Wednesday, 18 November 2015 13:57

 በስልጣን ዘመኑ ለክልሉ ህዝብ ምን ሰራ?

በይርጋ አበበ

የክልሉ መንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ያነገተ ወጣት እየዘፈነ ያሳያል። ዘፈኑን የሚያቀነቅነው የቀድሞው ወጣት ታጋይ የአሁኑ ኮማንደር አዲሱ ሀይሉ (ዳምሳሽ) ሲሆን የዘፈኑ ርዕስ ደግሞ “እንዳያልፉት የለም ያሁሉ ታለፈ” የሚለው በታጋይ ዮሴፍ ህላዊ የተደረሰ ግጥም ነው። አቶ ህላዊ ዮሴፍ የዚህችን ዘፈን ግጥም የጻፏት ድርጅታቸው ኢህዴን ደርግ ኢሰፓን እየታገለ ትግሉ በወሎ ጠቅላይ ግዛት አካባቢ በደረሰበት ወቅት ነበር።

የአማራ ክልል መንግስት የሆነው ብአዴን የፊታችን ቅዳሜ የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመት የልደት ቀኑን ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆኑን ተከትሎ የኮማንደር አዲሱ እንዳያልፉት የለም ዘፈን ከበርካታ የልማት ዜናዎችና የብአዴንን ጉዞ በስኬት መታጀቡን ከሚገልጽ መዘሙር ጋር እየተዋሴረች ትቀርባለች። በዚህ መሃል ታዲያ ነባር የብአዴን ታጋዮችም በቴሌቪዥን ጣቢያው ካሜራ ፊት ተቀምጠው ሰፋ እና ዘርዘር ያለ ዲስኩር ያቀርባሉ። በነባር ታጋዮቹ ወይም በአሁኖቹ ባለስልጣናት ሰፊ ማብራሪያ መሃል ታዲያ የሚሰማው “ሁለት ፈታኝ ትግሎችን ማለትም ጫካ በነበሩበት ጊዜ ከደርግ ጋር የተደረገውን እና አሁን ከድል በኋላ ደግሞ መንግስት ሆነው የገጠማቸውን የድህነት ትግል እንዴት በድል እየተወጡት እንዳሉ” የሚገልጹበት ሰፊውን ቦታ ይይዛል።

በሌላ በኩል ደግሞ የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ አንድ ዘጋቢ ፊልም እያሳየ ነው። የቢቢሲው ጋዜጠኛ “እንዳያልፉት የለም” የምትለው የአቶ ህላዊ ዮሴፍ መዝሙር በተገጠመችበት አካባቢ ራያ ቆቦ በመሄድ ወይዘሮ ብርቱካን ዓሊ የተባሉ እማውራ አብዲ መሃመድ ይባል የነበረ ልጃቸው በርሃብ ምክንያት እንደሞተባቸው እየተናገሩ ያሳያል። ዘጋቢ ፊልሙ ከወይዘሮ ብርቱካን መሪር ሀዘን በተጨማሪ ሌሎች በርሃብ ምክንያት ስጋቸው ከሰውነታቸው ሸሽቶ አጥንታቸው የሚቆጠርና ሆዳቸው የተወጠሩ ህጻናትን፣ ልጆቻቸው ተርበው የሚያበሏቸው በማጣታቸው እያለቀሱ ያሉ ጎስቋላ ወላጆችን (ወንዶችንና ሴቶችን) እና የሚልሱት የሚቀምሱት በማጣታቸው በቁማቸው የደረቁ እንስሳትን ያሳያል። የሞቱ እንስሳት አጽምም ይታያል።

ከላይ በሁለት አንቀጾች ተጽፎ የቀረበው መግቢያ የአማራ ክልል ሰሞንኛ ሁኔታን የሚያሳይ ነው። ክልሉን የሚያስተዳድረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ነው። ክልሉንም ላለፉት 24 ዓመታት ከስምንት ወራት እያስተዳደረ ሲሆን ቢያንስ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ከአራት ወራት ክልሉን ማስተዳደር የሚያስችለውን ባለ 294 ወንበር የክልሉን ምክር ቤት በብቸኝነት ተቆጣጥሮታል። በዛሬው ዝግጅታችንም የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለአማራ ክልል ህዝብ ባለፉት 24 ዓመታት ምን አስገኝቶለታል? የክልሉ ህዝብስ ከብአዴን የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚሉትን ሀሳቦች ይዘን ቀርበናል።

 

 

ብአዴን ማን ነው?

