በቅርቡ ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ስም ፤ ዋሽንግቶን ዲሲ ውስጥ ቪዥን ኢትዮጵያ የሚባል ድርጅትና ኢሳት/ግንቦት 7 ያዘጋጁት ፤ አንድ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር ። በአጠቃላይ ዋሽንግተን ዲሲንና የአበሻ ፖለቲካ ተዋንያኑን (ኤርትራን ጨምሮ ማለቴ ነው የሃበሻ ስል) የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ፤ ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ የነበሩትን በኢንተርኔት መስኮት ሲመለከት ፤ ዋሽንግቶን ውስጥ ስብሰባ ከተደረገ በፍፁም የማይቀሩ ግለሰቦችን ፤ ጋዜጠኞችን ፤ ጥቂት የግንቦት ሰባት ደጋፊዎችን እና የሻእቢያ የሰሜን አሜሪካ ተወካዮችንና ተራ የሻእቢያ አባላትን በቀላሉ በስም እየለዬ ፤ መጥራት ይችላል ።

ውድ አንባቢዎቼ ፤ በተለይ የዋሽንግተን ነዋሪ የሆናችሁ ፤ በረጅም ጊዜ ልምድ እንደምታውቁት ፤ ስብሰባ በተጠራበት ቦታ ሁሉ የማይቀሩና ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እጃቸውን እያወጡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ፤ ንግግር ወይም አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችን ታውቋቸዋላችሁ ብየ እገምታለሁ ። እነዚህ ሰዎች የአዘጋጆቹን ፍላጎት፤ በተለያየ መንገድ አስቀድመው ይረዳሉ ። ከዚያም ስብሰባው ላይ እሳተ-ነበልባል የሆነ ንግግር ያደርጋሉ ። የስብሰባውን አዳራሽ ፤ በተለይ የሰብሳቢዎቹ እጅ ፤ እስኪቃጠል ድረስም ያስጨበጭባሉ ። አዘጋጆቹን አስደስተው ፤ ራሳቸውም የሚፈልጉትን ትኩረትና የሚወዱትን ጭብጨባ ጠጥተው ፤ ደስ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ ። ታዲያ ለትግሉ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ፤ ከዚህ ከፍም ዝቅም አይልም ። እንደዚሁ ሁሉ ፤ ሆይ ሆይታ በሞቀበት ፤ ጭብጨባና ከንቱ ውዳሴ በበዛበት ቦታ ፤ ማንም ያዘጋጀው ማ ፤ ጉዳዩን ሳይመዝኑ ፤ አይምሮአቸውን ለተፈላጊው ጉዳይ አዘጋጅተው ፤ ታጥበውና ታጥነው የጠሯቸው የፖለቲካ መድረክ ላይ ሁሉ ፤ የፕሬዚዲየሙን ወንበር ለማሞቅ የሚገኙ ምሁራን ሰዎችንስ አስተውላችኋል ?

በዚህ የሻእቢያና የግንቦት ስብሰባ ላይ ፤ የውጪ እንግዶቹንና አንዳንድ ያልገባቸው ወገኖችን ትቼ ፤ በኔ በኩል ያስተዋልኩት እንዲህ አይነቶቹን ሰዎች ነው ። “ቪዥን ኢትዮጵያ” የሚባለው ቡድን ፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ፤ የቶሎ ቶሎ ስም ወጥቶለት ለሻእቢያ ተልእኮ የስጦታ መጠቅለያ ወረቀት ሆኖ የቀረበ ድርጅት ነው ። በግንቦትና በኢሳት ፊታውራሪነት ፤ ራሱን እንዲያቀርብ የተዘጋጀው ይህ ድርጅት ውስጥ ፤ በሃገርና በህዝብ ላይ የተሰራውን የሸፍጥ ተግባር ደግሞ ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አይኑን አፍጥጦ አይቶታል ። በተለይ ሻእቢያን ወክሎ የመጣው ግለ-ሰብ እዚያው እፊታቸው ፤ ሻቢያን ለመንካት ያሰበ ቢኖር “ራሽያን ሮሌት” እንደመጫወት ይቆጠራል ፤ እወቁት ብሎችኋል ። እደግመዋለሁ እያለም ያንኑ አባባሉን ደግሞ ነግሯችኋል ። ኢትዮጵያውያን ናችሁና ባዘጋጃችሁት መድረክ ላይ የሻእቢያን መልእክት ፤ አገጫችሁን ከፍ አድርጎ ይዞ ፤ የሚፈልገውን ሁሉ እንደኮሶ ግቷችሁ ሄዷል ። እናንተም የሻእቢያ ፕሮፓጋንዳና ጉድፍ ማስተላለፊያ ቱቦ ሆናችሁ አገልግላችኋል ። ህሊናቸሁ ምን እየተደረገባችሁ እንደሆነ ካልገለፀላችሁ ፤ ጊዜ ይገልፅላችዋል ። ከንቱ ውዳሴና ሙገሳ እንደ ጤዛ ብልጭ ብለው የሚጠፉ ነገሮች ናቸውና ።

