ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ከአንዱ የተለያየን አድርጎ ማቅረብ አሁን አሁን በሰፊው እየተሰማ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ የሚባሉ የታሪክ ሙሁራን ቢኖራትም ሙህራኑ በአገር ጉዳይ በያገባኛል መንፈስ በአንድነት ተሰባስበው ከመመካከር እና ከማስተማር ይልቅ ዝምታን መርጠዋል። የኢትዮጵያን እውነተኛውን ታሪክ ለህዝባቸው ከማሳወቅ ችልተኝነት ማሳየታቸው ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ እየሰራ ያለው ወያኔ ያስደስት ይሆናል። ወያኔ አሁን አሁን እየተከተለ ያለው የአረብ አብዮትን ነው። አረቦች ጥያቄአቸው እንዲመለስላቸው የሚፈልጉት በሁከት ነው። ግዛታቸውንም ማስከበር የሚፈልጉት በሁከት ነው። ሃሳባቸውን ሌላው እንዲቀበላቸው የሚፈልጉት በማስፈራራት እና በሁከት ነው። እየገደሉ ሞተብን ብለው ይጮሃሉ እያፈነዱ አፈነዱብን ብለው ይናገራሉ በሁሉ ነገር በደል ፈጻሚ ቀዳሚዎቹ እነሱ ሆነው ሳለ ምላሽ የሚሰጣቸውን አገር አረብን ሊያጠፋ ነው ብለው ሁሉም እንዲነሱላቸው ማሳደም መቀስቀስ ይጀምራሉ አንድ ችግር ሲያጋጥማቸው ይሄንን ያደረሱብን እንደዚህ የምትባል አገር እና እንደዚህ የተባሉ አገር ናቸው ብለው በራሳቸው የተፈጠረውን ጥፋት ከማመን ይልቅ ወደሌላ አገር ላይ በመለጠፍ አረብ አገር በሙሉ እና ወዳጅ አገሮታቸውን ጥላቻ እንዲቀረጽባቸው አድርጎ መመረዝ ነው። ወያኔም እየሄደበት ያለው አካሄድ ይሄንኑ ነው።
ኢትዮጵያ መሽቶ በነጋ ቁጥር አዳዲስ ነገሮችን የሚሰማባት አገር ሆናለች። እድሜ ለወያኔ በዘር ፐውዞ ፐውዞ አንተ አበሻ ነው እኔ አበሻ አይደለሁም። አንተ ሴም ነህ እኔ ኩሽ ነኝ። አንተ እንደዚህ ነህ እኔ እንደዚ አይደለሁም። አንተ ከገሌ ወገን ነህ እኔ ከእገሌ ወገን አይደለሁም የሚል ጫጫታ በስፋት እየተሰማ ይገኛል። ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት የተማረው እና ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሙህራኖች በአንድላይ ተሰባስበው ስለ አገር በማሰብ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እውነተኛውን ታሪካችንን ከማስተማር እና ከማሳወቅ ይልቅ ዝምታን በመምረጣቸው የተነሳ ወያኔ እና መድረኩን የፈቀደላቸው የማያውቁትን ታሪክ የየራሳቸውን ሃሳብ በማንጸባረቅ በተደጋጋሚ እየተነገረ እና በመጽሃፍም ጭምር እውነትነት የሌለው ታሪክ አስመስለው እየተጻፉ በመሆኑ እንደዚህ የተዛቡ ታሪኮች ሲነገር በአጉል ተስፋ ሰዎችን ስለሚሞላቸው የኢትዮጵያን ታርክ የኛ ታሪክ አይደለም ብለው እስከማመን እያደረሳቸው ነው። በዚህ የተነሳ የኛ ታሪክ ወድቋል፣ ጠፍቷል፣ ተሰርዟል፣ ተረግጧል…… ሌላም ሌላም እየተባለ ስለሆነ እውነተኛ ታሪክን እያፋለሱ ያሉትን ሰዎች ወደ ሚዲያው በማውጣት ከታሪክ ሙሁራኑ ጋር ፊት ለፊት በማገናኘትና በማነጋገር ኢትዮጵያን የማዳኑን ስራ ትሰሩ ዘንድ ጋዜጠኞች ትልቅ ድርሻም አደራም አለባችሁ።
