እኛም ካንተ፥ እኛም ወዳንተ ተመላሾች ነን!
የሰሜን አሜሪካ ኢስላማዊ ተቋማትን በመመስረት የመንፈስ አባት በመሆን ለአያሌ አመታት አግልግሎት የሰጡት አባታችን ሙፍቲ ሙሐመድ ሲራጅ አል አኒይ በመጨረሻም የ አሏህን ጥሪ ተቀብለው አረፉ። ሳዲቅ አህመድ በወርሃ ሜይ/2008 ከርሳቸዉ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። አጠር ባለ መልኩ የተዘጋጀዉን ቃለ መጠይቅ ከታች ያንብቡ።ኢና ሊላሒ ወኢና ኢለይሒ ራጂኡን እኛም ካንተ፥ እኛም ወዳንተ ተመላሾች ነን።
ሶላተል ጀናዛ (ለሙታን የሚደረግ ጸሎት) የሚከናወነው በነገዉ እለት ዳረል ሒጅራ መስጊድ ዉስጥ ከሁለተኛዉ የጁመዓ (የአርብ) ሶላት በሗላ ነዉ። አድራሻ: 3159 Row St, Falls Church, VA 22044
የቀብር ቦታ:National Memorial Park
7482 Lee Hwy, Falls Church, VA 22042
ቆይታ ከሼህ ሙሐመድ ሲራጅ ሷልህ ጋር
እንደ ከዋክብት የደመቁ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መንገድን አመላካች ብርሃን የሆኑ አገርንና ህዝብን ያቀኑ ህይወታቸውን በመማርና በማስተማር ሂደት ውስጥ ያሳለፉ አያሌ ኡለሞች (የሐይማኖት-ሊቃዉንት) በምድረ ሐበሻ መፈጠራቸው አሌ አይባልም።
ለዚህ ሰናይ ምግባር እማኝ ይሆን ዘንድ ፈርስት ሂጅራን ብሎም በድርን (የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ድርጅቶች) በመመስረት የመንፈስ አባት ከሆኑት ከልጅነት እስከ አረጋዊነት ህዝብን እና አገርን ካገለገሉት ሼህ ሙሐመድ ጋር አጭር ቆይታ አድርገን አንኳር የህይወት ተሞክሮአቸውን ጠየቅናቸው።መርሐባ በማለት የሚከተለውን አጫወቱን፦
ሳዲቅ፡በቅድሚያ የቤተሰብዎን ታሪክ ቢነግሩን?
ሼክ ሙሀመድ ሲራጅ: ቤታችን በይተል-ኢልም (የእውቀት ቤት) ነበር። ዓሊም ከነበሩት አባቴ ነው ብዙውን የተማርኩት። ሃብትም ነበራቸው። ብዙ የቀንድ ከብትና ግመሎች ነበሩን። አባታችን ብዙ ደረሳወችን (የሀይማኖት ተማሪዎችን) ይቀልቡ ነበር።
ሳዲቅ፡ ዒልሙ (ሐይማኖታዊ ትምርት) የጀመረው ከርሶ አባት ብቻ ነው ወይስ አያት-ቅድመ-አያቶችዎም ዓሊም ነበሩ?
ሼክ ሙሀመድ፡ የአባቴ አባት ሳይሆን አያታቸው
አሊም ነበሩ የአባቴ አባትም ቢሆኑ ሙእሚንና ፈጣሪን የሚፈሩ ነበሩ።
ሳዲቅ፡ የት ነው የተወለዱት?
ሼክ ሙሃመድ፡ የተወለድኩት ራያ ነው አውራጃው ማይጨው ራያ አዘቦ ሲሆን ወረዳውም ሙኸኒ ይባላል።
ሳዲቅ፡ መቼ ተወለዱ?
ሼክ ሙሃመድ፡ የተወለድኩት ጃንዋሪ 15/1930 እንደ አሮጳውያኑ አቆጣጠር ነው።
ሳዲቅ፡የመጀመሪያ ልጅ ነዎት? እህትና ወንድም ነበሮትን?
ሼክ ሙሃመድ፡ የአባቴ የመጀመሪያ ልጃቸው አብደላህ ይባል ነበር። እኔ ሁለተኛ ልጅ ነኝ። ከኔ በኋላ አሊ፤ ኢብራሂም፤ሙሃመድ፤ጁሃር እና ሃሺም የሚባሉ ወንድሞች ነበሩኝ በህይወት ያለው አሊ ብቻ ነው።
ሳዲቅ፡ ከርሶ ሌላ በዒልም ውስጥ የገባ ወንድም ነበሮት?
ሼክ ሙሃመድ፡ቁርዓን የቀሩ ቢሆን እንጂ ዒልም እምብዛም የገቡ አልነበሩም።
ሳዲቅ፡ እድገትዎ የት ነበር? ዒልሙን የት በመሄድ አካበቱት?