“…….በመንፈሳዊው አለም ሰው የለ ፤ በፖለቲካው አለም ሰው የለ ፤ በሽምግልናው አለም ሰው የለ ፤ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የሰው ምድረ-በዳ ሆነች ? እያልኩ አወጣለሁ አወርዳለሁ…… እንደኔው የሚጨነቁ ሰዎችም ያሉ ይመስለኛል ።”
ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር አገር ነች ፤
ልጆቹዋ ግን ሰይጣን አድሮባቸዋል ።……
ኢትዮጵያ ግን የምታደላላቸው ልጆች የሏትም ፤
የሚያሳዝኗት ግን ሞልተዋል ፤……
ኢትዮጵያ የወላድ አገር ነች ፤
ግን የሰው ምድረ-በዳ ሆናለች ።

የላይኛው ቃልም ሆነ ቅኔ ፤ እዚያው ስብሰባው ላይ እንግዳ ከነበሩት መስፍን ወ/ማርያም ፤ የክህደት ቁልቁለት ከተሰኘው መፅሃፍ የወሰድኩት ነው ።

የዛሬው ርእሴ “ቪዥን ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት አይደለም ። ምንም ስላልሆነና ከስጦታ መጠቅለያ ወረቀትነት ባሻገር ህልውና ስለማይኖረው ። እዚያው እነሱ ከኢሳት ጋር የጠሩት ስብሰባ ላይ የጋበዟቸው እንግዳ ናቸው የዛሬው ዋናው ርእሴ ። ዶ/ር ካሳ ከበደ ። ሳስበው ውዬ ሳስበው ባድር ፤ የካሳ ከበደ የኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገትሮ ተከራካሪነት አልገባህ ብሎኝ ከረምኩ ።

ዶ/ር ካሳ እኮ የደርጉ ዘመን አንቱ የተባሉ ባለስልጣን ናቸው ። ስጋ ሜዳ በኋላ ላይ ታጠቅ ጦር ሰፈር የተባለውን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለማስገንባት በጊዜው የሃገሪቱ መሪ በነበሩት ፤ በኮለኔል መንግስቱ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰው ናቸው ። የሃገሪቱን አንድነት ከገንጣይና ከሶማሊያ ወራሪ ለመከላከል ፤ በዚሁ በታጠቅ ጦር ሰፈር 3 መቶ ሺህ የኢትዮጵያ የገበሬ ልጅ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶበታል ። ይህ የገበሬ ወታደር ከሶስት ወራት ስልጠና በኋላ ፤ በሰሜንም በምስራቅም ያለክፍያ የሐገሪቱን አንድነት ትጠብቃለህ ተብሎ ተማግዷል ። ለዚህ ለአንድነት የፈሰሰ ደም ፤ በተለይ ደግሞ ከሻእቢያ ጋር እየተዋጋ መስዋእትነት ለከፈለው ህዝባዊ ሚሊሺያ ፤ ካሳ ከበደ ፤ እንደ ደርግ ባለስልጣን ሃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል ። በሰሜን የተደረገው ጦርነት ደግሞ የተካሔደው ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ከመራው ፤ ከሻእቢያ ጦር ጋር ነው ። እንዴት ሆኖ ነው ዛሬ ካሳ ከበደ ፤ ለሻእቢያው ቁንጮ ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራካሪ ሆነው የተገኙት ?

