ከፍ ባለ ድምፅ ‹‹ተሾመ እባላለሁ›› በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ በንግግራቸው ንዴት፣ ቁጭትና ፀፀት የተደበላለቁባቸው ይመስላል፡፡ ‹‹ስለመጽሐፉም ስለደራሲውም የምለው አለኝና ትንሽ እንድናገር ይፈቀድልኝ፤›› በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡
‹‹በበጎም በክፉም እንተዋወቃለን፡፡ ጓድ ብዬ መጥራት ግን አልፈልግም፤›› ሲሉም ቀጠሉ፡፡ ታዳሚዎችንም ፈገግ አሰኙ፡፡ ከደራሲው ጋር ቅርበት እንደነበራቸው ያስታውቃሉ፡፡ ‹‹በጠባያቸው ቆፍጣና ናቸው፡፡ በተለይ በቁም ነገር አዘል ቀልዳቸው ይታወቃሉ፤›› ብለዋል፡፡ በመግቢያ ንግግራቸው የተነቃቁት ታዳሚዎች፣ ይበልጥ ረገጥ አድርገው የሚያወጡትን ኃይለ ቃል የተሞላበት ንግግር ጆሮአቸውን አቅንተው ያዳምጣሉ፡፡ ፊት ለፊት አካባቢ አጠገባቸው ከተቀመጡ ሰዎች ውጪ አብዛኛው ሰው የሚያውቃቸው አይመስልም፡፡ እንግድነት ደግሞ አይነበብባቸውም፡፡ ከደራሲው ጋር የሆነ ነገር እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ግን መድረክ ላይ ተቀምጠው በግርምት ይመለከቱዋቸዋል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል የሎተና ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ መጽሐፍ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የጥንት ዘመን አስተዳደርም ሳይቀር ዓይነተኛ መለያው ‹‹ዳኝነት›› መሆኑን አውስተው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት ነፍጋችሁ መብታችን ይከበርልን አላችሁ፡፡ ይኼው መብታችሁ ተከበረላችሁ፤›› አሉ፡፡ ‹‹ሞት እንዲፈረድብዎት ተከራክሬያለሁ፡፡ የእርስዎን ክፉ ማየት አልፈልግም፡፡ ይኼ ግን የአገር ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ፣ የመድረኩ መሪና አወያይ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ አቋረጧቸው፡፡
‹‹ይቅርታ አቶ ተሾመ መጽሐፉን አንብበውታል?›› በማለት ፕሮፌሰር ገብሩ ጠየቁ፡፡
‹‹አላነበብኩትም›› ጥቁር ሙሉ ልብስ የለበሱት አቶ ተሾመ መለሱ፡፡
‹‹ለአሁኑ ይብቃዎትና ይቀመጡ፣ ለሌሎች ዕድል ልስጥ፤›› አሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
‹‹እንዲህ ነው? እቀመጣለሁ፡፡ ስለማምንበት አይደለም፡፡ ባለሥልጣኑን ሥልጣኑን ስለማከብር እቀመጣለሁ፤›› ብለው ተቀመጡ፡፡
ታዳሚዎች ትንሽ የመረበሽ ስሜት ቢስተዋልባቸውም አወያዩ ለሌላ ሰው ዕድል ሰጡ፡፡ እኚህ አስተያየት ሰጪም መጽሐፉን አላነበቡም፡፡ በእርግጥ በሥፍራው የተገኙ ታዳሚዎችም ሆኑ አስተያየት ሰጪው መጽሐፉን ቀድመው አግኝተው ያነበቡ አይመስሉም፡፡
ስማቸው ያልተገለጸው ሁለተኛው አስተያየት ሰጪ መጽሐፉን ትተው ቀደም ብለው አስተያየት ስለሰጡት አቶ ተሾመ ገብረ ማርያም መናገር ቀጠሉ፡፡ ‹‹ይኼ ሰውዬ ደፋር ነው፡፡ የወንድሜ ጓደኛ ነው፡፡ በደንብ ነው የማውቀው፡፡ ድፍረቱ ወሰን የለውም፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ምክትል ሚኒስትር ሆኖ እንድናምፅ ሲቀሰቅሰን ነበር፡፡ ሲያስተባብረን የነበረ ሰው ነው፤›› አሉ፡፡
በመቀጠልም፣ ‹‹ከዚህ መንግሥት ጋር በመሆን ጓዶች ሞት እንዲፈረድባቸው ስንት የደከመ ሰው ነው፤›› በማለትም ስለአቶ ተሾመ ተናገሩ፡፡ አወያዩ ፕሮፌሰር ገብሩ፣ ‹‹ይቅርታ መጽሐፉ ላይ ብናተኩር?›› አሉ፡፡
‹‹በቅድሚያ ጓድ ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ እንኳን ደስ አለዎት፡፡ እንኳን ለዚህ አደረሰዎት እላለሁ፤›› ሦስተኛ አስተያየት ሰጪ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ እኚህ አስተያየት ሰጪ ከሁለቱ ለየት ያሉ ናቸው፡፡ መጽሐፉን አንብበውታል፡፡ ታዋቂው የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ ይባላሉ፡፡
