የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ11.8 በመቶ ማሻቀቡን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የዋጋ መጨመር አዝማሚያ መታየቱን ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡

የአሁኑ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ውጤት፣ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ መሆኑን ኤጀንሲው ያስረዳል፡፡

የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ለማጥናት በአጠቃላይ 119 የገበያ ቦታዎች በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መዳሰሳቸውን፣ የኤጀንሲው የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ያስረዳል፡፡

በዚህም መሠረት የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የአገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ፣ ከጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ኢንዴክስ ጋር ሲነፃፀር በ11.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ለዚህ ጭማሪ ምክንያት የሆኑት ምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች በ16.2 በመቶ ዕድገት በማስመዝገባቸውና መጠጥ፣ ሲጋራና ትምባሆ በ11.3 በመቶ፣ ልብስና መጫሚያ በ7.1 በመቶ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ውኃና ኢነርጂ ደግሞ 6.3 በመቶ በማስመዝገባቸው ነው፡፡

የቤት ዕቃዎች፣ የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት ቁሳቁሶችና የቤት ሠራተኛ ደመወዝ በ5.7 በመቶ፣ ሕክምና 7.8 በመቶ፣ መገናኛ 2.2 በመቶ፣ መዝናኛ 8.6 በመቶ፣ ትምህርት 14.7 በመቶ፣ ሬስቶራንትና ሆቴሎች 10.8 በመቶና ሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች በ5.3 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በሌላ በኩል የትራንስፖርት የዋጋ ኢንዴክስ የ2.1 በመቶ ቅናሽ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. መታየቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡  በተለይ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ተፅዕኖ የሆነው የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት በአብዛኞቹ የምግብ ክፍሎች ላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ዳቦና እህል በ3.2 በመቶ፣ ሥጋ 14.1 በመቶ፣ ወተት፣ ዓይብና እንቁላል በ16.5 በመቶ፣ ዘይትና ቅባቶች በ16.6 በመቶ፣ ፍራፍሬ በ22.6 በመቶ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ፣ ድንችና ሌሎች ሥራ ሥሮች በ21.8 በመቶ፣ ስኳር፣ ማርና ቸኮሌት በ3.7 በመቶና ሌሎች ምግቦች በ74.5 በመቶ ዕድገት አሳይተዋል፡፡

ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ጭማሪ የታየባቸው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ገበያዎች ናቸው፡፡ አጠቃላይ አገራዊ የምግብ ዋጋ በ16.2 በመቶ ለማሻቀቡ ምክንያት  አዲስ አበባ በ30.3 በመቶ፣ ኦሮሚያ 23.7 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ 22.0 በመቶ፣ አፋር 21.5 በመቶ፣ አማራ 11.1 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት መጠነኛ የዋጋ ግሽበት በመኸር ወቅት የተለመደ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ግን በርካቶች የአገሪቱ ሰብል አምራች አካባቢዎች በድርቅ የተመቱ በመሆናቸው፣ አጠቃላይ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከዚህ በላይ እንደሚያሻቅብ ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡

Leave a Reply