ከዚህ ሌላ ፤ ካሳ ከበደ በተባበሩት መንግስታት ፅ/ቤት የዚያን ጊዜው መንግስት ፤ ማለትም የደርግ መንግስት የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ፤ አምባሳደር በመሆንም ሰርተዋል ። በጊዜው ኢትዮጵያን በመወከል ፤ የሐገራችንን በጎም ሆነ መልካም ገፅታ የመወከል አደራ ፤ በኢትዮጵያ እና በህዝቧ ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰው ናቸው ። (የደርግ ድንቁርና እንዳለ ሆኖ) በተሰጣቸው አገራዊ አደራ የተነሳም ፤ ላገለገሉት መንግስት መርሕ ቆመው መስራት ተገቢ ነበር ። የገንጣዮችን የነሻእቢያን ደባም ፤ አቅማቸው በፈቀደ በማክሸፍ ጥረት ላይ መንግስታቸውን ወክለው ሰርተዋል ብዬ እገምታለሁ ። ታዲያ እንዴት ተደርጎ ነው የዚያ መንግስት ፓርቲና የኢሠፓ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የውጪ ግንኙነት ሃላፊ ፤ ዛሬ ለገንጣዩ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገታሪ ሆነው የተገኙት ?

ወይስ ዶ/ር ካሳ ከበደ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ስርዓት ግፍና በደል ደርሶበታል ብለው አስበው ይሆን ? ከሆነስ የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃነት ፤ በኢሳኢያስ አፈወርቂ በኩል ላመጣው እችላለሁ ብለው ገምተው ነው ? ለኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገታሪ ለመሆን የቆረጡት ። እንዴትስ ተደርጎ ቢታሰብ ነው ፤ የገንጣዩ የሻእቢያ መሪ ኢሳኢያ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል አላማ የለውም ተብሎ በኢሳኢያስ አፈወርቂ ተነግሮ ፤ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ፤ በካሳ ከበደ በኩል የሚነገረን ።

በዚህም ብዬ በዚያ ባስበው ፤ ባወጣው ባወርደው ፤ ምክንያቱ በፍፁም አልመጣልህ አለኝ ። በነገራችን ላይ ፤ ካሳ ከበደ ፤ ከወንድምዎ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር በመሩት የመንግስት ስርዓት ውስጥ እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ ደልቶት አልኖረም ። ወንድምዎ ስል ግን ፤ ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታማ የነበረውና በኋላ ላይ “የአጥፍቶ መጥፋት” ደራሲ ፤ የፃፈውን መፅሐፍ ተመርኩዤ እንዳልሆነ በቅድሚያ ይታወቅልኝ ። ዛሬ እትሙን ባላስታውሰውም እርስዎ ራስዎ እዚህ አሜሪካ ከመጡ በኋላ በጦቢያ መፅሄት ላይ ፤ አንድ ቃለ መጠይቅ አድርገው ማንበቤ ግን ትዝ ይለኛል ። በዚያ ቃለ መጠይቅ ላይ ኮለኔል መንግስቱ በስጋ ባይወለዱኝም የርእዮተ-አለም ወንድሜ ናቸው ማለትዎን ግን በደንብ አስታውሳለሁና ነው ።

ስለዚህ ካሳ ከበደ ሆይ ፤ ሰው ምክንያታዊ ነውና እኔም ካሳ ከበደና ኢሳኢያስ አፈወርቂ ምን አገናኛቸው ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ ወደኋላ ተጓዝኩና ፍተሻ ገባሁ ። አቧራ ከለበሱት መረጃዎቼ ውስጥ አንድ ነገር አገኘሁና መልሱ ይህ ይሆን እንዴ ? ስል ጠረጠርኩ ። ጥርጣሬየን እርስዎ ደህና አድርገው ያውቁታል ። ከአንባቢዎቼ ጋር ግን ልካፈለው ወደድኩ ። ምንም ቢሆን ፤ በአንድ ዘመን ላይ የትከናወነ ታሪክ ፤ ምናልባት በጊዜ ምክንያት ይደበዝዝ ይሆናል እንጂ ፤ ጨርሶ ሊጠፋ ግን አይችልም ።

