15 November 2015 ተጻፈ በ 

‹‹ከ15 ዓመታት በፊት ለአንድ ስብሰባ ወደ ደቡብ አቅንቼ ነበር፡፡ በወቅቱ የክልሉ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ ተሳታፊዎች ያደረጉት ቲሸርት መፈክር “እኩል ነን!” የሚል ነበር፡፡ አሁን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በታሪክ ከተገፉና የተገለሉ ከነበሩት ከደቡቦች የተገኙ ናቸው፡፡

ከሃይማኖትም አንፃር በአገሪቱ የበላይነት ካለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ውጭ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ሐዋሳ ለስብሰባ ተገኝቼ የክልሉን ገዥ ፓርቲ አመራሮች ስለፌዴራሊዝም ስጠይቃቸው የነበራቸው የራስ መተማመንና ለሥልጣን ማዕከሉ የነበራቸው ቅርበት በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ አሁን ስለኃላፊነታቸውና ስለሚጫወቱት ሚና በድፍረትና በእኔንት ስሜት ነው የሚያወሩት፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ ላይ ጉልህ የሆነ ድርሻ አላቸው፡፡ ከብዝኃነትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ቢኖርባቸውም ደቡቦች ከሌሎች የኢሕአዴግ አባል ክልሎች በተሻለ እያደጉ ነው፡፡ ለነዋሪዎቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት እያደረጉት ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ የክልሉ አስተዳደር ቢሮክራሲ በማብዛትም አይታወቅም፡፡››

ይህ ምስክርነት የተሰጠው ከአገሪቱ ተቀዳሚ የፌዴራሊዝም ተመራማሪዎች አንዱ በሆኑት በዶ/ር አሰፋ ፍሰሐ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ጋር በመተባበር በአምስት አገሮች ላይ የፌዴራሊዝም የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ላይ ግምገማ የሚያደርግ የመነሻ ጥናት እየሠራ ሲሆን፣ ዶ/ር አሰፋ የዚሁ ጥናት አካል የሆነውን የኢትዮጵያ ክፍል ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በአምባሳደር ሆቴል የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ተወካዮች በተገኙበት መድረክ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ዶ/ር አሰፋ ይህንኑ ጥናት ለማድረግ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የመስክ ጉብኝት እንዳደረጉና ለጥናቱ ግብዓት የሆኑ መረጃዎችን በቃለ መጠይቅና በቡድን ውይይቶች እንዳገኙም ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ ለፌዴራሊዝም መዋቅር መዘርጋት መነሻ የሆነውን የአገሪቱን የፖለቲካ ታሪክ፣ የሕግ ማዕቀፍና በአፈጻጸም የተገኙ ግብረ መልሶችን በተለይም ተግዳሮቶችና ስኬቶችን የያዘ ነው፡፡

ውዝግብ በማያጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የፌዴራል መዋቅሩ ጉልህ ሥፍራ አለው፡፡ የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተለያዩ ጉዳዮችን የደነገገ ቢሆንም፣ በፌዴራል መዋቅሩ ላይ የሚጻፉት ሰነዶች ብዛት ሕገ መንግሥቱ ሌሎች ጉዳዮችን ያልያዘ ያስመስላሉ፡፡ ከይዘት አኳያም ጽሑፎቹ ፅንፍ የያዙ ናቸው፡፡ ለአንዳንዶች ብሔር ተኮር የሆነው የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ በሌላ ፅንፍ ለሚገኙት ደግሞ የአገሪቱን ታሪክ የተቀየረውና የስኬት ጎዳናው የተቀየሰው በፌዴራል ሥርዓቱ አማካይነት ነው፡፡

