Thursday, November 19th, 2015
15 ሚሊዮን ሕዝብ ተርቦ በሚሊዮኖች ብሮች እየፈሰሰ እየተከበረ በሚገኘው የብአዴን (ብዙዎች “በድን” ይሉታል) 35ኛ ዓመት በዓለን አስመልክቶ ሽር ጉዱ እንደቀጠለ ነው:: ፍርፋሪ እየተወረወረላቸው ወይም በተስፋ የሚሰሩት መንግስታዊ ጋዜጠኞች የተለያዩ ባለስልጣናትን ቃለምልልስ እያደረጉ በማቅረብ ላይ ናቸው:: ከነዚህም መካከል በቅርቡ ሞተዋል ተብሎ የተዘገበላቸውና በኋላም አልሞቱም ተብሎ የተወራላቸው አቶ በረከት ስምዖን (ብዙዎች በቁማቸውና በሕዝብ ልብ ውስጥ ከሞቱ ቆዩ ይሏቸዋል) ቃለምልልስ ተደርጎላቸዋል:: በአማራ ክልል ቴሌቭዥን ላይ የቀረቡት አቶ በረከት በአብዛኛው ለማውራት የፈለጉት ስለኢሕ አፓ ነው:: “ኢሕአፓ ትልቅ አቅም ይዞ ተነስቶ ያንን ያባከነ ድርጅት ነው” ያሉት የአቶ በረከትን ቃለምልልስ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ዘ-ሐበሻ እንደወረደ አስተናግዳዋለች::

ጋዜጠኛው አቶ በረከትን ሲያስተዋውቅ እንዲህ ይላቸዋል “በጐንደር ከተማ አስተዳደር አባጃሌ ተብሎ በሚታወቀው ቀበሌ ውስጥ ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በጐንደር ከተማ ተምረዋል፡፡ ከ1967 እስከ 1968 ዓ.ም እድገት በህብረት ዘመቻ አዲርቃይ ከተማ ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ከሀምሌ 1968 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ ተቀላቅለዋል፡፡ ኢሕአፓ ሲፈራርስ ከኢሕአፓ ወጥተው ኢሕዴንን ከመሰረቱት ነባር ታጋዮች አንዱ ናቸው፡፡”

ቃለምልልሱን እንደወረደ እነሆ:-

ወደ ኢህአፓ እንዴት ተቀላቀሉ?

የ1960ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ አብዮት ንቅናቄ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር:: በወቅቱ የነበሩት ተማሪዎች በጣም ብስለት ያላቸው ሀሣቦች እያነሱ አገሪቱን ይመራ የነበረውን ዘውዳዊ አስተዳደር ይሞግቱ፣ ይታገሉ ነበር:: ትግሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ደግሞ ያኔ በነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት ነው:: ይህ ግን በእነሱ ብቻ የታጠረ አልነበረም:: ብዙም ሳይቆይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዛወረ:: ዘውዳዊውን አገዛዝ በመቃውም የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ የአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት እንዲረጋገጥ፣ ሙሰኝነት እንዲወገድ፣ የብሔሮች እኩልነት እንዲከበር ትግል ይካሄድ ነበር:: በ1960ዎቹ መጀመሪያ በተለይም ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ እኛም ወደ ተማሪዎች ነቅናቄ መቀላቀል ጀመርን:: ሁኔታው ከዚያ በፊት የነበሩት ትልልቅ ተማሪዎች የሚያነሷቸውን በጣም ብስለት የተሞላባቸው ሀሣቦች እንድንሰማ፣ ለፖለቲካ እንድንጋለጥ ሠፊ እድል ሰጦን ነበር::

በዚህ መሠረት እኛም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሆነን ትግሉን ተቀላቅለናል:: ቀስ በቀስ የህዝቡ ትግል እየተጠናከረ ሂዶ በ1966 ዓ.ም መላው ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ንጉሳዊውን አስተዳደር መታገል ይጀምራል::ትግሉ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ የተማሪዎች ንቅናቄ ያንን ትግል ወደ ፖለቲካዊ ስልጣን ለማምጣት የሚያስችል ብልሀት ጐድሎት ተገኘ:: ይህን ጉድለት ለመሙላት የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት በጣም አስፈላጊ ሆኖ መጣ:: ይህን ተከትሎ ብዙ ድርጅቶች ተመሰረቱ::

ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ህወኃት፣ ኢኮፖ/ኢትዮጵያ ኮሚኒስት ፓርቲ/ የመሳሰሉ በርካታ ድርጅቶች መመስረት ቻሉ:: ከተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በወቅቱ በመሀል ሀገር ሰፊ ተቀባይነት የነበረው ድርጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ/ ኢሕአፓ/ ነበር:: ስለዚህ እኛም እ ን ደ ማ ን ኛ ው ም የድርጅት ጥማት እ ን ደ ነ በ ረ ው ወጣት ኢሕአፓን ለመቀላቀል ቻልን::

ስለዚህ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ኢሕአፓን በአባልነት ለመቀላቀል በቃሁ:: ስለኢሕአፓ ምን ይላሉ? ኢሕአፓ ሲጀመር ዴሞክራሲያዊ የትግል ፕሮግራም ይዞ የተነሳ ድርጅት ነው:: በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት በህብረተቡም ፣ በወጣቱ ትውልድም የነበረውን ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጐት ተንተርሶ ፕሮግራሙን የቀረፀ ድርጅት ነው:: ስለዚህ በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ላይ ብዙ ሊሻሻሉ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉት ሆኖ ኢሕአፓ የሚያታግል ድርጅት ነበር::

በማንኛውም የድርጅት ፕሮግራም ሲጀምር ባለቀለት መልኩ ምንም መሻሻል በማይፈቅድ መልኩ አይደለም የሚዘጋጀው::በሂደት ሊሻሻል የሚችልበት እድል እንደተጠበቀ ሆኖ ለመነሻ ያህል ግን አስፈላጊዎችን የትግል አላማዎች በትክክል የያዘ፣ የትግሉን ስትራቴጅዎች በወሳኝነት የሚያመለክት ሆኖ ከተዘጋጀ ብቁ የትግል መሣሪያ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ነበር:: ኢህአፓም የዚህ አይነት ፕሮግራም ነው የነበረው:: ህውኃትም በወቅቱ የነበረው ፕሮግራም፣ ሌሎች ፓርቲዎችም የነበራቸው ፕሮግራም በሂደት ነው እየተሻሻለና እየጠራ የመጣው::

ስለዚህ ድርጅቱ ለሁላችንንም ሊያታግል የሚችል ፕሮግራም ይዞ የተነሳ ነበር:: በሂደት ፓርቲው ይህን ፕሮግራም ተከትሎ በጽናት መታገልና ይበልጥ እያሻሻለው የሚሄድ እድል ቢኖረውም ይህን ግን ሳይጠቀምበት ቀረ::

1966/1967 ዓ.ም በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ በጣም ብዙ ድርጊቶች የተፈፀመበት ወቅት ነበር:: ደርግ ወደ ሥልጣን መጣ:: ደርግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ የአርሶ አደሩን ትግል ለመግታት መሬት ከፌውዳሎች መንጠቅ የጀመሩ አርሶ አደሮችን አረፋችሁ ተቀመጡ፣ ፊውዳሎችን እንዳትነኳቸው ማለት ጀመረ:: ነገር ግን ደርግ የአርሶ አደሩን ትግልሊያቆመው አልቻለም:: አርሶ አደሩ በጉልበት መሬት መንጠቁን በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ በሰፊው ቀጠለ:: በዚህ የተነሳ የመሬት አዋጅ ለማወጅና ትግሉን ለማቀዝቀዝ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጠረ:: የመሬት አዋጅ ሲታወጅ ኢሕአፓ ላይ ትልቅ ፈተና መጣ::
Berekey simon