ዶ/ር ካሳ የዛሬን አይድርገውና በስራ ምክንያትም ሆነ በግል በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ፤ መጡ መጡ ተብለው ፤ ተፈርተው ፤ ታፍረው ተከብረው ሁሉም ሰው ሽር ጉድ ይልልዎ እንደነበር አይዘነጋዎትም ። መጨርሻ ላይ ግን ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንዴት አድርገው ነው በዚያው በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ጥለዋቸው የወጡት ?

ቃሬዛውና የሂልተን ሆቴል ብርድ ልብስ !

ከዛሬ ሃያ አራት አመታት በፊት የሆነ ታሪክ ነው ። የመጨረሻውን “ኦፕሬሽን ሰለሞን ” የተሰኘውን ተልእኮ በመሪነት ይወጣ ዘንድ ፤ የእስራኤል መንግስት ፤ ኡሪ ሊብራኒን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ፤ ልዩ ወኪል በማድረግ ሾሞታል ።

“ኦፕሬሽን ሰለሞን” የመጨረሻው ሰአት ላይ ከመድረሱ ሶስት አመታት በፊት ፤ ይላል ስቴፓን ስፔክል ፤ የአሜሪካ አይሁዶች ማሕበር ሰዎች ፤ ጌሊ ኩሊንክና ናትሻፕረን ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሳ ከበደን አግኝተው ሲወያዩ “አንተ ሕልውናህ ከዚህ ከምትሰራው ተልእኮ ጋር የተያያዘ ነው ። የተፈለገው ግብ ላይ እንድንደርስ ከተባበርከን ፤ በአስፈላጊው ሰአት ልንደርስልህ እንደምንችል ፤ እርግጠኛ ሁን ። ብለውት ነበር ።

የእስራኤሉ “ኦፕሬሽን ሰለሞን” ሹመኛም ፤ ስለ ካሳ ከበደ ማንነት የራሱን ግምት የሰጠው እንዲህ በማለት ነበር ። “ገና መጀመሪያ ላይ ከካሳ ጋር ፤ እንደተገናኘን ለኔ የሚስማማኝ የራሴ ሰው እንደሆነ አወቅኩኝ ።………..ለዚህ አለም ኑሮ የተስተካከለ ስብእና ያለው ፤ ነገር ግን ንቁና ተጠራጣሪ ቀበሮ ፤ ጨካኝና ግትር መሆኑን ካላወቅህ ይጎዳሃል።” ነበር ያለው ፤ ይላል መፅሐፉ ።

ኡሪ ሉብራኒ የሰጠው አስተያየት እንዳለ ይቀመጥና ፤ ፈላሻዎቹን ከኢትዮጵያ የማውጣቱ ተግባር “በኦፕሬሽን ሰለሞን ዘመቻ” እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት ፤ የመጨርሻው ሰአት ላይ ፤ ኡሪ ሉብራኒ ሁለት መኪናዎች አስከትሎ ፤ የመጨረሻዎቹን ተጓዦች እያሳፈረ የነበረው ሲ 130 ሄርኩለስ አውሮፕላን ውስጥ ሁለት በቃሬዛ ላይ የተኙ ፤ ህሙማንን ለማሳፈር ዝግጅቱን አጠናቀቀ ።እነዚህ በሽተኛ ተጓዦች ከሂልተህ ሆቴል በተወሰደ ብርድ ልብስ ተጠቅልለዋል ።