በዚህ መሐል ያሉ የሥርዓቱን በጎ ጎኖችና ድክመቶች በእኩል ዓይን የሚመለከቱ ምክንያታዊ ምሁራን ቁጥራቸው ይነስ እንጂ በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ይላሉ፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ለረጅም ጊዜያት የተመራመሩት ዶ/ር አሰፋ ከዚህ ጎራ የሚቀላቀሉ ናቸው፡፡ የመነሻ ጥናቱ ጭማቂም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ የተገጸው ዓይነት አዎንታዊ ለውጦች መኖራቸውን ከመመስከር ወደኋላ የማይሉት ዶ/ር አሰፋ፣ ሥርዓቱ ላይ የተጋረጡ ጉድለቶችንም ነቅሰው በማውጣት ይታወቃሉ፡፡

የፖለቲካ ታሪክ እንደ መነሻ

ዶ/ር አሰፋ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ያሉት ውዝግቦች ከአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ፣ ከይዘትና የሕግ አወቃቀሩ ጋር የተገናኙ መሆናቸውን የሚቀበሉ ሲሆን፣ የታሪክ አተረጓጎም ግን የጎላ ቦታ እንዳለው ያምናሉ፡፡ በታሪክ የነበረው ንጉሣዊ አስተዳደር የተለያዩ ግዛቶች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲወስኑ መፍቀዱ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ መደበኛ ባልሆነ መልኩ በታሪክም ቦታ እንደነበረው እንደሚያሳይም ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና በዚህም ጊዜ ቢሆን ጠረፍ አካባቢ ያሉ ክልሎች ይህ አንፃራዊ ነፃነት እንዳልነበራቸው አመልክተዋል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻና በ20ኛው ክፍለ መጀመሪያ ላይ በስፋት ተግባራዊ የሆነው የተማከለ አስተዳደርን የማስፋፋት ዘመቻ፣ ልዑላን የነበራቸውን ማዕከላዊ ሥልጣን የመጋራት ዕድል የገታ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የዚህ አካሄድ ተፅዕኖም በሥልጣንና በሀብት ክፍፍሉ ላይ የተንፀባረቀ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህ የአገር ግንባታ ፕሮጀክት የአገሪቱን ባህሪ እንደለወጠው የጠቆሙት ዶ/ር አሰፋ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የመጡት የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ክልላዊ እንቅስቃሴዎች ብሔር ተኮር ንቅናቄ እንዲያደርጉ ማስገደዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የበላይነት የነበረውና በማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ይመራ የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎቹ መደብና ብሔር ላይ የተመረኮዙና የተካረሩ እንዲሆኑ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ የፖለቲካ ጥያቄዎቹ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት ልሂቃን ዛሬ ታሪክ የሚተረጎምበትን አቅጣጫም ለመወሰን ጉልህ ሚና መጫወታቸውን እንደቀጠሉ አመልክተዋል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ላይ ታሪክ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የታሪክ ምሁራን በርካታ ትንታኔዎች እንደሚያሳዩም ጠቅሰዋል፡፡ ልሂቃኑ ዛሬ ላነገቡት አጀንዳ ደጋፊዎቻቸው ለድጋፍና ለተቃውሞ እንዲሠለፉ ለማድረግ ታሪክን በምሉዕነቱ ሳይሆን የተመረጡ የታሪክ ትርክቶችን ብቻ በማቅረብ ያላግባብ መጠቀም መቀጠላቸው የራሱን ጠባሳ ጥሎ እያለፈ እንደሆነም አስጠንቅቀዋል፡፡