ኢሕአፓም የመሬት አዋጅ የአርሶ አደሩን ጥያቄ መልሶለታል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰ:: ነገር ግን “አርሶ አደሩ መሬት ቢያገኝም ዴሞክራሲን አላገኘም፣ መሬት ቢያገኝም ስልጣን አላገኘም፣ መሬት ቢያገኝም የብሔር ጥያቄው አልተመለሰትም ነበር:: እነዚህ ምክንያቶች ቢኖሩም ኢሕአፓ አርሶ አደሩ ለትግል የተመቸ አይደለም” ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ:: ስለዚህ ትኩረቱ ሁሉ በከተሞች ወደሚካሄድ ትግል አዘነበለ:: በከተሞች ደግሞ ደርግ የተከማቸ አቅም ይዞ የተቀመጠበት ሁኔታ ነበር:: ወታደሩ፣ የትራንስፖርት አቅሙ፣ የጦር መሣሪያው፣ የእዝ ሠንሰለቱ፣ የኮሙኒኬሽን መሳሪያው በሙሉ የተከማቸው ከተማ ላይ ነው::
ስለዚህ ኢሕአፓ በከተሞች የትጥቅ ትግል ደርግን እጥላለሁ ማለት ሲጀምር ያልተመጣጠነ ግጥሚያ ውስጥ መግባት እንደማይቀርለት የታወቀ ነበር:: የምትገጥመው ተቀናቃኝህ ሀይሉን በሚያከማችበት ቦታ ላይ ሂደህ የምትገጥም ከሆነ ከውድቀት በስተቀር ሌላ እድል የለህም:: የሽምቅ ውጊያ ህግ የሚለው የጠላትን/የተቀናቃኝህን/ ስስ ብልቶች እያየህ ማጥቃት አለብህ ነው:: ኢሕአፓ ግን የጠነከረውን ብልት፣ የጠነከረውን የደርግ አቅም መርጦ መፋለም ጀመረ:: ከዚህ በኋላ ብዙ ነገር ከእጁ እየወጣ እየተበላሸ ሄደ::
ኢሕአፓ በከተማ የትጥቅ ትግል ላይ ሲያተኩር፣ በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን እይዛለሁ ብሎ ሲያስብ በረሀ ላይ ያቋቋመውን ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ወደ መዘንጋት ሄደ:: በዚህ የተነሳ ለሰራዊቱ ብቁ አመራር ለመስጠት የሚያስችላውን እንቅስቃሴ ማካሄድ አቆመ:: ከዚያ በረሀ የነበረው ሀይልም እውነተኛ ተዋጊ ሀይል ሆኖ ሊገነባ አልቻለም:: ከዚህ ይልቅ እንደማቆያ ምናልባትም በከተማ ያለው ትግል ከተሳካ ያንን ደግፎ ኢሕአፓ የማታ ማታ መጠቀሚያ ሊያደርገው የሚችል ሠራዊት ከመሆን በዘለለ እውነተኛ ተዋጊ እንዲሆን ለማድረግ የተደረገ ትግል አልነበረም:: ይህ ሠራዊቱ ውስጥ የነበሩና ለትግል የተዘጋጁ ብዙ ወጣቶችን ሞራል በከፍተኛ ደረጃ የሚጐዳ ሆኖ ነበር::

ወጣቶቹ “የእንዋጋ” ጥያቄ ያቀረቡት ገና ከጠዋቱ ነበር:: በ1968 ዓ.ም ወደ ትግሉ ተቀላቅየ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ “ለምንድን ነው ወደ ጦርነት የማንሄደው? ለምንድን ነው የማታዋጉን” የሚል ጥያቄ እስከመነሳት ደርሶ ነበር:: 25 የማይማሉት የፀለምት ታጋዮች ይህን መሠል ጥያቄ ያቀረቡ ነበር:: ይህን ለመሰለው ታጋይ ግን ብቃት ያለው አመራር
አልተሰጠውም ነበር::