ህሙማኑ ሲጫኑ ያዩ የሞሳድ አባላት ኡሪ ሉብራኒን ፤ “እነዚህ ሰዎች እንዲህ በጠና ከታመሙ ለምን እናጓጉዛቸዋለን ? ከህመማቸው ሲያገግሙ ቢመጡ አይሻልም ? ብለው ይጠይቁታል ። ማን ያውቃል ፤ ከሞት ተርፈው ፤ እንነሱም በስትሬቸር ወደ እስራኤል ገባን ፤ ብለው ለማውራት ያስችላቸው ብዬ ነው የፈቀድኩት ፤ ሲል ተናገረ ።……….እነዚህ ሁለቱ ከሂልተን ሆቴል በቃሬዛ ብርድ ልብስ ለብሰው የተጓዙት ህሙማን ከኢትዮጵያ ፀጥታ ሃይሎች እይታ እንዲያመልጡ ፤ በስራኤል የፀጥታ ሰራተኞች በጥንቃቄ በተቀነባባረ ዘዴ ፤ ወደአውሮፕላኑ የተሳፈሩት ሰዎች ናቸው ። ኡሪ ሉብራኒ አውሮፕላኑ ህሙማኑን እንደያዘ በፉሪ ተራራ አናት ላይ እያዘገመ ፤ ከአይናቸው እስኪሰወር ሲያዩ ከቆዩ በኋላ አብረውት ለነበሩት ባልደረቦቹ “ ካሳ ከበደ እንደፈለገው በቃሬዛ (ስትሬቸር) ላይ እንደተኛ ወደ እስራኤል ሊገባ ነው” አለ ፤ እየሳቀ ይላል ፤ መፅሐፉ ። እነዚህ በሂልተን ሆቴል ብርድ ልብስ ተጠቅልለው የነበሩት ህሙማን ፤ ካሳ ከበደና የኢትዮጵያ ደህንነት ም/ሚንስትሩ መርሻ ቀፀላ ነበሩ ።

ዶ/ር ካሳ ከበደ ስንትና ስንት ጊዜ በክብርና በአጃቢ ከተሸኙበት የቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ፤ እንዲህ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው ነው ከኢትዮጵያ የወጡት ። በሰሜን አቅጣጫ ፤ በእስራኤሎቹ ሄርኩለስ አውሮፕላን ወደ ቴልአቪቭ ሲነጉዱ ፤ ለአንድ ሳምንት ብቻ የቆየው የሃገሪቱ ጊዜያዊ መንግስት አባላት ለስብሰባ ቤተ-መንግስቱ ካፊቴርያ ውስጥ ካሳ ከበደን ፤ ለስብሰባ እየጠበቋቸው ነበር ። ይህ ከመሁኑ ከአንድ ሳምንት በፊትም ፤ ኮለኔል መንግስቱ በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ፤ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ዚምቧቡዌ ሸምጥጠው ነበር ።

እዚህ ላይ የፍቅሬ ቶለሳ አንድ ቅኝት ትዝ አለኝ ።

“ሞኝ ዋርካ ሊተክል
ግንዱን ተሸክሞ ያምጣል።
ብልጥ ዋርካውን ኪሱ ከቶ
ፈጠን ፤ ቀልጠፍ ብሎ ይራመዳል ።”

እንግዲህ ፤ ከላይ ያቀረብኳቸውን መረጃዎች ያገኘሁዋቸው ስቴፓን ስፔክል ከተባለ ደራሲ መፅሓፍ ላይ ነው ። “ ኦፕሬሽን ሰለሞን ያልተነገሩ ምስጢሮች” ይላል የመፅሐፉ ርእስ ። ደራሲው ስቴፓን ስፔክል ፤ በዚህ መፅሃፉ ላይ ፤ ከፈላሻዎቹ ጋር በተያያዘ የነበሩትን ጉዳዮች ፤ ከዋሽንግተን እስከሞስኮ ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ቴልአቪቭ ፤ የነማን እጅ እንዳለበትና እነማን ምን ሚና እንደነበራቸው በሚገባ ገልፆበታል ። ስለዚህም በአሜሪካዊው ኸርማን ኮህንና በእስራኤላዊው ኡሪ ሉብራኒ መካከል በሚደረጉ የንግግር ልውውጦች ፤ ካሳ ከበደን “ዘ ብሮከር ፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ “ኮካኮላ” የሚል የሚስጥር ስምም ሰጥተዋቸው ነበር ። ይህ ቅፅል ስም የወጣላቸው ፤ ካሳ ከበደ ፈላሻዎቹን ከማስለቀቅ ጋር ባላቸው ሚና ፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ በጥቁረታቸው የተነሳ ከኮካኮላ ቀለም ጋር አያይዘውት ይሆናል ብየ እገምታለሁ ። የፈላሻዎቹ ጉዳይ ፤ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ሻሚር ፤ እስከ ከፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ የደረሰ ጉዳይም ነበር ።