‹‹ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ የሰሙትን ማስተጋባት ልማድ በሆነባቸው ሰዎች ብዙ ተብሎባቸዋል፤›› በማለትም የመጽሐፉን የተለያዩ ገጾች በመጠቆምና ስማቸው መጠቀሱን ተናግረው ወደ አስተያየታቸው አመሩ፡፡
በአንድ ወቅት አራት ኪሎ በነበረው የኢሠፓ ጽሕፈት ቤት ብቻቸውን አስጠርተው ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ የነገሩዋቸውን ተረኩ፡፡
‹‹ፍሰሐ በአብዮቱ ላይ እያሴረ ነው ብላችሁ እመኑ ተብለው ብዙ ሰዎች እየተገረፉ ነው፡፡ ምናልባት አንድ ነገር ከሆንኩኝ ለምስክርነት ነው ያስጠራሁህ፤›› እንዳሏቸውም አስታውሰዋል፡፡ አቶ ሞላ በመቀጠል፣ ‹‹ሁሉም ሰው በወቅቱ ስህተት ሠርቷል፡፡ እኔን ጨምሮ፤›› አሉ፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንድትጓዝ ማድረጉንም መስክረዋል፡፡ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በፍርድ ቤት እንዲዳኙና በመጨረሻም በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉንም አድንቀዋል፡፡
በኢሠፓ የመደራጀት ጥያቄ
አቶ ሞላ፣ ‹‹ትናንት ለአገራችን ብዙ ነገር የሠራን ሰዎች አለን፡፡ ደንቆሮዎች ሆነን በወታደሮች ብንመራም ብዙ ነገር የሠራን ሰዎች ነን፡፡ አምስት ሚሊዮን አባላት ያሉት ፓርቲ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ዴሞክራሲንና ነፃነትን የሚረጋገጠውና ዕርቅ የሚፈጠረው እነዚህ የቀድሞ አባላት መደራጀት ሲችሉና መድረክ ሲመቻችላቸው ብቻ ነው፤›› በማለትም የኢሠፓ አባላት ዳግም እንዲደራጁ ጠይቀዋል፡፡
ለጥቂት አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት ኮሎኔል ፍሰሐ ግን የኢሠፓ በድጋሚ የመደራጀት መብት የተዘጋ እንደሆነ፣ በሕገወጥነት የፈረሰን ፓርቲ ማደራጀት ወንጀል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላ ዕድል የተሰጣቸው ተናጋሪ የውይይቱ አካሄድ መሆን ያለበት በመጽሐፉ ላይ ተንተርሶ እንደሆነ ተናግረው፣ ‹‹እገሌ እዚህ ነው የተወለደው››፣ ‹‹የእገሌ ጓደኛ ነበር››፣ ‹‹እንዲህ ሠርቷል››፣ ወዘተ. ከሚል የሰዎችን ሰብዕና ከማጉደፍ ነፃ እንዲሆን ጠይቀው ንግግራቸውን ገቱ፡፡
ቀጥሎ ፕሮፌሰር ፍሰሐ ጽዮን መንግሥቱ ዕድሉ ሲሰጣቸው ወዳጆች እንደነበሩና እሳቸው አምስተርዳም በነበሩበት ወቅት፣ ኮሎኔል ፍሰሐ እዚያ በሄዱ ጊዜ የፖለቲካ አቋም ሳይገድባቸው አግኝተዋቸው መነጋገራቸውን አድንቀው አስተየየታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በፖለቲካ አመለካከት ወንድም ከወንድም ጋር መጋደሉን አስታውሰው፣ ‹‹አሁንስ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተመችቶታል ወይ? ያ ሁሉ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ በሠለጠነ ቋንቋ መነጋገር አልተቻለም፤›› በማለት አሁን ያለው አዲሱ ትውልድም ካለፈው የተሻለ እንዳልሆነና የመጠፋፋትና የአለመነጋገርን ታሪክ ነፃ አለማድረጉን ተናግረው ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ከዚያ ቀጥሎ ሌሎች መጽሐፉን ያነበቡ ሰዎች አንዳንድ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ኢንጂነር ታደሰ ኃይለ ሥላሴ ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ በደርግ ጊዜ የተፈጠሩ ስህተቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ቁልጭ አድርገው በማሳየታቸው አድንቀው፣ አንድ ቦታ ላይ ግን ፀቡ በተማሪዎችና በአብዮተኞች መካከል ነበር