ሼክ ሙሃመድ፡ ቁርዓንን ከአባቴ ራያ ተምሬአለሁ ወደ ደቡብ ወሎ እና ወደ የመን በመሄድም ተምሬAለሁ።
ሳዲቅ፡ ወደ የመን ሲሄዱ ስንት ዓመት ይሆኖት ነበር? የመንንስ እንዴት አገኟት? የቋንቋስ ችግር ገጥሞት ነበርን?
ሼክ ሙሃመድ፡ ሃያ አራት ወይም ሃያ አምስት ዓመት ይሆነኝ ነበር የየመን ሰዎች በጣም ጥሩዎች ነበሩ ተግባቢና ሰውን የሚረዱ ነበሩ በስራ ላይ ትጉህ ከመሆናቸው ሌላ በጣም የተለየ ጥሩ ፀባይ ያላቸው ነበሩ። የቋንቋ ችግር አልነበረ ብኝም ገና አገሬ ሳለሁ አረብኛን አውቅ ነበርና።
ሳዲቅ፡ ከየመንስ ሲመለሱ ወዴት ሔዱ?
ሼክ ሙሃመድ፡ አባቴ አረፉ ልጆቻቸውን ትተው ሄዱ ወንድሞቼን ማሳደግና መቆጣጠር ስለነበረብኝ ወደ ስራ ዓለም ገባሁ። እርሻ እና ንግድን መከታተል ጀመርኩ።በከብት እርባታችን ውስጥ እስከ ሶስት መቶ የሚደርሱ ከብቶች ነበሩን። የልጆቹ እድሜ እስኪፀና ድረስ ለሰባት መታት መቆጣጠር ነበረብኝ።
ሳዲቅ፡ የቤተሰብን ሀላፊነት ከመወጣት ባሻገር ምን ያደርጉ ነበር?አ
ሼክ ሙሃመድ፡ አስተምርም ነበር ቢሆንም ከኔ በላይ ዒልምየነበራቸው ዓሊሞች በአከባቢያችን ስለነበሩ እማርም ነበር።
ሳዲቅ፡ወንድሞቾ ካደጉ በኋላ የነበረው ህይወቶ እንዴት ነበር?
ሼክ ሙሃመድ፡ የአገር ምርጫ ስለመጣ በአከባቢው ህብረተሰብ ለፓርላማ ተመርጬ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1954 ወደ አዲስ አበባ ሔድኩኝ።
ሳዲቅ፡የፓርላማ ህይወቶ እንዴት ነበር?
ሼክ ሙሃመድ፡አላህ አጅሩን ይቁጠርልን እንጂ ግዜው በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንዳንዶቹ ደካሞች ነበሩ ፓርላማ የመጡት በባላባትነት እንጂ በእውቀት ባለመሆኑ፤ የሆነው ቢሆንም አላህ ከኛ ጋር ነበር። ቁርዓን በሬዲዮ እንዲቀራና ጁመዓን ለመስገድ እንዲፈቀድልን ጥያቄ ለንጉሱ አመራር ብናቀርብም ጁመዓ ከጉባዔ ወጥተን እንድንሰግድ፤በሮመዳን መንዙማና ዱዓ ከፉጡር በኋላ እንዲተላለፍ ተፈቀ ደልን። ከፓርላማው ስራም ጎን ለጎን የህግ ትምህርት ጀመርኩ በመጀመሪያ ሰርተፊኬት አግኝቼ በመቀጠልም በዲፕሎማ ለመመረቅ በቃሁ።
ሳዲቅ፡ ከዚያስ ፓርላማ ማገልገሉን ቀጠሉ ወይስ ወደ ዒልሙ ተመለሱ?
ሼክ ሙሃመድ፡ ወደ ፓርላማ አልተመለስኩም የአምባሳደርነት ሹመት Aግኝቼ ወደ የመን ሄድኩኝ።
ሳዲቅ፡ እንዴት አምባሳደር እንደተደረጉ ያው ቃሉ? ሼክ ሙሃመድ፡ እኔ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም አንድ ቀን አንዋር መስጊድ ተሰባስበን የሀጅ ኮሚቴን እያቋቋምን ሳለን ከቤተ-መንግስት የተላከ ሻምበል እበርላይ ቆሞ ጠራኝና ከቤተ- መንግስት እንደምፈለግ ነግሮኝ በመኪናው ይዞኝ ሄደ። እንደ እኔ የተጠሩ አምስትሰዎች ነበሩ ሁላችንም ለምን ይሆን የተጠራነው ብለን መጨነቅ ጀመርን የንጉሱ ተላላኪ መጥቶ አይዞአችሁ የተጠራችሁት ለደግ ነገር ነው ብሎ አጽናናን ከዚያ አንድ በአንድ እየተጠራን ማዕረግ ተሰጠን።
ሳዲቅ፡የመን በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ ሁለቱን አገሮች በማቀራረብ ረገድ ምን ያደረጉት ነገር ነበር?