ከዚህ ታሪካዊ ዳራ ተነሥቶ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓት እንደ ብሔር ጥያቄ ላሉ የመጀመሪያው ትውልድ የፌዴራሊዝም ጉዳዮች ምላሽ እንደሰጠ የሚከራከሩት ዶ/ር አሰፋ፣ የሥርዓቱ ተቺዎች የሚያቀርቧቸው ብዙኃነትን የማስተናገጃ አማራጭ አሠራሮች ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር እንዲዋሀዱ ከተደረጉ ተጨማሪ መንገዶች የመሆን ዕድል እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም አንዱ እንደ አሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ባሉ ሊበራሎች የሚደገፈው የዜጎች እኩልነት መርህ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ መርህ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ከተከበረና ሀብት ለሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎች በእኩልነት ከተከፋፈለ፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ ማንነት ጉልህ ቦታ እንደማይኖረው ያመለክታል፡፡ አልፎ አልፎም ይህ የመንግሥት ፖሊሲ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ይህን ለማሳለጥ ጠንካራ የፍትሕ አካልና ንቁ ሲቪል ማኅበረሰብ እንደሚፈለግም አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህን አካሄድ ተቃዋሚዎች በተለይ በምርጫ ወቅት እንደሚያቀርቡትም ገልጸዋል፡፡ ይህን ለመቀበልም ሆነ ለመቃወም አገር የሚመራበት ሁኔታ ወሳኝነት እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ አሠራሩን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በክልል ደረጃ የተለያዩ ችግሮችን እየተጋፈጡ ላሉት አናሳዎች ይህ አሠራር መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ግን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዜጎች እኩልነት ሁሉ ምርጫ ጠብቆ ብቅ የሚለው ሌላኛው አሠራር አካባቢያዊ ፌዴራሊዝም እንደሆነ ዶ/ር አሰፋ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አሠራር አሜሪካ የምትከተለው ቢሆንም በአፍሪካ ደረጃ በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጄሪያና በኬንያ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ በእነዚህ አገሮች የአንድ ብሔር አባላት ተበታትነው እንዲኖሩ እንደሚደረግና ብሔር ተኮር ፓርቲዎችም እንደሚከለከሉ አመልክተዋል፡፡

እነዚህ አማራጮች ለኢትዮጵያ ተገቢ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ የምትከተለው ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት ከልማታዊ መንግሥት ሞዴል ጋር በመሆን በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲፈጠርና የተሻለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለ ዶ/ር አሰፋ ያምናሉ፡፡ ይህ ስኬት በሙስና፣ በዘርፎች ውጤታማ አለመሆንና በመሳሰሉት ችግሮች የታጀበ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ለውጡ አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ለውጥ አገሪቱ በ1983 ዓ.ም. ከነበረችበት ሁኔታ ሲነፃፀርም አስደናቂ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም. የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ከአንድ ቡለቲን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የአገሪቱ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ላይ ጥርጣሬ እንዳለ አስረግጠው ማስረዳታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ወደ 17 የሚጠጉ ነፃ አውጪ ግንባሮች ባሉበት ሁኔታ የአገር መበታተን አደጋ ከንድፈ ሐሳባዊ መላምት የዘለለ ዕድል አለው፤›› በማለትም መናገራቸውን አውስተዋል፡፡

ይሁንና የፖለቲካ ብዝኃነትን ከማስተናገድ አኳያ የሽግግሩ ጊዜ አሁን ካለው እጅግ የተሻለ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በተለይ 87 አባላት የነበሩት ምክር ቤት የተለያዩ የፖለቲካ አቋም የነበራቸው አካላት የተወከሉበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡ የሽግግሩ ፓርላማ አባል የነበሩ ተቃዋሚዎች በሽግግሩ ማብቂያ ላይ ራሳቸውን ማግለላቸው የፈጠረው መምታታት አሁንም እንዳልጠራ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ሐሳቦች በሽግግሩ መንፀባረቃቸውን ያስታወሱት ዶ/ር አሰፋ፣ ከእነዚህም አንዱ በአገሪቱ አስተዳደር ላይ የተደረገውን ሥር ነቀል ለውጥ የሚቃወምና የቀደመው አካሄድ እንዲቀጥል የሚፈልግ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አቋም በሽግግሩ ጊዜ በፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና በሻለቃ አድማሴ ዘለቀ የሚንፀባረቅ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ይህን አቋም የሚደግፉ በቀድሞው ሥርዓት የተከናወኑ የአገር ግንባታ ፕሮጀክቶች በሌላው ዓለም ከተከናወኑት የተለዩ እንዳልሆኑ እንደሚከራከሩም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ለኢትዮጵያ ያለ ታማኝነት ከምንም በላይ ሊቀድም እንደሚገባና በየትኛውም ዋጋ ቢሆን ሊረጋገጥ ይገባል ብለው እንደሚከራከሩም ጠቅሰዋል፡፡ ባላቸው ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› መፈክር የተነሳ ብሔር ተኮር እንቅስቃሴዎችን በጥርጣሬ እንደሚመለከቱና ለኢትዮጵያዊነት ታማኝ ያልሆነ ገንጣይ የሆነ አመለካከት አድርገው እንደሚስሉትም አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ መዋቅርና ይዘት ተኮር ጥያቄዎች