ብለው ጸሐፊው ማስፈራቸውን ግን ተቃውመዋል፡፡ ‹‹አንደኛው ፕሬዚዳንቱ [ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም] የሁሉ ነገር ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ፡፡ ለውጥ ማምጣት ያልቻላችሁት እውነትን ተከትላችሁ ስላልሠራችሁ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች መካከል ቀደም ብሎ ከአንድ አስተያየት ሰጪ የተነሳውን የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተም ኢንጂነሩ ሲናገሩ፣ ‹‹መድረክ ሲዘጋጅ ምን ያስቀመጡት ራዕይ አለ?›› ብለው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ደሃ የሆንነው የምሥራቅ አውሮፓ ሶሻሊዝም ስለተከተልን ነው፡፡ አጉል ፍልስፍና፣ የሰነፎች ፍልስፍና ታጥቀው በእሱ ስለመሩን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ይህንን ካባ አውልቀነዋል ወይ?›› በማለት የመድረኩን አስፈላጊነትና ዓላማን በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
‹‹ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ራስ ወዳድ››
መጽሐፉን ከገመገሙ ሦስት ሰዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ይገኙበታል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ እስካሁን ከተጻፉት የተሻለ ይዘትና ጥልቀት ያለው መሆኑን ተናግረው፣ በተለይ ደራሲው ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ በወቅቱ ትክክል ነው ብለው ያራመዱትን አቋም አሁንም ማንፀባረቃቸውና በጊዜና በሁኔታዎች አለመቀያየራቸው ፅናታቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአፈ ታሪክና ከአገሩ የሰማናቸው ነገሮች የደርግ አባላት 120 እንደነበሩ ሲሆን፣ 109 መሆናቸው ከመጽሐፉ አሳማኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፤›› ያሉት ዶ/ር ካሳሁን፣ በደርግ የተረሸኑት የአፄ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት 60 መባላቸው ስህተት መሆኑና 54 መሆናቸውና የተቀሩት ባለሥልጣናት እንዳልሆኑ፣ ደራሲው አብራርተው መጻፋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን በደርግ ጊዜ በተለይ የመሬት አዋጅንና የሶማሊያ ወረራን ለመቀልበስ የተደረገው ዘመቻ አድንቀው ወደ ልዩነት ነጥብ አምርተዋል፡፡
ከ20 ዓመታት እስር በኋላ በይቅርታ የተፈቱት ኮሎኔሉ በመጽሐፋቸው መጨረሻ የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ቆራጥ አገር ወዳድ ናቸው!›› ማለታቸውን እንደማያምኑበት ገልጸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ሽሽት በተመለከተ ተታልለው ነው የሄዱት፣ ሳያውቁ ነው ከአገር የወጡት ሲባል መቆየቱንና በመጽሐፉ አማካይነት ሸሽተው መውጣታቸውን እንደተረዱ ገልጸው፣ ‹‹እስካሁን አገር ወዳድ ነበሩ የሚለውን አስተሳሰብ ለመቀበል ያስቸግረኛል፡፡ ‘በእርግጥ ኢትዮጵያ አገሬ’ ይላሉ፡፡ አገር ወዳድ ነበሩ ለሚለው ግን ከሁሉም በላይ ራስ ወዳድ ነበሩ፡፡ ከሥልጣናቸውና ከግል ጥቅማቸው ቀጥሎ ነበር አገር የሚወዱት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን የአገር ፍቅር ያለው ሰው፣ ‘የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ሲዘምት እንጂ ሲዘመትበት አይታይም’ ብሎ ሕዝብ በሕዝብ ላይ አይቀሰቅስም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አገር ወዳድ ከሆኑ፣ አገርን ጥለው ከመሸሽ እንደ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን በሰጡላት፣ ወይም እንደ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ባጠፉ ብለዋል፡፡ ‹‹መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ አልነበሩም!