ይህ በሰራዊቱ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ በር ከፍቷል:: የከተማውን የትጥቅ ትግል ፋይዳ፣ ብስለት አስመልክቶ መጠየቅ ተጀመረ:: ኢሕአፓ ግን ለጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄ ያነሱ ታጋዮችን በአንጀኝነትና በፀረ ድርጅትነት እየፈረጀ ማሰር፣ መምታት ጀመረ:: የታጋዮች መታሰርና መመታት እንደገና ሌላ ጥያቄ መቀስቀስ ጀመረ:: ውስጠ ዴሞክራሲው ክፍተት እንዳለበትና ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር እንዳለ በፓርቲው አባላት ዘንድ ጥያቄ ሆኖ ተነሳ :: አልፎ ተርፎም ከሌሎች ብሔራዊ የትግል ድርጅቶች ጋር ውጊያ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ስለነበር ይህም ትክክል አይደለም “ለምንድን ነው ከትግል ድርጅቶች ጋር የምንዋጋው?” የሚል ጠንከር ያለ ጥያቄ በአባላቱ ዘንድ በስፋት መነሳት ጀመረ::

ስለዚህ ኢሕአፓ ጥሩ ጀምሮ፣ ሊሻሻል የሚችል ብዙ ነገር ነበረው:: ነገር ግን አመራሩ ይህንን በብቃት መምራት ባለመቻሉ ምክንያት ነገሮች ከእጁ እየወጡ ድርጅቱን በስኬትሳ ይ ሆ ን በውድቀት ጐዳና እንዲራመድ አድርጐታል:: ሌላ የፖለቲካ ድርጅት ከመመስረት ይልቅ ኢህአፓን አጠናክሮ መስቀጠል አይቻልም ነበር ወይ? ኢህአፓን አጠናክሮ እንደገና እንዲደራጅ ማድረግ አይቻልም ወይም ይቻላል ያከራክራል:: ለምን አልተሞከረም? ለሚለው ጥያቄ ግን መልሱ ሞክረናል ነው:: ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄው የመጀመሪያ አላማ አድርጐ የያዘው ኢሕአፓን ማቅናት ነበር::

ኢሕአፓ ብዙ መስዋዕት የተከፈለበት ድርጅት ነው:: ይህ ድርጅት ያሰባሰበው ቀላል የማይባል የሠው ሀይል ነው:: በኢትዮጵያ በመሀል ሀገር ከነበረው ወጣት ምርጥ የሚባለውን ሀይል አሰባስቦ ይታገል የነበረው ድርጅት ነው:: ስለዚህ ይህንን ሀይል ከማፋረስ ወይም በሌላ ከመተካት ይልቅ አስተካክሎ ወደ ተሻለ ብቃት ለመምራት የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር ኑሮ ተመራጭ ይሆን ነበር:: በመጀመሪያ የተደረገው ሙከራ ይሄ ነበር:: ይህ ሙከራ እንዲሳካ ለማድረግ ጥረት የተደረገው መሪዎችን በመቀየር ጭምር አይደለም:: ለምሳሌ ኢሕአፓ በ1972 ዓ.ም ሊካሄድ የታሰበው ጉባኤ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን፣ አመራሩም ተስተካክሎና ታርሞ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባናል ብለን ነበር:: አመራሩ እንዲስተካከል ለማድረግ ደግሞ የታጋዮቹ ወኪል የሆነ ኃይል በአመራሩ ውስጥ መግባት አለበት፣ ከታች አመራሩን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሠዎች ሁሉ ማስገባት አለብን የሚል ንቅናቄ ማካሄድጀምረን ነበር::