ብአዴን ማን ነው? ለሚለው የዚህ ጽሁፍ ጥያቄ መልስ የሚሰጠው ራሱ ብአዴን ይሆናል። ድርጅቱ በድረ ገጹ ከአመሰራረቱ ጀምሮ አሁን እስካለበት ድረስ ያሉትን የሂደት ደረጃዎች በዝርዝር ያስቀምጠዋል። የፓርቲው ድረ ገጽ “ብአዴን የተወለደው ከኢህዴን ነው” በማለት ይጀምርና “ኢህዴን ደግሞ የኢህአፓ ልጅ ነው” በማለት ስለ ፓርቲው አነሳስ ይገልጻል። ፓርቲው ከኢህአፓ ወደ ኢህዴን ከተሸጋገረ በኋላም ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም የትግራይ ህዝቦች የነጻነት ግንባር ወይም ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እርዳታ እና ድጋፍ ከፍተኛ ነበር ሲል ያክልበታል። የፓርቲው የምስረታ ቦታም ዋግህምራ ሲሆን ይህ ቦታም በዚያን ዘመን አጠራሩ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ነው ሲል ይገልጸዋል። ከ1973 ዓ.ም ጀምሮም  ደርግን ከስልጣን ለማውረድ የህይወት መስዋዕት ከፍሎ ታግሏል፣ ይላል ይሄው የፓርቲውን ድረ ገጽ ዋቢ በማድረግ ጽሁፉን ያሰፈረው ዊኪ ፔዳ ድረ ገጽ። “The Ethiopian People’s Democratic Movement (EPDM), the precursor of ANDM, the founding fathers were the former members of the Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP) who splintered themselves from the party and supported by the Tigrayan People’s Liberation Front (TPLF).[3] It was originally based inWaghimra in Wollo Province, and waged an armed struggle against the Derg in that area starting in 1982”

ብአዴን ዋግህምራ ላይ ሲመሰረት ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሆኖ ሲሆን ስያሜውም የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) እንደነበረ የሚገልጸው ፓርቲው በሂደት ግን ከህብረ ብሔራዊነት ወደ ብሔርተኝነት ፓርቲ ስሙን እንደቀየረ ይገልጻል። የስያሜ ለውጥ የተካሄደውም በ1986 ዓ.ም መሆኑን አስፍሮታል።

EPDM convened its first organizational conference in Jerba Yohannes, Waghimra, in November 1983. In 1989 EPDM and its long-time ally TPLF united to form the Ethiopian People’s Revolutionary Democratic Front (EPDRF).[3] At its third organizational conference in 1994, the EPDM changed its name to Amhara National Democratic Movement (ANDM), marking its transition from a pan-Ethiopian movement to an ethnic party.[3] In the May 2010 Regional State Council elections, the ANDM won all 294 seats in the Amhara Region ሲል ያስቀምጠዋል።

ፓርቲው በአሁኑ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉኝ ሲል በድረ ገጹ ያሰፈረ ሲሆን በክልሉ ህዝብም አመኔታ ያገኘሁ ነኝ በማለት ይገልጻል። ብአዴን ማለት ይህ ከሆነ ቀጥሎ ደግሞ ፓርቲው ላለፉት 296 ወራት በስልጣን ላይ ቆይቶ ያከናወናቸውን ተግባራት እና የክልሉን ህዝብ ጥያቄ እንመለከት።

 

 

ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው

የአማራ ክልል በስምንት ትላልቅ ዞኖች (ሰሜን ጎንደር ደቡብ ጎንደር ሰሜን ሸዋ ምስራቅ ጎጃም ምዕራብ ጎጃም እና ዋግሕምራ) እና በሁለት የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች (ኦሮሚያ እና አዊ ብሔረሰብ ዞኖች) እንዲሁም በአንድ የከተማ ልዩ ዞን (ባህር ዳር ከተማ ልዩ ዞን) የተከፈለ ነው። የክልሉ ህዝብ ከ20 ሚሊዮን የሚልቅ እንደሆነ ሲነገር የክልሉ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ ደግሞ እንደ አብዛኞቹ የአገራችን ክፍሎች በግብርና ላይ የተመረኮዘ ነው። ከ20 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ተብሎ ከሚጠበቀው የክልሉ ህዝብ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይይዘው ከትምህርት ቤት ደጃፍ ያልደረሰ እንደሆነ ይነገራል። ይህም የክልሉ ኢኮኖሚ ለቀጣዮቹ ዓመታትም ከግብርና ላይ የሚነሳ እንዳይሆን ያደርገዋል ማለት ነው።

ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን ያህል አኃዝ ያለው ህዝብ የሚያስተዳድር መንግስት ከሚያስተዳድረው ህዝብ የሚነሳው ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። የክልሉ ህዝብም በተደጋጋሚ ከሚያነሳቸው አብይ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ፓርቲው ምን አከናውኗል? የሚል ጥያቄ መነሳቱም ተገቢ ይሆናል።

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በመጀመሪያ ፓርቲው በራሱ ድረ ገጽ ያሰፈረውን እንመልከት “ብአዴን የክልሉን ህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል አድርጓል። ድርጅቱ በተለይም በህዝቡ አመኔታ እንዲያገኝ ያደረገው በግብርና ልማት፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በኢንቨስትመንት እና የአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ለማሳደግ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ስራ አከናውኗል” ይላል።

የክልሉ ህዝብስ ምን ይላል? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ በተለይ ለሰንደቅ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ወጣቶች “በክልሉ የፓርቲ የበላይነት እንጂ የህዝብ እኩልነት የለም። የተማረው ወጣት ስራ የሚይዘው በፓርቲ መታወቂያው እንጂ በትምህርት ብቃቱ ተለክቶ ሁሉን አሳታፊ የሆነ መመዘኛ ፈተና ተዘጋጅቶለት አይደለም” ብለዋል።

ፓርቲው በግብርና ልማት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ስራ ሰርቻለሁ ቢልም የሰሞኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ጨምሮ የተለያዩ የመዋለ ንዋይ ባለሙያዎች “ክልሉ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና በቂ የዝናብ መጠን የሚያገኝ ቢሆንም የክልሉ አርሶ አደር ግን ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ነው። አርሶ አደሩን አንድ ለአምስት በሚባል የፓርቲ መዋቅር ጠርንፎ በመያዝ ከእሱ አስተሳሰብ የተለየውን ደግሞ በማዳበሪያ እዳ እያሰቃየ ይገኛል” ሲሉ ይናገራሉ። ሰሞኑን ለዓለም የተሰራጨው የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም በበኩሉ በመላው አገሪቱ በደረሰው የዝናብ መዛባት (አንዳንዶች ድርቅ ይሉታል) ምክንያት ርሃብ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ የአማራ ክልል ነው።

የግብርና ምርትን ለማሳደግም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዳልተደረገ እና በክልሉ ከ25 ዓመታት በፊት ይታረስ እንደነበረው ዛሬም በበሬ ጫንቃ የሚሳብ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እንደሆነ እየተነገረ ቢሆንም ብአዴን ግን የግብርና ልማትን በተጨባጭ ማሳደግ ችያለሁ ብሏል። በኢንቨስትመንት በኩል ክልሉ ምን ያህል ኢንቨስተሮችን በመሳብ በኩል በተለየ መልኩ ከክልሉ ዞኖች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞንን ብቻ ለማየት እንሞክር።

የጥረት ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን በደብረ ብርሃን ከተማ አንድ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በውይይት መድረኩ የዞኑን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ነበር። በጥናታዊ ጽሁፉ የቀረበው ነጥብ በዞኑ የኢንቨስትመንት ስራ ከገጠሙ መሰናክሎች መካከል አንዱ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ምሁራን እና ባለሀብቶች ወደ ትውልድ ቀያቸው ሂደው መዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ስራ አለመጀመራቸው ነው። ይህ መረጃ የዞኑ አስተዳደር የሰጠው መረጃ ሲሆን በሌሎች ዞኖችም ተመሳሳይ አካሄድ እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሚያሳየው የሰሜን ሸዋም ሆነ ሌሎች የክልሉ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ለአካባቢ ተወላጅ ባለሃብቶችና ምሁራን ተስማሚ አለመሆናቸው ነው የሚል መላምታቸውን ለሰንደቅ ተናግረዋል።

 

 

