Wednesday, 11 November 2015 13:40

·  በግብፅ እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ውጥረት ነግሷል

·  ሳዑዲ ዓረቢያ በናይል ወንዝ ላይ ለሱዳን ሶስት ትልልቅ ግድቦች ልትገነባ ነው

·  የሳዑዲ አረቢያ መከላከያ ሚኒስትር በአዲስ አበባ

·  የየመን ጦርነት አደራዳሪ አልባ ሆኗል

በሳምሶን ደሣለኝ

በየመን የተደረገው፣ እየተደረገ ያለው ጦርነት አቅጣጫው ወዴት እየሄደ እንዳለ አሁን ላይ ሆኖ መናገር በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል። የፖለቲካ ተንታኞች ለጦርነቱ መንስኤ የተለያየ ምክንያቶች እየሰጡ ይገኛሉ። ጦርነቱ ከውስጣዊ ችግሮች በዘለለ፣ ከባቢያዊ መሰረት ያለው ጦርነት አድርገው የሚተነትኑ ባለሙያዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል። ከሁሉ በላይ በዚህ የየመን ጦርነት መነሻ በዓረቡ ዓለም አዲስ የኃይል አሰላለፉ ይዞ እየመጣ መሆኑ በስፋት እየታየ ያለ ጉዳይ ነው። በተለይ በሳዑዲ አረቢያና በግብፅ መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን መረጃዎች ያሳያሉ።

በግብፅ ሻርም-አል-ሼክ እ.ኤ.አ. ማርች 28 እና 29 ቀን 2015 በተደረገ የዓረብ ሊግ ስብሰባ የዓረብ ሀገሮች የጥምር ጦር ሰራዊት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወቃል። በዚህ የጥምር ጦር አደረጃጀት ላይ በወቅቱ በሳዑዲ አረቢያ እና በግብፅ መካከል መሰረታዊ ልዩነቶች ተንጸባርቀዋል። ግብፅ ተቋማዊ ይዘት ያለው ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ትብብር እንዲኖር ያላትን ፍላጎት ስታንጸባርቅ፤ ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ በጊዜያዊ ኮሚቴ የሚመራ ለአጭር ጊዜ የሚመሰረት ወታደራዊ ትብብር እንዲፈጠር ሃሳብ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።

በሻርም-አል-ሼክ ስብሳባ የዓረብ ሊግ ያሳለፈው ውሳኔ አጠቃላይ መንፈሱ እንደሚለው፣ የሚዋቀረው ጥምር ጦር ሰራዊት በአባል ሀገሮች ላይ በሚፈጠር የሉዐላዊነት ችግር ፈጥኖ ጣልቃ በመግባት የአባል ሀገሩን ሉዐላዊነት የማስከበር አቅም እንዲኖረው ይደረጋል። እንዲሁም በአባል ሀገሮች በድንበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን ይከላከላል። ጥምር ጦር ሰራዊቱ 40ሺ ጦር ሰራዊት ይኖረዋል። አፈፃጸሙን በተመለከተ በአባል ሀገሮች ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል በሚደረግ ተከታታይ ስብሰባ የሚወሰን ይሆናል የሚል ነበር።

ግብፅ የፓን አረብ ጦር ሰራዊት ለማቋቋም እቅድ ያቀረበችው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ የመሆናቸው እድል እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ ነው። በተለይ የሙስሊም ወንድማማቾች ፖለቲካ ፓርቲ ከግብፅ የፖለቲካ መድረክ ከተወገደ በኋላ፣ ግብፅ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ሆናለች። የግብፅ መንግስትም የሙስሊም ወድማማቾች ፖለቲካ ፓርቲን አሸባሪ ድርጅት ነው ብሎ ከመሰየሙም በላይ፣ የነበራቸውን ንብረቶች ሙሉ ለሙሉ በመውረስ ፓርቲውን ማፍረሱ ይታወሳል። በሌላ በኩል ግን ግብፅ የአሸባሪዎች ስጋት ስላስፈራት ሳይሆን፣ በፓን አረብ ጥምር ጦር ሰራዊት ምስረታ ስም በአካባቢ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋት ያለመ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት የግብፅ ጦር ሰራዊት በተቋም ደረጃ የተገነባ በመሆኑ የፓን-አረብ ጥምር ሠራዊትን ከግብፅ ውጪ መምራት የሚችል የለም ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ግብፅ 400 ሺህ መደበኛ ሠራዊት አላት።

በግብፅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝደነት መሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግስት በመገልበጥ ስልጣን የተቆናጠጠው የግብፅ ወታደራዊ ጁንታ ከዓረብ ሊግ አባል ሀገሮች በተለይ ከሳዑዲ፣ አረብ ኤምሬት እና ከኩዌት ከ2013 ጀምሮ 23 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ በማግኘት ሕልውናውን ማረጋገጥ ችሏል። ሆኖም ግን በየመን ጦርነት ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምር ጦር ሰራዊት ውስጥ ከአፍ ባለፈ ተሳታፊ አለመሆኑ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ውጥረት መንገሱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።

ሳዑዲ አረቢያ በየመን የሚደረገው ጦርነት የውስጥ ትግል ሳይሆን፣ ኢራን በአካባቢው ሀገሮች ላይ የበላይነት ለማግኘት የምታደርገው ጦርነት ነው ሲሉ ይከሳሉ። ይህም በመሆኑ ዘጠኝ የሚሆኑ የሱኒ እስልምና ተከታይ የአረብ ሀገሮችን በማስተባበር በየመን ጦርነት ውስጥ ጣልቃ ገብታ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመረች ወራቶች ተቆጥረዋል። በተለይ ኢራን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ከኒውክለር ቦምብ ጋር በተያያዘ የነበራትን ውዝግብ በዲፕሎማሲ መንገድ መቋጨቷ እና በየመን ጦርነት የሁዚ አማፂያን ወደ ስልጣን መምጣታቸው፣ ለሳዑዲ አረቢያን መንግስት የደህንነት ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።

በአንፃሩ ግብፅ ከኢራን እና ከየመን ሁዚ አማፂያን ጥምረት የበለጠ የሙስሊም ወንድማማችች ፖለቲካ ፓርቲ ከግብፅ ፖለቲካ መድረክ መገለሉን ተከትሎ የመጣው የአሸባሪዎች ጥቃት ከፍተኛ የደህንነት ስጋቷ ሆኗል። ይህም በመሆኑ በየመን ጦርነት ውስጥ የጦር መርከቦችን ወደ ቀይ ባሕር ከማስጠጋት ውጪ የእግረኛ ጦር አሰልፋ በቀጥታ በጦርነቱ ተሳታፊ መሆን አልፈለገችም። እስካሁንም አልተሳተፈችም። የየመን ጦርነትንም ቅርብ የደህንነት ስጋት አድርጋ አትቀበለውም። ይህ የግብፅ አቋም፣ በሳዑዲ አረቢያ በኩል ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ ሳዑዲ አረቢያ የአረቦች ፀደይ አብዮትን ተከትሎ ግብፅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ሲያጋጥማት፣ የአረብ ሀገሮችን በማስተባበር ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለግብፅ ወታደራዊ መንግስት ድጋፍ አድርጋለች። ከዚህ አንፃር የግብፅ ወታደራዊ መንግስት በየመን ጦርነት ላይ የያዘው አቋም አላስደሰታቸውም። በአፍ ከቀረበ ድጋፍ ውጪ ከግብፅ ወታደራዊ መንግስት እስካሁን የተገኘ አንዳች ተጨባጭ እርምጃ የለም። ይህም በመሆኑ ሳዑዲ አረቢያ ከግብፅ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምትመረምረው አሳውቃለች።