ስለዚህ ኢሕአፓን አስተካክሎ መቀጠልየመጀመሪያው ፍላጐት ነበር:: ነገር ግን የኢሕአፓ መሪዎች በነበራቸው ግትርነት ለዴሞክራሲያዊ ሀሣቦችና ጥያቄዎች በነበራቸው ጥላቻና ፍርሀት ምክንያት ሊሳካ አልቻለም:: ኢህአፓ ሀሣቡን ተቀብሎ ከማስተካከል ይልቅ ወደ ማሰር አመራ:: ልዩነቱ በቀላሉ እንዳይታረቅና በቀላሉ እንዳይጠገን የሚያደርግ ግፊት አደረጉ:: ይህ ግፊት በዋነኛነት ለታጋዮች ጥያቄዎች ቀና ምላሽ ባለመስጠት የሚገልጽ ነበር:: አንደኛው ችግር ይሄ ነው:: ሁለተኛው ተጨባጭ ችግር በለሳ፣ ጠለምት፣ ወልቃይት ጠገዴና አርማጭሆ በሚባሉ ሪጅኖች /ክልሎች/ ላይ የነበረ ነው:: እነዚህን ሪጅኖች/ ክልሎች/ እንደ አንድ አካል ማግኘት ከባድ ነበር::

ስለዚህ መጨረሻ ላይ እያዳንዱ ሪጅን/ክልል/ ለራሱ መቆም የጀመረበት ሁኔታ ተፈጠረ:: አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ ወልቃይት የነበሩት ወደ ሱዳን በቀላሉ ወጡ ወደ ኤርትራ ደርግም በብዛት የገቡበት፣ በለሳ ላይ የነበርነው ደግሞ ለመታገል ሞክረን ሁኔታው አስቸጋሪ ሲሆን ወደ ትግራይ መሄድ የመረጥንበት ሁኔታ ተፈጠረ::

ኢ ሕ አ ፓ ን ለ ማ ቅ ና ት ና አ ስ ተ ካ ክ ሎ ለ ማ ስ ቀ ጠ ል ጥ ረ ት ተ ደ ር ጓ ል : : ነገር ግን በ ኢ ህ አ ፓ አ መ ራ ር እ ም ቢ ታ ና በሁኔታዎች አስገዳጅነት የታሰበው ሊሳካ ባለመቻሉ አዲስ ድርጅት ወደ መመስረት አምርተናል:: ወደ ትግራይ የመሄዱ ሀሣብ እንዴት መጣ?

መጀመሪያ ወደ ትግራይ ከመሄዳችን በፊት 1971 ዓ.ም ህዳርና ታህሳስ አካባቢ ኢሕአፓና ህወኃት ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ዙር ጦርነት ወልቃይት አካባቢ ይጀምራሉ:: በፊት አካባቢ ጦርነት ሲጀመር በለሳ የነበረው ንቅናቄ አንድ የተጠናከረ ደረጃ ላይ ደርሷል:: በኢሕአፓ ላይም ሙሉ ግምገማ አድርጐ ኢሕአፓ ችግር ያለበት ድርጅት ነው ወደ ሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል:: ኢሕአፓ መስተካከል አለበት የሚል አቋምም ይዟል:: ይህን አቋም ይዞ የነበረው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ኢሕአፓን በመታገል ሂደት እያለ “ ጦርነት ውስጥ ግቡ” ተባልን::

ከብሔራዊ የትግል ድርጅቶች ጋር የሚካሄድ ጦርነት ትክክል አይደለም፤ አንደግፈውም፤ የበለሳው ንቅናቄም ለጦርነቱ አስተዋጽኦ አያደርግም እስከማለት ተደረሰ :: ያም ሆኖ ጦርነቱ ተካሄደና ኢሕአፓ ተሸነፈ:: በዚህ ሁኔታ እያለን ኢሕአፓ ውስጥ የነበረው ቀውስ እየተባባሰ መጣ:: ታጋዩ በብዙ ጉዳዮች ላይ ግራ ተጋባ:: የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ:: በዚህ ምክንያት ግማሹ ወደ ደርግ መሄድ ጀመረ:: ግማሹ በተናጠል ወደ ቤቱ ተመለሰ:: ግማሹ ወደ ሱዳን ተበተነ::