ሴም ወይንም ሴሜቲክ ማን ነው? ኩሽ ወይንም ኩሸቲክ ማን ነው? ሐበሻ የሚባሉትስ እነማን ናቸው? የሚለውን እንመልከት
ኖህ፡- ሴም፣ ካም፣ እና ያፌትን ወለደ ዘፍጥረት ፲+ ፩-፴፪ (10+1-32)
ሴም፡- ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሎድ፣ አራም፣ ቃይናን ወለደ።
ካም፡- ኩሽ፣ ምስራይም፣ ፍጥ፣ ከነዓን ወለደ።
ያፌት፡- ጋሜል፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያህያን፣ ያልሳ፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣ ቴራስን ወለደ።
ከላይ የዘረዝርኳቸው የኖህ ልጆች እና የኖህ የልጅ ልጆች የሆኑ ናቸው።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በሆነ የዘር መጠላለፍ የሚታየው ይሄንን እውነት ካለመረዳት ነው። ሴም በሉት ሴመቲክ ኩሽ በሉት ኩሸቲክ ለሴም አባቱ ለኩሽ አያቱ የሆነው ኖህ ነው። ታዲያ የአንድ ዘር ግንድ የሆንን ወንድማማቾች ይሄንን ያህል መጠላላት እና መለያየት ለምን አስፈለገ? ዛሬ ሴሜቲክ ነን እያልን የምንፎክር ዛሬ ኩሸቲክ ነን ብለን የምንፎክር አባታችን አንድ እንደሆነ ሲነገረን መደምደሚያችን ኖህ እንደሆነ ስናውቅ ምን ይሆን መልሳችን። ከየት ተነስተን ወደ የት ነው የምንሄደው? ወዴየትስ ነው መሄድ የምንፈልገው? ከማንስ ተፈጥረን ነው የሌላ ነን የምንለው ዛሬ እኛ ሴም ነን እኛ ኩሽ ነን ብለን የምንናገረው የተፈጥሮ ዑደታችን እውነቱ ይሄ ነው። ለዚህ ነው ብንጣላ የማንኮራረፈው ብንሰዳደብ የማንራራቀው የአንድ ቤተሰብ ልጆች ስለሆንን ነው። ነገሮችን ጠለቅ ብለን ስናውቅ ማንነታችንን እናውቀዋለን ማንነታችንን ስናውቅ ታሪካችንን እንወዳለን ታሪካችንን ስንወድ አገራችንን እንገነባለን አገራችንን ስንገነባ ለአለም ሁሉ የፍቅር፣ የሰላም የአንድነት የስልጣኔ መሰረት ሆነን እንታያለን።
ሌላው ሐበሻ ሴሜቲክ ናቸው እንጂ ኩሸቲክ አይደሉም ይሉናል። ከመነሻው እንዳየነው ሴም ለኩሽ አጎቱ ነው የኩሽ አባት እና ሴም ወንድማማቾች ናቸው ማለት ነው። በቃ የኛ አመጣጥ እዚህ ጋር በአራት ነጥብ ተዘግቷል። ኩሸቲክ እና ሴመቲክ የአንድ ዘር ልጆች ነን። ታዲያ ሐበሻ የሚለው ቃል የመጣው ከየት ነው? ከተባለ መልሱ ከአረቦች ነው።
ነብዩ መሃመድ ከቆሬሾች ጋር ከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት በጃፋር መሪነት የነብዩ የቅርብ ሰዎች የነበሩትን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ የተናገሩትን ቃል እጠቅሳለው ቃሉ ቃል በቃል ከቁርአን ነው የተወሰደው << ሐበሻ (ኢትዮጵያ) የእውነት አገር ናት በውስጧም ሰውን የማይበድል