም በራስ ያለመተማመን ስሜት የሚመነጨው ተጠራጣሪነት ብሎም ራስን ከሌላው አልቆ በማክበር የመኮፈስ አዝማሚያ ሲሆን፤ መዳረሻው ደግሞ ጦርነት፣ ውድቀትና ትንሳዔ አልባው ሁለተናዊ ሞት ነው፡፡ ይሄን በመሰለው የበቀል መንገድ ላይም፤ ደርጎች ብቻ ሳይሆኑ ኢሕአፓዎች፣ መኢሶኖች፣ አንድነቶች፣ መኢአዶች፣ ሕብረቶች፣ ቅንጅቶች፣ ኦነጎች፣ ኢሕአዴጎች ….ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡ ፡ ዛሬም ከራሳቸውም ጋር ይሁን ከሌላው ወይም ከባላንጣዎቻቸው ጋር አልታረቁም፡፡ አንዳንዶቹ ታሪክ ራሱና ትውልድ ድብን አድርጎ እስኪታዘባቸው ድረስ፤ የጋራ በሚሆን ባላንጣቸው ተደምስሰው ባለፉበት ሁኔታ እንኳን፤ መካሰስና መወነጃጀላቸውን አላቆሙም፡፡ እስከደም መቃባት ደረጃ ካደረሳችው ፖለቲካዊ ሥልጣን ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀውና ‹‹እንሞትልሻለን…›› ያሏትን ሀገር በፉክክር አፍርሰው ካበቁም በኋላ፤ ህሊናቸው ልጣቸው መራሱን፣ ጉድጓዳቸው መማሱን እየነገራቸውም ቢሆን የመረጡት በበቀል መንገድ ላይ መረማመዱን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አድባርና አውጋር ግን፤ ወደ ደም መፋሰሱና ወደ ርስ በርስ ዕልቂቱ… የሚያሳልፈው ከተንበሪ ( መዝጊያ ) ተዘግቶ የሚያይበትን ቀን በመናፈቅ፤ ካርቱም ላይ የተሰማው የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ፤ ከኢሕአዴጋዊው ቤተ-መንግሥትም እንዲመነጭ የሚማፀን ይመስላል፡፡ ምን ይሻለናል? የሚሻለን ዛሬም ብሔራዊ ዕርቅ ነው፡፡ የሚሻለን ቂም የሚያርቅ፣ ደም የሚያደርቅ ብሔራዊ ዕርቅ በኢትዮጵያ እንዲወርድ መመኘት ብቻ አይደለም፡ ፡ ለተግባራዊነቱም ከልብ መትጋት ነው፡፡ ለዓመታት የዘለቁትንና ከድጡ ወደ ማጡ እያመሩ ያሉትን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግር ለማስወገድ፤ የሚኖረው የተሻለና አማራጭ የማይኖረው ምርጫ ብሔራዊ ዕርቅ ለማውረድ ዝግጁ መሆን ነው፡፡ ዝግጁነቱም ያልተንዛዛ ሰበብንና ጊዜ ቀጠሮን ይሻል፡፡ በዚህ ገረድ የሚኖረውን የበለጠ ድርሻ ማንሳት የሚኖርበት ደግሞ፤ እንደ አልበሽር መንግሥት ሁሉ፤ በሕወሓት ኢሕአዴግ የሚዘወረው የአቶ ኃይለማርያም አስተዳደር ነው፡፡ አስተዳደሩ በክፉ ከሚነሳበት ‹‹የአገዛዝ ባሕሪው›› እና ዕርቅን ከሚጠየፈው መጥፎ አዚሙ ተላቆ በተጨባጭ የሀገርና የመንግሥት አስተዳዳሪ መሆኑን ለማሳየት፣ ለራሱም ይሁን ለኢትዮጵያ የሚበጀውን መስመር በቁርጠኝነት ለመከተል …በሆደ ሰፊነት የብሔራዊ ዕርቁን አይቀሬነት የሚያበስረውን የጥሪ ደወል ለመደወል፤ ነገ ሳይሆን ዛሬ ከነበረ ማንነቱ ጋር ተወያይቶ ከአንድ ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት፡፡ የነፍጥ አምልኮ ሲያበቃ፣ የትምክህተኝነት ፖለቲካዊ ውርስ ሲያከትም፤ በይበልጥ የሚጠቀመውና ከበቀል መንገድ ጉዞው ኪሣራ ነፃ የሚሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን በመገንዝብ፤ የሕወሓት ኢሕአዴግ መንግሥት የፖለቲካ እሥርኞቹን ‹‹አሟጦ›› በመፍታትና የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ በማስተላለፍ አዲስና በኢትዮጵያ የትንሳዔ ዘመን የታሪክ መዝገብ ላይ ስሙን በደማቅ ቀለም የሚያፅፍ አስመስጋኝ ተግባር ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ ለኢትዮጵያው መንግሥት የሚሻለው ከፍ ሲል የተገለጸው ነው፡፡ እርስ በርሳቸው ለሚወነጃጀሉት፣ የሀገሪቱን እና የሕዝቧን የጣዕር ዘመን በመነካከሳቸው ብዛት ለሚያረዝሙት ስመ ተቃዋሚዎችም ቢሆን ለብሔራዊ ዕርቅም ይሁን ከየራሳቸው ጋር ለመታረቅ፤ ከዛሬ የተሻለ ቀን፣ ከዛሬ የተሻለ ሰዓት፣ ከዛሬ የተሻለ ዕድል የላቸውም፡፡ ለግራ ቀኙ ወገን የተሻለው ነገር ይኸውና ይኸው ብቻ ሲሆን ከዚህ ውጪ ያለው፣ ሊኖር የሚችለውና የሚታየው መንገድ ሁሉ ግን፤ እስከዛሬ ኢትዮጵያ ‹‹ይበጀኝ ይሆናል…›› እያለች ወይም ‹‹ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ያበቃታል…›› እየተባለላት ወደ አዘቅት የምትወርድበት የቁልቁለት መንገድ ነው፡፡ ልማትም ቢሆን ብዙኃኑ አብሮ በኑሮው መሻሻል፣ በተስፋው መለምለም፣ በአብሮነቱ ፍቅር ያለ አንዳች ስጋት ከነአዕምሮው መልማት ሲችል እንጂ በፎቅ ክምርና በጥቂቶች ማበጥ የሚመዘን ወይም የሚለካ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚሻለው አብሮ በጋራ በሁለንተናዊ መስክ መልማት ነው፡፡ ወደዚህ የሚያደርሰውም ለዓመታት ያልተፈቱትን ችግሮች የሚቀርፈው፣ በበቀል መንገድ ላይ ከምናደርገው አጥፊ ጉዞ ሊያቅበን የሚችለው፣ ኢትዮጵያን በሀገርነቷ የማስቀጠል ዋስትና የሚሆነው፣ አመንም አላመንም በሀገሪቱ አየር ላይ የሚያንዣብበውን የሕዝባዊ አመፅ ደመና በመግፈፍ ዳግመኛ ሠይፍ ከምንማዘዝበት ሜዳ እንዳንወርድ የሚገላግለን፤ ዛሬም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዕርቅ የመውረዱን አስፈላጊነት አምነን በመቀበል ተግባራዊ ስናደርገው ነው፡፡ እጅግ ለሚያስፈልገውና ለብሔራዊ ዕርቁ መውረድ መደላድል የሚሆነውም፤ የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት ነው፡፡ አዳዲስ የፖለቲካ እሥርኞችን ወደ ወህኒ ከማጋዝ መቆጠብ ነው፡፡ ሥልጣንን ለማጋራት፣ አገሪቱን የጋራ ቤት ለማድረግ መወሰን ነው፡፡ በጥሪ ደረጃ የተሰማውን ነገር ግን ከልብ እንዲሆን የሚፈለገውን የአልበሽርን አማራጭ መከተል ነው፡፡ የካርቱምን ጥሪ ‹‹ለእኔም…›› ብሎ መስማት ነው፡፡ አማራጩን ለመከተልና አስደሳቹን ጥሪ ለመስማትም፤ የግድ ኢትዮጵያ ሱዳን የገባችበት የፖለቲካ ማጥ ውስጥ በመግባት ሂሣቧን ካወራረደች በኋላ መሆን የለበትም፡፡ የደቡብ ሱዳን መገንጠልና ገና በጫጉላነት ዘመኗ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ያለፈችበት፣ የረሃብ፣የችጋር፣ የማይነጥፍ የሚመስለው የጠብ ቆስቋሽነት ሁኔታና እንደ ኤርትራ ዓይነቱ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥም ተደግሞ መታየት ይኖርበታል አይባልም፡፡ ይህም ክፉ ነገር በሃገራችን ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያችን ‹‹የዕብድ ገላጋይ›› ያስፈልጋታል ተብሎ አይተሰብም፡፡ አሁን ላይ ሆኖ የዳርፉርና የአቢዬ ግዛት ውጥረትና ጡዘት ብቻውን አልበሽርን ለብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ …ገፋፍቷል ብሎ ማሰብም ትንሽ የማይባል የአመለካከት ጉድለት አለው፡፡ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች በጎረቤት ሀገራት ተፈጠረ የሚባለውን ቀውስ ለማስወገድ በሽምግልና ስም መሯሯጥ ብቻ አይደለም የሚጠበቅባቸው፡፡ በቤታቸውም ለነፋስ የተጋለጠ የነገር ፍም መኖሩን ተገንዝበው ሰደዱ ከመቀስቀሱ በፊት የአደጋው ተከላካይ ዳኛ ሆነው የመቆም ህሊናዊም፣ታሪካዊም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአንቀፅ 39 ላይ የተዋደደው የመጠበቂያ ቀለበት ከተነቀለ የሚያስከትለው መዘዝ ‹‹ጦርነትን እንሠራዋለን…›› ለሚሉት ሰዎች የሚጠፋቸው አይመስለንምና ነው ዛሬም የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ እናሰማለን የምንለው ፡፡

 

Leave a Reply