›› በማለትም ደራሲው አሁንም አገር ወዳድ ነበሩ ብለው መግለጻቸውን ሞግተዋቸዋል፡፡ በእርግጥ ኮሎኔል ፍሰሐ ለዚህ ግምገማ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹በመጨረሻ ከአገር ሸሽተው እስከሄዱ ድረስ አገር ወዳድ ነበሩ!›› የሚል ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጄኔራል አማን ሚካኤል አምዶም ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ባይፈጸም፣ የኤርትራ ጉዳይ የተለየ ይሆን ነበር ተብሎ በመጽሐፉ የቀረበውን ትንታኔም እንደማያምኑበት ዶ/ር ካሳሁን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የአማን አምዶም መገደል ብቻ ሳይሆን ትልቅ የፖለቲካ ስህተት ተፈጽሟል፤›› ብለዋል፡፡ ኮሎኔሉ ግን እሳቸው ባይገደሉ ውጤቱ የተለየ ይሆን ነበር የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር
ዶ/ር ካሳሁን ማንም ይጀምረው ማን ቀይ ሽብርም ነጭ ሽብርም የኢትዮጵያ ታሪካዊ መጥፎ ገጽታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጣን ላይ የነበረው አካል የፈጸማቸው ግድያዎች ግን በወቅቱ ከነበሩት ሁኔታዎች አንፃር መታየት አለባቸው ብለው፣ ለአብነትም ያቀረቡት የሶማሊያ ጦርነት፣ የኤርትራና የትግራይ አማፂዎች ጉዳይ፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ የእርሰ በርስ ፉክክሩን ነበር፡፡ አንድ ጥያቄ ያቀረቡ አስተያየት ሰጪ ግን፣ ‹‹ምኑ ነው ግንዛቤ ውስጥ የሚገባው ዓውድ? የግድያ ትንሽ ትልቅ አለው ወይ?›› በማለት ተቃውመዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን፣ ‹‹በወቅቱ የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ግምት ውስጥ መግባት አለበት ማለት የተፈጸመውን ትክክል ነበር ማለቴ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የይቅርታ አርዓያ
ከገምጋሚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ ‹‹የሥነ ጽሑፍ ሃያሲ የለንም፣ እኔም ዓይን አውጣ ሆኜ ነው፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ በማድረግ ግምገማቸውን ጀምረዋል፡፡ በተለይ መጽሐፉ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳቱን ተናግረዋል፡፡ አንደኛ ኮሎኔል ፍሰሐ እስካሁን ከደርግ ባለሥልጣናት መካከል በግላጭ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ቀዳሚ መሆናቸው ወደር የሌለው ቁርጠኝነት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ትልቅ የአገር አርአያነት›› በማለት ‹‹ኮሎኔሉ የሚያልሟት ኢትዮጵያ የምትገነባው መቼ ነው?›› በማለት ከጠየቁ በኋላ፣ ‹‹ሥልጣን ላይ ይወጡና ሳይገነቧት ይወርዳሉ፡፡ አንዱ የጀመረው ከሥር መሠረቱ ይናዳል፡፡ ምዕመናን ተስፋ አይቆርጡም ካላላችሁን በስተቀር መቼም የምትገነባ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን ፀሎት እንዳይቋረጥብን፣ ሌሎች ሰዎች ጠላታችንን እንዲገድሉልን የምንመኝ ሰዎችን ነን፤›› ብለዋል፡፡
የተዘበራረቁ ስሜቶች
ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የመድረኩ መሪ ሆነው የተዘበራረቀ ስሜት የፈጠረባቸው የታሪክ ምሁርነት፣ ኢትዮጵያዊነታቸውና ራሳቸው የፖለቲካ ተሳታፊ መሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከደራሲው ከሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ የተለዩባቸው ነጥቦች ላይ በማተኮር፣ በመጽሐፉ ትግሉ በአብዮተኛና በፀረ አብዮተኛ መካከል ሆኖ መቅረቡን ተቃውመዋል፡፡ ሦስቱ ተሳታፊ ድርጅቶች ማለትም ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ደርግ በተለይ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ውስጥ የነበራቸው ግንኙነት የማይታረቅ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አልነበረም ብለዋል፡፡ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችና ነፃ አውጪ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የማዕከላዊ መንግሥት መድቀቅ ለደረሰው መጨፋጨፍ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹አንድ ትውልድ አለቀ›› ብለው ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐንና ፕሬዚዳንት መንግሥቱን ኢሕአፓን በቆራጥነቱ ማድነቃቸውን ገልጸው፣ እሳቸውም ሕዝባዊነቱንና የዓላማ ቆራጥነቱን አውስተዋል፡፡
ኢሕአፓን በመከላከል የሚታወቁት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ‹‹ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን አምኜያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ይህን ሲሉም በከፍተኛ ጭብጨባ ታጅበዋል፡፡ ለዚህ የአቋም ለውጥ መነሻ የሆናቸውን ሲገልጹም፣ ‹‹አሁን በዕድሜም እየገፋሁ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የኢሕአፓ ውድ ታጋይ አስማማው ኃይሉ (አባ ሻውል) ስለ ኢሕአሠ ከጻፈው ሁለተኛ ቅጽ ካገኘሁት ግንዛቤ በመነሳት ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብያለሁ፤›› በማለታቸው ነበር ከሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች በከፍተኛ ጭብጨባ አድናቆት የተቸራቸው፡፡
ግምገማቸውን ሲያጠቃልሉ በተለይ የሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ‹‹እኛና አብዮቱ›› መጽሐፍ ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መጽሐፍ የተሻለ ነው ብለው፣ ‹‹አሁን ደግሞ የኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ከስፋትና ጥልቀት፣ ከዝርዝር አቀነባበርና ከሚዛናዊነት አንፃር የተሻለ ነው፡፡ ያልዳሰሱት ጉዳይም ያለ አይመስለኝም፤›› በማለት በአንፃራዊነት በጣም የተሻለ ሥራ ብለውታል፡፡
የሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ የመጽሐፍ ምረቃ ፕሮግራም ላይ በተለይ የኢሕአፓና የመኢሶን አባላት በነበሩት መካከል ጠርዝ የያዘ ጭቅጭቅ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ ‹‹ደርግ በወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ በማወቅ፣ በድፍረት፣ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤›› የሚለው በመጽሐፉ የፊት ሽፋን የውስጥ ገጽ ያሰፈሩት ቁም ነገር ለታዳሚዎች የተለየ ትርጉም የሰጠ ነበር፡፡ አስተያየት ሰጪዎችም ሆኑ ገምጋሚዎች፣ ትንተናቸው መሠረት የሚያደርገው ከዚሁ ዓረፍተ ነገር እየተነሳ ሲሆን፣ ብዙዎች ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐን በዚህ አገላለጻቸው በአርዓያነት አሞግሰዋቸዋል፡፡
Reporter Amharic