ይህ ሁኔታ እየጠነከረ ሲሄድ “ምን እናድርግ?” የሚል ጥያቄ አነሳን:: በለሳ ውስጥ ለመቆየት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጣ:: ደርግ ብዙ ሠራዊት መበተኑን ሲያይ ወታደራዊ ዘመቻዎቹን በተደጋጋሚና በቅርበት መፈፀም ጀመረ:: ሠራዊቱ መዋጋት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ፣ አርሶ አደሩ ደግሞ ደርግ የሀልይ ሚዛን ብልጫ እንደወሰደ መመልከት ሲጀምር ኢሕአፓንና ሠራዊቱን ገሸሽ የማድረግ አዝማሚያ እያሳየ መጣ:: ስለዚህ ሁኔታው አስቸጋሪ መሆን ጀመረ::

በዚህ ሁኔታ ንቅናቄው ከዚያ አካባቢ የመቆየት እድሉ ጠባብ ሆነ:: በዚህ ጊዜ “ወደ ትግራይ ብንሄድ ይሻላል” የሚል አቅጣጫ ማውጠንጠን ተጀመረ:: ከመከላከላችን ወደ አርማጭሆ እንሂድ የሚል ሀሣብም ተነስቶ ነበር::

ወደ አርማጭሆ የምንሄደው በደርግ ግዛት አቋርጠን ነው:: የታጠቀ ሠራዊት ይዘን፣ ደርግ የሚቆጣጠረውን ግዛት አቋርጠን ወደ አርማጭሆ መሄድ አደጋው ከፍተኛ ነው:: ሙሉ በሙሉ መጥፋትም ይመጣል:: አርሶ አደሩም የሀይል ሚዛን ብልጫውን ተመልክቶ ወደ ደርግ ያዘነበለበትና እኛን ጠቁሞ መሾሚያ ማድረግ የሚፈልግበት ጊዜ ነበር:: ስለዚህ ያኔ ነጭ መሬት/ነጻ መሬት/ በምንለው በኩል አልፈን መሄድን አንደ መልካም አማራጭ ወስደነው:: ለዚህ ደግሞ የተሻለው አማራጭ ትግራይ መሄድ ነው የሚል ነው:: ከህውሓት ጦርነት ገጥመን የነበረ ቢሆንም አሁን ወደሱ ብንሄድ ኢሕአፓ እንደሚነግረን ላይሆን ይቻላል:: እንደማንኛውም ታጋይ ድርጅት የትግል ፍላጐት ይኖረዋል:: ሲሆን አንድንደራጅ ይተባበረናል:: ካልሆነ ደግሞ ወደ ሱዳን ማለፊያ መንገድ ይሠጠናል:: ገብተን ተደራጅተን ተመለስን በአንዱ የአማራ አካባቢ እንደገና ትግል እንሞክራለን በሚል ሀሣብ ነው ወደ ትግራይ የሄድነው::

ሕወሓት ጋ ምን ጠበቃችሁ?

ትግራይ ስንሄድ ብዙ ነገር ነው ያገኘነው:: ብዙ ነገሮችን ነው የተመለከትነው:: ከሁሉ በፊት እኛ ከቆየንበት ከበለሳ አካባቢ የተለዩ ሁለት ትልልቅ ነገሮችን አግኝተናል:: አንደኛ የትግራይ ህዝብ ሁኔታ ነው:: ሁለተኛ የህውሓት ድርጅትና ሠራዊቱ ሁኔታ ነው:: እነዚህ ሁለቱ ትልልቅ ነገሮች ነበሩ:: በዚያን ወቅት የትግራይ ህዝብ በጣም ከፍተኛ የሆነ የ ት ግ ል መ ነ ሳ ሳ ት እንደነበረው ታዝበናል:: መ ሀ ል ሀገር ያለው ሁኔታ ትግሉ ተቀዛቅዟል:: ደርግ በቀይ ሽብር በወሰደው እርምጃ በጣም ብዙ ወጣቶች ተጨፍጭፈዋል:: የትግል ድርጅቶች ተበታትነዋል:: የህዝቡ የትግል መነሳሳትም ተቀዛቅዟል:: ከዚያ አልፎ ከባድ የሞራል ውድቅት ተከስቷል:: የደርግ መንግስት ባካሄደው ጭፍጨፋ ህዝቡ ከልክ በላይ ስለተቀጣ የተሸማቀቀበትና ግራ የተጋባባት ሁኔታ ነበር::