ዶ/ር አሰፋ የሕገ መንግሥቱ የዲዛይን ችግር መሠረታዊ የአፈጻጸም ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል በሚል የሚከራከሩ ምሁራንን ሐሳብ ተገዳድረው የተለያዩ ሥራዎችን አቅርበዋል፡፡ በዚሁ የመነሻ ጥናትም ሕገ መንግሥቱን ‹‹ቸር ነው!›› ብለውታል፡፡ ለፌዴራል መንግሥቱ፣ ለክልሎችና ለአካባቢያዊ አስተዳደሮች የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ለእነዚህ አካላት የፖለቲካ ምኅዳር እንደፈጠረም አመልክተዋል፡፡ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ከመፈቀዱም በላይ ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ ፖሊሲዎችን የመቅረፅ ነፃነት እንዳጎናፀፋቸውም ገልጸዋል፡፡ በተለይ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጣቸው ሥልጣን ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የሚጋሩት ሲሆን፣ ፌዴራል አቀፍ ደረጃዎችን የፌዴራል መንግሥቱ የማውጣት ሥልጣን ሲሰጠው ክልሎች ልዩ ሁኔታዎቻቸውን ከግምት ውስጥ እያስገቡ እንዲሠሩ ማዕቀፉ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ በተቃራኒ በተግባር በክልሎች መካከል የፖሊሲ ልዩነት እምብዛም እንደማይስተዋል ዶ/ር አሰፋ አስታውሰዋል፡፡ ይህ አገሪቱ በአውራ ፓርቲ የምትመራና ገዥው ፓርቲም የተማከለ ፖሊሲ የማውጣት ሒደት የሚከተል በመሆኑ የመጣ ተፅዕኖ እንጂ፣ በሕገ መንግሥት የዲዛይን ክፍተት እንዳልሆነም ተከራክረዋል፡፡ በአፋርና በሶማሌ ተንቀሳቃሽ ቀበሌዎች እንዲቋቋሙ መደረጉ ክልሎች ለልዩ ተጨባጭ ሁኔታቸው የተሻለ ምላሽ እየሰጡ እንደመጡ የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ክልሎችና አካባቢያዊ አስተዳደሮች የፌዴራል መንግሥቱን ፖሊሲዎች ኮፒ ያደርጉ እንደነበር ግን አስታውሰዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች በርካታ ኃላፊነቶችን ቢሰጥም ይህን ለመወጣት የሚያስችል የገቢ መሠረት እንዳልጣለ ግን አመልክተዋል፡፡ አገሪቱ ከምታገኘው ገቢ ውስጥ አብዛኛው ወደ ፌዴራል መንግሥቱ እንዲገባ ታስቦበት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የክልል መንግሥታት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥገኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የአዲሱ ትውልድ የፌዴራሊዝም ጥያቄዎች

ዶ/ር አሰፋ በ1983 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አመራሮቹ በ25 ዓመታት ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ላይ አቋም እንዲቀይሩ መገደዳቸውን የጠቀሱ ሲሆን፣ የዚህ አንዱ መገለጫ በፌዴራሊዝም አፈጻጸም ላይ ያሳዩት ለውጥ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የባንዲራ ቀን፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተደረገው ለውጥ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣበት ሰሞን ትኩረት ይደረግበት የነበረው በብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ብዝኃነት ጉዳይ ወደ የሕዝቦች የጋራ አጀንዳ ሽግግር መደረጉን የሚያመላክቱ እንደሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

ይሁንና ሥርዓቱ ዜጎችን በፖሊሲ ቀረፃ የማያሳትፍ መሆኑ አጥጋቢ ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ እንደሆነ ዶ/ር አሰፋ አመልክተዋል፡፡ በፖሊሲ ጉዳይ ሕዝቡ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚጠራው ስብሰባ ገዥው ፓርቲ ያዘጋጀውን ሰነድ ለሕዝቡ ለማስረዳት የሚያደርገው ስብሰባ ሆኖ እንደሚጠናቀቅም፣ በቅርቡ የተካሄደውን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተደረጉ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በምሳሌነት በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡

በክልሎች የሚገኙ አናሳዎች እየደረሰባቸው ያለው አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መድልኦ አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ እንደሆነም መክረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የገነቡት ድንበር ተሻጋሪና የጋራ እሴቶች በተገቢው መንገድ እንዲስፋፉም ጥረት መደረግ እንዳለበት በመስክ ጉብኝታቸው ካገኙት ግብዓት ጋር በማጣቀስ አመልክተዋል፡፡

የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ያሉ ከተሞች ባሉበት የፌዴራል ሥርዓት አዲስ አበባ ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት መደረጉ ሊቆም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ 60 በመቶ የአገሪቱ ኢንቨስትመንት መገኘቱ፣ እንዲሁም በ2008 የበጀት ዓመት ከአራት ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ ያላት አዲስ አበባ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካለው የአማራ ክልል በላይ በጀት የተመደበላት መሆኑ ጤናማ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው በፖለቲካ ብዝኃነት አለመታጀቡና የተቋማት ግንባታውም ያለበት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ተብለው በዶ/ር አሰፋ ከተለዩት የሚካተቱ ናቸው፡፡

ዶ/ር አሰፋ የመነሻ ጥናቱን አቅርበው ከጨረሱ በኋላ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ፣ በአገሪቱ የሰፈነው ሰላምና ደኅንነት ለተገኙት አንፃራዊ ስኬቶች ያደረገው አስተዋጽኦ በጥልቀት ሊመረመር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አኳያ ያለበት ጉድለትም ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልገው ነው ብለዋል፡፡

የፊስካል ፌዴራሊዝም (የገንዘብ ነክ ፌዴራሊዝም ጉዳዮች) ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ንጉሤ በ1983 ዓ.ም. የነበረው የፖለቲካ ጥርጣሬ በ2008 ዓ.ም. ካለው በምን ይለያል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ አቅምን በምን እንለካዋለን?›› ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፣ ጠንካራ ክልላዊ ፓርቲዎችና የተለያዩ አካላት ሙሉ ተሳትፎ እስካላደረጉ ድረስ የመንግሥት ጥንካሬ ዘላቂ እንደማይሆንም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ዘሪሁን ይመር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ አጥጋቢ ሥራ በፍጥነት ካልተሠራ የዘር ማጥፋት ወንጀል አይሠራም የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኔ ይሄ ይፈጸማል ብዬ እፈራለሁ!›› ብለዋል፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎና እንደ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማት መጠናከራቸው አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ክርስቶፍ ቫንደር ቤከን፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በስፋት ዕውቅና የተሰጠው የዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ፣ በፌዴራሊዝም ጥናቶችና ውይይቶች በቂ ትኩረት እንደማይሰጠውና እንደሚዘለል አመልክተዋል፡፡ በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ ትኩረት የሚሰጠው የዜጎች እኩልነት መርህ በተወሰኑ መልኩ ከዚህ እንደሚጣጣም አስገንዝበዋል፡፡

Source  =  Ethiopian Reporter

 

Leave a Reply