እርሱም ዘንድ አንድም የማይበደል ንጉስ አለና ወደዚያ ብትሄዱ መልካም ነው>> ይላል። ነብዩ መሃመድ በእስልምና እምነት አማኞች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰው ናቸው። ሐበሻ የሚለውን ስም እስካሁንም ድረስ አረቦች ይጠቀሙበታል። ታዲያ በነብዩ መሃመድ እንዲህ የተገለጹት ደግ በደልን የማያደርጉ ህዝብን የማይበድሉ መሪ ኢትዮጵያ ነበራት። እኚህ መሪ የሴምም የኩሽም ልጅ የሴምና የኩሽ ሃረግ የነበራቸው መሪ ናቸው እንጂ ዛሬ ዛሬ እንደሚነገረው የወያኔ ፖለቲካ እና የወያኔ አካሄድ የሚከተሉ እንደሚሉት ሐበሻ ስለተባሉ የሴም ወገን ናቸው ተብሎ መነገሩ የራስን ታሪክ ጠንቅቆ ካለመረዳት እና የፖለቲካን ትርፍ ለማግኘት ተብሎ ታሪክን በገዛ ፍቃድ እንደመጣል ይቆጠራል። ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የታሪክ፣ የጀግንነት፣ የስልጣኔ፣ የሃይማኖት፣ የስነ ፈጠራ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ ድርሻ የሴምም የኩሽም እኩል ታሪክ ነው። ማንም ከማንም የተነጠለ ታሪክ የለንም። ማንም ከማንም የሚለያይ ስራም የለንም። ወያኔ ለአገዛዙ ማቆያ ለስልጣኑም ማራዘሚያ በማሰብ መጀመሪያ እና መሃል የሌለው ጫፍ ብቻ ያለው ታሪክ ይነግረናል። ጫፉ ላይ ወጥተን ከማንነታችን ውጪ ግዜአዊ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ማንነታችንን እና አገራችንን አደጋ ላይ መጣል ተገቢ አይደለም ነገም ታሪክ ይጠይቀናል ማንም ከተጠያቂነት አያመልጥም። ስለዚህ ወደ እውነተኛው ማንነታችን መመለስ ያስፈልገናል።
እንደ ማሳሰቢያ መናገር የምፈልገው አንድ ሰው የተለየ ሃሳብ ለምን አመጣ ተብሎ አይከለከልም ማንም የፈለገውን ሃሳብ ማምጣት ይችላል ያንን ሃሳብ ግን በማስረጃ ሊያቀርብ ያስፈልጋል። በነጻ ሚዲያ ዘርፍ የተሰማራችሁ ጋዜጠኞች በታሪክ ዙሪያ የተለየ ሃሳብ ያለው ሰው ካለ ወደሚዲያው በመጋበዝ ከታሪክ ሙሁራኑ ጋር ግልጽ ትንታኔ ከሁለቱም ወገን እንዲሰጡበት በማድረግ እና ጥያቄአቸውን በማስረጃ እንዲመልሱ በማድረግ እውነታውን ህዝቡ እንዲያውቀው የማድረጉን ስራ ቢሰራ በህዝቡ ዘንድ የሚኖሩትን ብዥታዎች ያጠራዋል። ህዝብን በመከፋፈል ዙሪያ ወያኔ የሚጠቀምበትን መንገድ አንድ አንዶችም በመከተል ላይ ስለሆኑ የፈረሰውን በመገንባት የሃሰት ታሪካዊ ወሬዎችን እውነተኛ በሆነው ታሪክ በማነጽ ያስፈልጋል። ጥያቄ አንሺውን እና ሙሁራኑን በማገናኘት በየግዜው ትንታኔ እንዲሰጥበት በማድረግ በጋዜጠኝነት ሙያውስጥ ያላችሁ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአገራችሁ ታሪክ ስሩ። ኢትዮጵያን ወደ ሰላሟ እና ወደ እረፍቷ የሚያመጣት መልካም መንገድ ነውና።
ከተማ ዋቅጅራ
Email- waqjirak@yahoo.com
Source = http://ethiomunich.com/