ትግራይ ላይ ሥንገባ ያየነው ሁኔታ ከዚህ ለየት ይላል:: ህዝቡ በህወሓት እየተመራ የተለያዩ ድሎችን እየተጐናፀፈ ነው:: የተራዘመ የገጠር ትጥቅ ትግል የሚባለው አቅጣጫና ስትራቴጂ በትክክል ተግባራዊ ተደርጐ ውጤት ማምጣት ጀምሯል:: ደርግም በትግራይ ተከታታይ ግዙፍ ዘመቻዎች ያካሄደ ቢሆንም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በጋራ ሆነው ባደረጉት ትግል በብቃት መክተው መልሰውታል:: በትግራይ ነጻ መሬቱ ሠፍቶ ህዝቡ ለሌላ አዲስ ትግል የሚነሳሳበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ስለዚህ በሄድንበት ሁሉ የትግል ወኔን ይበልጥ የሚቀሳቀስ፣ ከታገሉ ይህን የመሰለ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል የሚል አስተሳስብ እንድንይዝ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ መመልከት ቻልን::

ህወሓትም ኢሕአፓ ውስጥ እያለን አንስማው ከነበረው የተለየ ነው:: ስንገናኝ በትጥቅ ትግል
አካሄድና በገነቡት ሠራዊት ጥንካሬ በጣም የሚያስቀና ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር:: ገና ተፈላጊው የአንድነት ደረጃ ላይ አልደረሱም እንጂ ጠንካራ የሚባል ብቃት ያለው፣ በአግባቡ የተደራጀ፣ በጥሩ ሁኔታ የሚመራ ሠራዊት ገንብተው ነበር:: ተዋግቶ፣ ድል አድርጐ የራሱን ነፃ መሬት ገንብቶ መከላከል የሚችል ሀይል ፈጥረው ነበር:: ይህም ከታገልክ ጥሩ አመራር ማግኘት፣ እንዲህ አይነት የትግል ሠራዊት መገንባት ይቻላል የሚል ትምህርት እንድንወስድ በር የከፈተ ነበር::

በሌላ በኩል ህወሓት ጋ ስንገባ ያገኘነው ሌላው ነገር የአስተሳሰብ ብስለትናግልጽነት ነው:: እኛም ኢሕአፓ ውስጥ ሆነን ስናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች በህውሓት ደረጃ ተነሳተው ውይይት ተደርጐባቸው የተሻለ አቅጣጫና ግልጽነት ተይዞባቸዋል:: ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄው ትግራይ ሲገባ ከሞላ ጐደል በጣም የተመቸ ሁኔታ ገጥሞናል:: “መታገል አለብን!”
ብለን መወሰናችን ትክክል እንደነበር የሚያረጋግጥ፣ ወደ መደራጀት እንድናመራ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ
ነበር ::
ረጅም ጊዜ ወስደን በብዙ ነገሮች ላይ ከህወሐት ጋር ለመወያየትና ለመከራከር እንዲሁም በሚያስማሙን መስማማት፣ በሚያለያዩን ነገሮች መለያየት የምንችልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ማረጋገጥ የጀመርንበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

ወደ ትግራይ ከገባችሁበት ጊዜ ኢህዴን እስከ ተመሰረተበት ድረስ ያለው ወቅት ምን ይመስል ነበር?

ያ ስዓት ብዙ ነገሮች የነበሩበት ነው:: መሀል ሀገር ላይ የኃይል ሚዛኑ ተገለባብጧል:: የሀይል ብልጫ ሚዛኑን ደርግ ወስዷል:: በመሀል ሀገር ብቻ አይደለም:: ትግራይ ላይ በተነፃፃሪ የተሻለ ሁኔታ ቢፈጠርም 1969 እስከ 1975 ዓ.ም የቀይ ኮከብ ዘመቻ ድረስ በነበሩት ዓመታት ደርግ የበላይነቱን ያረጋገጠበት ዘመን ነበር::