ሳዑዲ ዓረቢያ ለሱዳን ሶስት ግድቦች ልትገነባ ነው

ሳዑዲ ዓረቢያ የየመን ጦርነት ለደህንነቴ ያሰጋኛል ብትልም በዓረብ ሊግ በኩል አንድ ወጥ የሆነ አቋም ባለመያዙ ሌላ አማራጭ ለመጠቀም መገደዷ ይታወቃል። ይህም ሲባል ከዓረብ ሊግ ፈቃድ ሳያስፈልጋት በራሷ ባደረገችው የድረሱልኝ ጥሪ፣ ከዘጠኝ የዓረብ ሀገሮች ጋር ጥምር ጦር ሰራዊት በመመስረት ወደ ጦርነቱ ለመግባት ፈቃዳቸውን ማግኘት ችላለች። ከእነዚህ ሀገሮች መካከል አንዷ ሱዳን ነች። ሱዳኖች ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በመሰለፍ በየመን የጦር አውድማ ውስጥ በምድር ውጊያ እየተዋጉ ይገኛሉ።

እንደሚታወቀው ሰሜን ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር ከተለያዩ በኋላ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መዘፈቋ ይታወቃል። የሰሜን ሱዳን መንግስት የገጠመውን የገንዘብ ጉድለት ለማሟላት የወሰዳቸውን የተለያዩ የሪፎርም እርምጃዎችን በመቃወም አደባባይ የወጡ ብዙ ሱዳናዊያን ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው። ሰሜን ሱዳን ይህን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመሻገር ያላት ብቸኛ አማራጭ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን መጠቀም እንደሆነ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። ይህን ለማድረግ ከፍተኛ የውሃ መጠን መሸከም የሚችሉ ግድቦችን መስራት ይጠበቅባታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለመበደር የሰሜን ሱዳን መንግስት እየሮጠ ይገኛል።

የሰንደቅ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ከአስተማማኝ የመረጃ ቋት ያገኙት መረጃ እንደሚያሳየው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት እና የሰሜን ሱዳን መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ ሶስት ትልልቅ ግድቦች ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሰሜን ሱዳን በሚገነባው ግድብ በመጠቀም ለእርሻ የሚሆኑ መሬቶቿን ጥቅም ላይ እንደምታውል ይጠበቃል። የሰሜን ሱዳን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከሌሎች መንግስታት ቀደም ብሎ ብድር የጠየቀ መሆኑ ቢታወቅም፤ ሱዳን ለሳዑዲ ዓረቢያ የደህንነት ስጋት ጥሪ የሰጠችው ፈጣን እና ተግባረዊ ምላሽ ለስምምነቱ የራሱ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑን ዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ነግረውናል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተደረሰው የግድብ ግንባታ ስምምነትን በተመለከተ የግብፅ መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ነው። እንደ ዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ከሆነ፣ ግብፅ በዚህ ስምምነት ደስተኛ አትሆንም። ኢትዮጵያ ሃይል ለማመንጨት ብቻ በምትሰራው የሕዳሴ ግድብ ደስተኛ ያልሆነችው ግብፅ፣ የመስኖ ውሃ ለመያዝ በሚገነቡ ግድቦች ላይ ሊኖራት የሚችለው አቋም አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

የሳዑዲው መከላከያ ሚኒስትር በአዲስ አበባ

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመስራት ይፋ ካደረገችበት ጊዜ አንስቶ፣ እስካሁንም ድረስ ግብፅ የእጅ አዙር ተፅዕኖ ለማሳረፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። በተለይ የዓረብ ሊግን ለማስተባበር የሳዑዲ ዓረቢያን እገዛ አጥብቃ ትሻም ነበር። ግብፅ ሳዑዲን ከሕዳሴው ግድብ አንፃር መጠቀም የምትፈልገው፣ በሌሎች ዓረብ ሀገሮች ላይ ያላትን ተፅዕኖ በመረዳት እና በኢትዮጵያ ውስጥ የምታደርገውን ኢንቨስትመንት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከመፈልግ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው።

እ.ኤ.አ. በ2013 የአረብ ሀገሮች የውሃ ካውንስል ስብሰባ በካይሮ በተደረገበት ጊዜ፣ የቀድሞ ሳዑዲ አረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ካሊድ ቢን ሱልጣን የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ትልቅ ግድብ በመገንባት በግብፅ እና በሱዳን ሉዐላዊነት ላይ አደጋ ጋርጠዋል ሲሉ መክሰሳቸው የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታንም የፖለቲካ ሴራ እንጂ ከኢኮኖሚክ ጠቀሜታ ጋር በተያያዘ የሚገነባ ግድብ አይደለም ሲሉ ጨምረው መክሰሳቸው የአደባባይ እውነት ነው። ደግነቱ በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ እንደሚባለው፣ የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ አቋም የሳዑዲ አረቢያን መንግስት የማይወክል ከመሆኑም በላይ፣ በንጉስ ፉአድ መመሪያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።

