Wednesday, 02 December 2015 14:25
የጋሞ ብሔር ተወላጆች
በይርጋ አበበ
ከወራት በፊት በህግ ባለሙያው አቶ ታደለ ቱፋ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃው “ማዶላ የማላና ዶጋላ ህዝብ ታሪክ” የሚለው መጽሀፍ በጋሞ ብሄረሰብ ላይ አድርሶታል የተባለው የክብርና የማንነት ጥሰት እስካሁንም መልስ እንዳልተሰጠው የብሔረሰቡ ተወካዮች ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናገሩ።
የ6ሺህ 734 ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ አሰባስበው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለኢህአዴግና ለደኢህዴን ጽ/ቤቶች እና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ለሌሎች የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ተቋማት ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን የገለጹት የአገር ሽማግሌዎቹ “ለ20 ቀናት ሙሉ ጥያቄያችንን ይዘን ከአንዱ ተቋም ወደሌላ ተቋም ብንመላለስም መልስ የሚሰጠን አካል አላገኘንም። በተለይ መልስ ይሰጡናል ብለን ተስፋ አድርገናቸው የነበሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ቢሆንም ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጥያቄው ከእኔ አቅም በላይ ነው ብለው መመለሳቸው አሳዝኖናል። ለስድስት ጊዜ ያመላለሰን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤትም ጥያቄያችሁን ማስተናገድ አልችልም ብሎ መልሶናል” ብለዋል።
የአገር ሽማግሌዎቹ አያይዘውም “የጋሞ ህዝብ ሰላማዊና ሰው አክባሪ ቢሆንም እንደ አቶ ታደለ ቱፋ አይነት በብሄሩ ተወላጆች ላይ የንቀት ስድብ ሲሰድቡን መብታችንን አስከብሩልን፣ ደራሲውንና ግብረ አበሮቹን በህግ ጠይቁልን፣ መጽሐፉም ተሰብስቦ ይቃጠል የሚል ጥያቄ ይዘን ብንቀርብም ‘ይህ የጥገኞች አስተሳሰብ ነው። አሸባሪዎች ናቸው’ እያሉ በርካታ የብሄሩን ጥያቄ ያነሱ ግለሰቦችን አስረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “በተለይም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩትና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት መምህር አቶ ወንድምአገኝ አንጄሎ ‘የጋሞን ህዝብ የሚያዋርድ ስድብ የጻፈ ደራሲ ሊከሰስ ይገባል’ ብለው በመጠየቃቸው የግንቦት ሰባት አባል ተብለው ተጠርጥረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስደው በእስር ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብሔሩን ጥያቄ ተቀብለው መልስ ለመስጠት ተስፋ እንደሰጧቸው የገለጹት ሽማግሌዎቹ ደራሲው የጋሞን ብሔር ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም ህገ መንግስት ጥሰዋል ሲሉ ይናገራሉ። ሀሳባቸውን ሲገልጹም “የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ‘የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው’ ብሎ የሚደነግግ ቢሆንም አቶ ታደለ ግን በግልጽ ‘ጋሞ የሚባል ብሔር የለም’ ብለው መጻፋቸው ህገ መንግስቱን መናድም ነው። እኛም የህገ መንግስቱን አዋጅ ሳይቀር የጣሱትን ደራሲ በህግ እንዲጠየቁ የጋሞ ህዝብ ለዞኑ እና ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ቢያቀርብም ጥያቄውን ከመቀበልና መልስ ከመስጠት ይልቅ ጠያቂዎቹን ባልዋሉበት እየወነጀሉ ማሰርን መርጠዋል። ይህ ደግሞ ለዓመታት በሰላማዊነቱ ተለይቶ የሚታወቀውን የጋሞን ህዝብ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ያደርጉታል” ሲሉ ይናገራሉ።
የጋሞ ጎፋ ዞን ከጋሞ እና ከጎፋ ብሔረሰቦች ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አኃዝ ያለው ህዝብ የሚኖርበት ቢሆንም የጋሞ ብሔር ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሚናገሩት የብሔረሰቡ ተወካዮች “ነገር ግን በዞኑ የመንግስት መዋቅሮች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የጎፋ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ በአቶ ታደለ ቱፋ የደረሰብንን ጥያቄ ይዘን ስንቀርብ መልስ ለመስጠት ፍላጎት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል” ሲሉ ይገልጻሉ። አቶ ታደለ ቱፋ የጎፋ ብሔር ተወላጅ መሆናቸውንም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።
ደራሲው መጽሐፉን ከማሳተማቸው በፊት አስተያየታቸውን እንዲሰጧቸው የመጽሐፉን ረቂቅ ከጋበዟቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መካከል የደኢህዴን ጽ/ቤት የክልሉ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንደሆኑ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎቹ “ሆኖም አቶ ተስፋዬ የመጽሐፉ ረቂቅ እንደደረሳቸው ቢያምኑም ‘መጽሐፉ ላይ አስተያየት ለመስጠት ያልቻልኩት በምርጫ ስራ ተወጥሬ ስለነበረ ትኩረት ስላልሰጠሁት ነው’ በማለት ከደራሲው በላይ የክልሉን መንግስት የሚመራው የደኢህዴን ኃላፊ ንግግር በብሔሩ ላይ ቁጣን አስነስቷል” ሲሉ ገልጸዋል። “የዴታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኦኬ ቦሌ በበኩላቸው ‘ችግራችን ይስሙትና መፍትሔ ይስጡን’ ብለን ብንጠይቃቸው ‘መንግስት ወደ ህዝብ አይሄድም ህዝብ ነው ወደ መንግስት የሚሄደው ስለዚህ እናንተ ኑ እና አነጋግሩኝ’ አሉን። እኛም ልናነጋግራቸው ስንሄድ በሶስት መኪና ሙሉ የተጫኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን አሰልፈው ጠበቁን” ብለዋል።
ምንጭ ስንደቅ