“አሜሪካውያኑም ሆኑ እስራኤሎቹ ፤የካሳ ከበደ መፃኢ እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅና ለጉዳት እንዲጋለጥ አይፈልጉም ። ቦብ ፍሬዘር በጉዳዩ ላይ ሲናገር ‘የኋላ ኋላ የካሳ ከበደ ማረፊያው የተደላደለና ከላባ የተሰራ ምቹ ፍራሽ እንዲሆን ለማድረግ ዝግጁ ነን ብሏል ።’

በጉዳዩ ዙሪያ በአዲስ አበባ ፤ በዋሽንግቶንም ሆነ በቴል አቪቭ ሁሉም የየራሱን የካርታ ጨዋታ መቀመር ይዟል ። የዛሬው ርእሴ መሪ ተዋናይ ዶ/ር ካሳ ከበደም የራሳቸውን ጆከር ካርታ መዝዘዋል ።

ደላላው የጠየቀው ክፍያ ስንት ነው?

ለኢትዮጵያ መንግስት የሚከፈለውን ገንዘብ ካሳ ከበደ ሲደራደሩ ፤ ለራሳቸውም የሚገባውን ድርሻ እንዴት እንዳስቀመጡ ፤ ስቴፓን ስፔክል እንዲህ ሲል ዘግቦታል ።

“አርብ እለት ይላል “ኦፕሬሽን ሰለሞን ያልተነገረው ሚስጥር’ መፅሃፍ ደራሲ ፤ አርብ እለት ፤ ከኡሪ ሉብራኒ ጋር ተገናኝቶ ፤ በገንዘቡ መጠን ዙሪያ የጀመረውን ውይይት በመቀጠል ፤ ፈላሻዎቹን በአየር ትራንስፖርት ለማጓጓዝ ፤ የሚያስፈልገውን ዋጋ በማውጣት በአጠቃላይ 60 ሚሊዎን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግስት እንደፋይናንስ ድጋፍ እንዲከፈልና ለራሱም የልፋቱ ዋጋ እንዲታከልለት ካሳ ከበደ ጥያቄ አቀረበ ።” ይላል ።

አዎ ፤ የካሳ ከበደ ጆከር ካርታ ፤ የልፋታቸውን ዋጋ ከእስራኤላውያኑ መጠየቅ ነበር ። ከአመታት በፊት ለሌላ ተልእኮ ወደአሜሪካ ጎራ ብለው የነበሩት ካሳ ከበደ “American “Association for Ethiopian Jews” ከሚባል ድርጅት ጋር ግንኑነት አድርገው ፤ ለልፋታቸው ዋጋ ጠይቀው ፤ ቃል ተገብቶላቸው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ፤ እንደ እስቴፓን ስፔክል መፅሃፍ ። ለመሆኑ ካሳ ከበደ ፈላሻ የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ፤ የልፋታቸው ዋጋ ስንት ነበር ?

መፅሐፉ የገንዘቡን መጠን ፍንጭ ሲሰጥ …….. “የአይሁድ አጀንሲው ፕሬዚደንትም ሆኑ ገንዘብ ያዡ ፤ የቀረበውን የክፍያ መጠን ግዙፍነት ቢሰሙ ፤ ብዙ የተገፋበትን ጥረት በድንጋጤ ፤ ወደ ቀድሞው ስፍራው ሊመልሱት ይችላሉ ።” ካለ በኋላ ፤ በመቀጠል ፤ “በተለይ ካሳ ከበደ ጉዳዩን እንዲያቀላጠፍና እንዲያሳካ ላደረገበት $3.4 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ለመክፈል እንደተስማሙ ቢሰሙ ፤ በጉዳዩ ላይ የሚያደርጉት መንቀርፈፍና የሚፈጥሩት ማነቆ ፤ ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት ፤ ለጊዜው ዩሪ ሊብራኒ ፤ በጉዳዩ ላይ ከነሱ ጋር አለመነጋገርን መረጠ” ይላል ።