አሁን ላይ በሳዑዲና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ጊዜ መሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል። አሁን በሁለቱ ሀገሮች ለደረሱበት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በዋና ድልድይነት የሚጠቀሱት የክብር ዶ/ር ሼክ ሙሐሙድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ናቸው። በሁለቱ ሀገሮች የሚደረጉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውጤቶችን ለመተንተን የሚፈልግ ባለሙያ፣ የሼክ ሙሐሙድን ኢንቨስትመንት ከግንዛቤ ሳያስገባ መተንተን አይችልም፣ አይቻለውም። በአሁን ሰዓት ከ110 ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የስራ እድልን የፈጠረ የኢንቨስትመንት መዋዕለ ንዋይ አፍስሰዋል፡፡

ባሳለፍነው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ የሁለት ቀናት ጉብኝት አደርጎ ነው የተመለሰው። ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከተጓዘው ቡድን ጋር የመከላከያ ኢታማጆር እና የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሩ አብረው መጓዛቸውን ለማወቅ ችለናል። በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ሳምንት የሳዑዲ አረቢያ መከላከያ ሚኒስትር መሐመድ ቢን ሳልማን ከከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ይፋዊ ያልሆነ ጉብኝት አድርገዋል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በወታደራዊ ትብብር ዘርፍም ከፍ ማለቱ አመላካች የሆነ ጉብኝት ተደርጎ በባለሙያዎች ተወስዷል። በተለይ በአሁን ሰዓት በየመን የሚደረገው ጦርነት እልባት በፍጥነት ካላገኘ ቀውሱ ወደ ምስራቅ አፍሪካም ሊዛመት እንደሚችል ተገምቷል። እስከአሁን ባለው ሂደት ከየመን የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለው የደህንነት ስጋት በጋራ ለመከላከል በሁለቱ ሀገሮች መካከል ውይይት መደረጉን መላምት ያስቀመጡ ባለሙያዎች አሉ።

የየመን ጦርነትን ማን ያደራድር?

ከተባበሩት መንግስታት ውጪ በሀገሮች ደረጃ የየመንን ጦርነትን ወደ ድርድር መምራት የሚችሉ ሀገሮች መኖራቸው አጠያያቂ ሆኗል። ምክንያቱም በአንድም በሌላም መልኩ በዚህ ጦርነት በቀጥታ የተሳተፈም አለ፤ ድጋፍ ብቻ የሰጠ አለ፤ ምንም ያላለም አለ። ይህም በመሆኑ ገለልተኛ ሀገር ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።

አሁን ካለው አማራጭ ግን ከአረብ ሀገሮች በዚህ ጦርነት እጇን ያላስገባችው ኦማን ብቻ ነች። ይህም በመሆኑ ድርድር በኦማን ከተማ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ሌላው አማራጭ አዲስ አበባ ነው። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ ለሚገኙት ስደተኛው ፕሬዝደንት እውቅና መስጠቱ ከሁዚ አማፂያን በኩል የአዲስ አበባ አደራዳሪነትን አጠራጣሪ ያደርገዋል። በአንፃሩ የቀድሞ የየመን ፕሬዝደንት አብደላ ሳላህን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት የሚችለው የአዲስ አበባው መንግስት ብቻ ነው። ይህም በመሆኑ ሳዑዲ አረቢያ አሁን ከገባችበት የጦርነት ቀውስ ለመውጣት የመውጫ ስትራቴጂ ለማበጀት ከወሰነች ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ይኖራታል። አንዳንድ ወገኖች የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስትሩ ጉብኝትም አንዱ ዓላማ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልፃሉ።¾

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply