ኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከጓንግዙ ቻይና ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ የነበረ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ውስጥ የተሳፈረ መንገደኛ፣ በስካር መንፈስ ሁከት በመፍጠሩ በመንገደኞች ርብርብ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡

የበረራ ቁጥር ኢቲ607 ከ300 በላይ መንገደኞች አሳፍሮ ከጓንግዙ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የተነሳው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነበር፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ከበረረ በኋላ በበረራ አስተናጋጆች አማካይነት ለመንገደኞች እራት ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ አብዛኛዎቹ መንገደኞች አሸልበው ነበር፡፡

በአውሮፕላኑ የተሳፈሩ መንገደኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከእንቅልፋቸው የነቁት በሰሙት ጩኸት ምክንያት ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ክፍል የነበሩ የበረራ አስተናጋጆች እየተጯጯሁ ወደ ቢዝነስ ክፍል ሲሮጡ መመልከታቸውን መንገደኞች ተናግረዋል፡፡ ከእንቅልፋቸው ተደናግጠው የተነሱ የተወሰኑ መንገደኞች የበረራ አስተናጋጆቹን ተከትለው ሮጠዋል፡፡

‹‹የበረራ አስተናጋጆቹ ሊገለን ነው›› እያሉ እየሮጡ ወደ ቢዝነስ ክፍል መምጣታቸውን የገለጹት ተሳፋሪዎች፣ ዕድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ የሚገመት ናይጄሪያዊ መንገደኛ በስካር መንፈስ ተገፋፍቶ የበረራ አስተናጋጆችን ለመደብደብ ሲያባርር መመልከታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህን ወቅት በቢዝነስ ክፍል ውስጥ የተሳፈሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት፣ በቢዝነስ ክፍል መግቢያ ላይ ጠብቀው ከሁከት ቀስቃሹ ናይጄሪያዊ ጋር ግብግብ ፈጥረዋል፡፡ ናይጄሪያዊው ግዙፍ ቢሆንም ኢትዮጵያዊው ባለሀብት እንደምንም ብለው መተናነቃቸውን ገልጸው፣ ሌሎች ናይጄሪያዊያን መንገደኞች ባደረጉላቸው እገዛ ግለሰቡን ከወለል ላይ ሊጥሉት ችለዋል፡፡ መንገደኞቹ ነውጠኛውን ተሳፋሪ በደረቱ በማስተኛት እጁን የኋሊት አስረውታል፡፡ ግለሰቡ መጠጥ መጠጥ ይሸት እንደነበር መንገደኞች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር በላከው ማብራሪያ፣ ግለሰቡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የአልኮል መጠጥ እንዳልቀረበለት ገልጿል፡፡ ለመንገደኛው የቀረበለት ለስላሳ መጠጥና ምግብ ብቻ እንደሆነ የጠቆመው አየር መንገዱ ግለሰቡ ግን ሰክሮ እንደነበር ይታመናል ብሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው መንገደኞች ግለሰቡ አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ በፊት፣ የአልኮል መጠጥ በብዛት ሳይወስድ እንዳልቀረ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ነውጠኛው ግለሰብ በሌሎች ተሳፋሪዎችና በአውሮፕላኑ ላይ ጉዳት ሳያደርስ፣ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር በመተባበር ሁኔታውን መቆጣጠራቸውን አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ አውሮፕላኑ ለሰባት ሰዓታት ያህል በመብረር ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሰላም አርፏል፡፡ መንገደኞቹና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ግለሰቡን ለኤርፖርት ደኅንነት ሠራተኞች አስረክበዋል፡፡ ግለሰቡ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ፣ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደበት መሆኑ ታውቋል፡፡

ከግለሰቡ ጋር ግብግብ የፈጠሩት ተሳፋሪዎች ለወደፊቱ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጠር በግለሰቡ ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት ሊጣል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹የፖሊስን ሪፖርት ተመልክተን በቀጣይ መደረግ ስላለበት ጉዳይ እንመክራለን፤›› ያለው አየር መንገዱ፣ የፖሊስ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በግለሰቡ ላይ የወንጀል ክስ ይመሠረታል የሚል እምነት እንዳለው አስታውቋል፡፡

The Reporter

Leave a Reply