የአማራ ህዝብ የፖለቲካ እና የወሰን ጥያቄ

የክልሉ ህዝብ ባለፉት 25 ዓመታት ያለማቋረጥ ከሚያቀርባቸው ጥያቄዎች መካከል ቀዳሚው ጉዳይ ቢኖር የፖለቲካ እና የወሰን ጥያቄ ነው። አማራ ክልል ከአጎራባች ክልሎችም ሆነ ከጎረቤት አገር አዋሳኝ ድንበሮች ጋር በተገናኘ በርካታ ጥያቄ የሚነሳበት ክልል ነው። በሰሜን ትግራይ፣ በሰሜን ምስራቅ አፋር፣ በምዕራብ ሱዳንና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ክልል የሚያዋስኑት አማራ ክልል በተለይ ከሱዳን እና ከትግራይ ክልል ጋር በሚያዋስኑት የድንበር አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሳ የቆየ ክልል ነው። በዚህ ጥያቄው ምክንያትም በተደጋጋሚ ጊዜ አነስተኛ እና መካከለኛ ግጭቶች ተከስተዋል።

ከቅርብ ጊዜዎቹ እንኳ ብንጀምር ከሶስት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከሱዳን ጋር በድንበር ይገባኛል ምክንያት በተነሳ ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን ሱዳን ትሪብዩን አስነብቧል። በዚህ ጉዳይ ግን የአማራ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ያሉት ነገር የለም።በሰሜን ጎንደር ዞን ምዕራባዊ ክፍል እና በሰሜን ወሎ ክልሉን ከሚያዋስነው የትግራይ ክልል ጋርም እስካሁን ያልተፈቱ እና ወደፊትም ስጋት የሆኑ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ሲኖሩ የክልሉ ህዝብም በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጥያቄ ነው።

በክልሉ ከሚኖሩ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የቅማንት ብሔረሰብ የእውቅና ይገባኛል ጥያቄ ያስነሳው ግጭትም ከሰሞኑ የበርካታ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሳበ ክስተት ነው። ከዚህ በተጨማሪም የአማራን ክልል መሰረት ያደረጉ ሰላማዊ ትግልን የመረጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በብአዴን ከሚያቀርቡት አቤቱታ መካከል በክልሉ በሰላማዊ መንገድ እንዳንታገል በሮቹን ሁሉ እየዘጋ ነው በማለት ነው። (በዚህ ጉዳይ ኢህአዴግንም ሆነ አጋር ፓርቲዎችን ተቃዋሚዎች በተመሳሳይ ክስ ያቀርቡባቸዋል)

የሀይል አማራጭን በብቸኝነት መጠቀምን የመረጡ ነፍጥ ያነሱ ቡድኖችም በብዛት የሚገኙት በአማራ ክልል ነው። እነዚህ ሀይሎች መሰረታቸውን አማራ ክልል አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን መንግስት “ፓርቲዎቹን አላውቃቸውም” ብሎ ቢናገርም በተደጋጋሚ ጊዜ ግን ከእነዚህ ሀይሎች ጋር በምስጢር ሲገናኙ እና መረጃ ሲለዋወጡ ደርሸባቸዋለሁ ብሎ በፍርድ ቤት በአደባባይ ይከሳቸዋል። መንግስት እውቅና ባይሰጥባቸውም ተጠርጣሪዎችን የሚከስባቸው የትጥቅ ትግልን መርጠው ጫካ የገቡ ተቃዋሚ ሀይሎች ግንቦት ሰባት፣ አርበኞች ግንባር፣ የአማራ ወጣቶች ንቅናቄ፣ የአማራ ዴክራሲያዊ ሀይሎች እና የመሳሰሉት ይገኝበታል።

ከእነዚህ በተጨማሪም የአማራ ክልል ህዝብ በአስተዳዳሪው ብአዴን በርካታ ስራዎች እንዲሰሩለት አሁንም ጥያቄውን እያቀረበ ይገኛል። የመልካም አስተዳደር፣ የጸጥታ፣ የሰመረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች የማህበራዊ ጉዳዮችን ጥያቄዎች ያቀርባል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በደቡብ ክልል ጉራ ፋርዳ ወረዳ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጸም ብአዴን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱን በማንሳት ቅሬታቸውን የሚያቀርቡ የክልሉ ነዋሪዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

እነዚህና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ከክልሉ ህዝብ የሚቀርብበት ብአዴን የፊታችን ቅዳሜ 35ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በባህር ዳር ከተማ በድምቀት እንደሚያከብር ቀነ ቀጠሮ ቆርጧል። ብአዴን በበኩሉ ገና ያልመለሳቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ያልካደ ቢሆንም እስካሁን የሰራሁት በራሱ እውቅና ሊሰጠኝ ይገባል ያለ ይመስላል።

ምንጭ ስንድቅ

Leave a Reply