በመጨረሻም ! መርጃዎቼን ካገኝሁበት ከስቴፓን ስፔክል መፅሐፍ ላይ የሚቀጥለውን ርእስ ልዋስ ነው ።

ካሳ ከበደ “የመክፈቻ ቁልፍ” መሆኑ አብቅቷል

ዶ/ር ካሳ ከበደ ፤
1ኛ) የኢትዮጵያን ህዝብ ፤ በቀውጢው ሰአት ፤ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት እርስዎ ፤ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው ፤ ሜዳ ላይ ጥለውት ነው እኮ እንደ ኮለኔል መንግስቱ የፈረጠጡት ።
2ኛ) ከስጋ ሜዳው ማሰልጠኛ ወጥተው በኤርትራ በረሃና ተራሮች ላይ ፤ የትም ወድቀው የቀሩት ኢትዮጵያውያን የገበሬ ልጆች ደም እኮ ፤ እስካሁን ድረስ አልደረቀም ።
3ኛ) ፈላሻዎቹን ኢትዮጵያውያን ወደሌላ አገር ለማስተላለፍ ፤ የልፋቴ ዋጋ ይከፈለኝ ብለው ዋጋ የጠየቁ ሰው ነዎት እንደ መፅሃፉ መረጃ ።
አሁን ምን ተገኝቶ ነው ኢሳኢያስ አፈወርቂ በኔ ይሁንብህ ካሳ ! እኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እቅድ የለኝም ብሎ ለእርስዎ የሚነግርዎ ? እሺ ፤ እርስዎ እንዳሉት ፤ ነገረዎ ብለን እንውሰድልዎ ። ከስቴፓን ስፔክል መረጃ ተነስተን ፤ ያለፉትን ሁኔታዎች ሁሉ ስንገመግም ፤ እርስዎ ዛሬ ማን ስለሆኑ ነው የእርስዎን ቃል የምናምነው ? ወይስ ገንጣዩ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ፤ ለእርስዎ ከነገረዎት ቃል ጀርባ ፤ እንደ መጨረሻዋ ሰአት ሁሉ ፤ አንድ የተደበቀ ነገር አለ ?

ዶ/ር ካሳ ከበደ ፤ መቼም ኢሳኢያስ አፈወርቂ ገንዘብ ከፍሎዎታል ብዬም አልጠረጥርም ፤ ለራሱም በአረቦች ድጎማ የቆመ ፤ መናጢ ድኻ መንግስት ነውና ። ኢሳኢያስን በከንቱ ውዳሴ መደለል ፈልገው ከሆነ ደግሞ ፤ እሱ መንግስቱ ኃ/ማርያም አይደለምና አይሸነግሉትም ። እርሱ ራሱ ከልጅነቱ ጀምሮ በዚህ ተግባር ጥርሱን ነቅሎ አድጎበታል ።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ፤ ዶ/ር ካሳ ከበደ የእርስዎ መክፈቻ ቁልፍነት አክትሟል ። የሚያመጡት ለውጥም የለም ። እውነትም ይሁን ሐሰት የተናገሩት ሁሉ የሚደመጥበት ፤ ያዘዙት ሁሉ የሚፈፀምበት ፤ የረገጡት መሬት የሚንቀጠቀጥበት ፤ ዘመን “Gone with the wind” ። የኮለኔል መንግስቱ ፀኃይ የጠለቀች ጊዜ የርስዎም አብራ ጠልቃለች ።

በተረፈ ቸር ይግጠመን እላለሁ ።
በዚህ አጋጣሚም ፤ ለነፃነት ዘለቀ ሰላምታዬን ያቅርቡልኝ አደራ ።

በፅሁፉ ላይ አስተያየትም ሆነ ፤ ትችት ካላችሁ ፤ እነሆ ኢሜል አድራሻዬ anbesawyibra@gmasil.com .

ላስ ቬጋስ ኒቫዳ
ኖቬምበር 22/ 2015

Source  = Ethiopian Media Forum

 

 

Leave a Reply