ሼክ ሙሃመድ፡ በኢትዮጵያና በየመን መካካል ግኑኝነት ነበር ቢሆንም እኔ ከሄድኩ በኋላ ያደረግሁት ነገር ቢኖር ግልጽ ያልነበረዉን የባህር ሀብታችንን ማካፈል ነው። በተጨማሪም ወንጀለኛን መለዋወጥ ማለትም የየመን ወንጀለኛ ኢትዮጵያ እንዳይቀመጥ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ የመን ውስጥ እንዳይቀመጥ። ሌላው ብዙ ነው ትዝ አይለኝም።
ሳዲቅ፡ከየመን ሌላ በአምባሳደርነት የሰሩበት አገር አለ?
ሼክ መሃመድ፡ ስምንት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ወደ ካይሮ ግብፅ እንድዛወር ተወስኖ ሳለ ስራ ከመጀመሬ በፊት የመንግስት ለውጥ መጣ። በደርግ ጥሪ ተደርጎልኝ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዉስጥ የመካከለኛዉ ምስራቅ አገሮችን እንዳነጋግርና የመንግስትን ፖለቲካ እንዳሰራጭ ስራ ተሰጠኝ። ይህ በተጽዕኖ የመጣው የኮሚኒስት ስርዓት ለኢትዮጵያ አይመችም ብዬ ኢትዮጵ ያን ለቅቄ ወደ የመን ሄድኩኝ ከዚያም ወደ ሳውዲ አረቢያ በመሄድ ለ13 ዓመታት ከተቀመጥኩ በኋላ በስራ ምክንያት ወደ አሜሪካ መጣሁ።
ሳዲቅ፡ ወደ አሜሪካ እንዴት መጡ?
ሼክ ሙሃመድ፡መካ ያለው ራቢጠተል አለመል ኢስላሚያ (Muslim World League) የተሰኘው ድርጅት ኒውዮርክ ባለው ቅርንጫፍ ቢሮው ስራ ሰጥቶኝ ነው የመጣሁት።
ሳዲቅ፡ ራቢጣ በሚሰሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚጠቅም ምን ያደረጉት ነገር አለ?
ሼክ መሃመድ፡ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች የሚመሩ ኡለሞች ክፍያ አልነበራቸውም በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ያሉ ኢማሞች ደሞዝ ሲኖራቸው የኢትዮጵያ ኡለሞች ደሞዝ የላቸውም። ለብዙዎቹ ደሞዝ እንዲከፈላቸው አድርጌአለሁ። ትምህርት ቤቶች እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርቤ ነበር ግን አልተፈጸመም። የራቢጣ ስራዬን በ1997 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) ስጨርስ በብዙ ወንድምና እህቶች ጥያቄ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ መጣሁ። የኔው ከሆኑት ሙስሊሞች ጋር በመገናኘት ደዕዋ (ሰበካ) ማድረግ ጀመርኩኝ። በዓመት በዓል ካልሆነ የማይገናኙትን ሙስሊሞች መገናኘት በመጀመራቸው ቤት ተከራይተን ትምህርታችንን ቀጠልን። ዛሬ አለሀምዲልላህ የራሳችን መስጂድ ብሎም የራሳችንን ሬዲዮ ፕሮግራም ለማስተላለፍ በቅተናል።
ሳዲቅ፡ ስንት ልጅና የልጅ ልጆች አሎት?
ሼክ ሙሃመድ፡ አስራ አራት ልጆች አሉኝ። ስምንት ወንድ ሰባት ሴቶች አስራ ስምንት የልጅ ልጆች አሉኝ።
ሳዲቅ፡ለመላው ኢትዮጵያውያን የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ሼክ ሙሃመድ፡ መልዕክቴም አደራችሁን አደራችሁንዲናችሁን(ሐይማኖታችሁን) አጥብቃችሁ ያዙ፤ እንደ ማዕበል ወደላይና ወደታች የሚማታ ነገር መጥቷል። ሃይማኖቱ አንድ ነው ቁራአንና ሃዲስን ቀጥ ብላችሁ ያዙ።በዘመናችን ወጣቱን ግራ የሚያጋቡ ሰዎች አሉ፤ ወጣቱ የሰራው መጥፎ ስራ የለም። ተጠንቅቃችሁ ቁርዓንና ሐዲስን ይዛችሁ እንድትራመዱ፤ እውነትን እንድትይዙ፤ ለሸይጣን እጃችሁን እንዳትሰጡ። ሀቅ በጣም መሪር ናት ጀግንነት ያለው ሰው እንጅ ሌላ አይወጣትም፤ ስለዚህ አደራ የምላችሁ ዲናችሁን አጥብቃችሁ ያዙ፤ ሞት አይቀርም፤ ይህች ታልፋለች።
Source = Zehabesha