በዚህ ዘመን መደራጀት አለብን ብለን ስንነሳ መጀመሪያ ያደረግነው ልክ ትግራይ እንደገባን የእርማት እንቅስቃሴ ብለን ራሳችን ንቅናቄው የፈፀማቸው ስህተቶች ካሉ እነዚህን ማረም ጀመርን:: አዲሱ ትግል ከኢሕአፓ ሥህተቶች በፀዳ መንገድ ብቻ ሣይሆን ከራሳችንም ሥህተቶች በፀዳ መንገድ መካሄድ አለበት የሚል አቋም ወሰደን ወደ እርማት እንቅስቃሴ አምርተናል::
የእርማት እንቅስቃሴው ተካሄደ:: የራሳችንን ድክመቶች ሙሉ በሙሉ ወስደን እናስተካክላለን አልን:: አዲሱ መተዳደሪያ ደንባችን ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለን ያንን በመተዳደሪያ ደንባችን ቀርጽነው:: ይህን ከጨረስን በኋላ የፖለቲካ ፕሮግራማችንን የመንደፍ ሀሣብ ይዘን ተንቀሳቀስን:: የፖለቲካ ፕሮግራማችን በራሳችን ለመንደፍ ጥናቶች ወደ ማድረግ ፣ መከራከርና ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መስማማት አለበት የሚል አቋም ያዝን::በዚህ ዝግጅት በአብዛኛው ከህወሓት ጋር የሚመሳሰል ግን በተወሰኑ ሁኔታዎች ደግሞ ከህወሓት የተለየና እኛ በምናምንባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የተዋቀረ ፕሮግራም ይዘን ወጣን:: ሦስተኛውና የመጨረሻው የመደራጀት እንቅስቃሴ ነው:: በዚያን ጊዜ በነበርንበት ሁኔታ ይብዛም ይነስም ፕሮግራም ማዘጋጀት፣ የአደረጃጀት መመሪያዎቻችንን ማጠቃለልና ለጉባኤ ዝግጅት የማድረግ ሥራ የምንሰራበት ወቅት ነበር::

የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ኢህዴን/ የተመሰረተበትን ቀን እንዴት ያስታውሱታል?

ለእኔ ትልቅ ቀን ነበር:: ብዙ ጊዜ በትግል በቆየሁባቸው አመታት ውስጥ አንዳንድ ለራሴ የያዝኳቸው ግቦች ተሳክተው ካየሁ በኋላ በትግሉ የሚያጋጥም መስዋእት ቢያጋጥምም ግድ የለኝም የምልባቸው ነገሮች ነበሩ:: ገና ኢሕአፓ እያልን ከኢሕአፓ ወጥተን የራሳችንን ድርጅት አቋቁመን ለትግል የምንነሳሳበትን ሁኔታ አይቼ ብሞት የሚል ሀሣብ ነበረኝ:: ስለዚህ ኢሕዴንን ለመመስረት የነበረው እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ተሳክቶ መጨረሻ ላይ አዲስ ድርጅት በምንፈጥርበት ጊዜ ሁላችንም የተስማን ስሜት በጣም ትልቅ እፎይታ የፈጠረ ነበር:: ድርጅት ምን ያህል አቅም እንደሆነ እናውቃለን::

ኢሕአፓ ትልቅ አቅም ይዞ ተነስቶ ያንን ያባከነ ድርጅት ነው:: እኛ ትንሽ ሆነን ተነስተን ወደ መደራጀት በማምራት ላይ የነበረን ነን:: ህውሓት እንዲህ ትንሽ ሆኖ ጀምሮ ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ ትግራይን ነፃ በማውጣት፣ ለኢትዮጰያ ህዝቦች ትግልም የበኩሉን ማበረከት የሚችልበት ብቃት እየተጐናፀፈ መሄድ የቻለ ድርጅት ነው:: ድርጅት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ምን ያህል ትልቅ የለውጥመሣሪያ እንደሆነ እንረዳ ነበር::

Source=http://www.ethiosun.com

 

 

Leave a Reply